22 Jun 2020

የመንግስት ኃላፊነት

የመንግስት ኃላፊነት
መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው ደግሞ አወቃቀሩና አደረጃጀቱ ሲገፉት የሚፍረከረክ ዓይነት ‘ልል’ ወይም ውስን መንግስት መሆኑ ቀርቶ ጡንቻው የዳበረና ስልጣኑ የሰፋ ጠንካራ መንግስት ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቆች መፍትሔ መስጠት የመንግስት ግዴታ ነው ሲባል ሚናው ከተለመደው ስርዓትና ፀጥታ ማስከበር ባሻገር ሰፊና ውስብስብ አዎንታዊ ተግባራትን ወደ ማከናወን መሸጋገር እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡በዚሁ መሰረት የመንግስት ሚና ቀስ በቀስ ከፖሊስነት (Police State) ወደ ማህበራዊ አገልግሎት አቅራቢነት ሊሸጋገር ችሏል፡፡ መንግስት በአገልግሎት አቅራቢነት ሚናው ውሀ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ ወዘተ የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጐቶችን የማሟላት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅጣጫውን ፈር ለማስያዝና ፍትሐዊ የሀብት ድልድል እንዲኖር እንዲሁም ለደካማው የህብረተሰብ ክፍል ጥበቃና ከለላ ለማድረግ በአጠቃላይ የነፃ ገበያን አሉታዊ ውጤቶችን ለመቀነስ ሰፊና ተከታታይ ቁጥጥርና ክትትል (Regulation) ያደርጋል፡፡ አዲሱ የማህበራዊ መንግስት አዲሱን አዎንታዊ ሚናውን በብቃትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ይወጣ ዘንድ በዓይነትና በይዘት የጠንካራ ስልጣን ባለቤት ሊሆን የግድ የሚል ሀቅ ነው፡፡cየስልጣን አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስልጣን በየጊዜው ወሰኑ፣ መጠኑና ቅርጹ እያደገና እየሰፋ በመጣ ቁጥር ግን የግለሰቦችን መብትና ነፃነት መንካቱ አይቀርም፡፡ የመንግስት ስልጣን እየተለጠጠ መሄድ አቅመቢስ ለሆነው ዜጋ የስጋት ምንጭ ነው፡፡ ፍፁም የሆነና ወደ ፍፁምነት የተጠጋ ስልጣን ወደ ህገ ወጥነትና የበዘፈቀደ ድርጊት የማምራት አደገኛ አዝማሚያ አለው፡:የአስተዳደር ህግ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የመንግስት ‘ጡንቻ መፈርጠም’ በቅጡ ለመቆጣጠር በታሪክ ሂደት በተጓዳኝ የተፈጠረ የህግ መሳሪያ ነው፡፡ መንግስት ተግባራቱን ለማከናወን ፖሊሲ ቀርጾ፣ ህግ አውጥቶ በሚያስፈጽምበት ወቅት በስልጣን እና በፍትህ (የግለሰቦች ነፃነት) መካከል ቅራኔ መከሰቱ የማይቀር እውነታ ነው፡፡ ጥያቄው ቅራኔው እንዴት ይፈታል? ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ የዚህ ቅራኔ የራሱ ውጤት ሲሆን ቅራኔውን በአንፃራዊ መልኩ ለማስማማትና ለማጣጣም በታሪክ ሂደት ብቅ ያለ ተግባራዊ መሳሪያ ነው፡፡d የአስተዳደር ህግ በዕቅድ ታስቦ የተወለደ ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ ህጉ በሁለት በጉልበት የማይመጣጠኑ ጐራዎች ማለትም በመንግስትና በግለሰብ መካከል ሚዛናዊነትንና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ይጥራል፡፡የአስተዳደር ህግ መንግስት በተለይ ስራ አስፈፃሚውና የአስተዳደር አካላት በህግ ከተፈቀደላቸው የስልጣን ክልል አልፈው ህገ ወጥ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ቁጥጥር የሚያደርግና ይህንንም የሚያረጋግጥ ህግ ነው፡፡e በዚህም የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የግለሰቦች ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዳይሸራረፉና እንዳይጣሱ ከለላ በመስጠትf ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ስልጣን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል መሪ ደንቦችን በማስቀመጥና ስነ ስርዓታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን በመዘርጋት የተለያዩ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችን በመጠቀም የግለሰቦችና የዜጐች መብቶችና ነፃነቶች እንዳይገሰሱና እንዳይደፈሩ ከለላ በመስጠት የህገ መንግስት ማስፈፀሚያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የአስተዳደር ህግ ምንነትለአስተዳደር ህግ ብያኔ በማበጀት ረገድ የመስኩ ባለሙያዎች በከፊልም ቢሆን የተለያየ እይታ አላቸው፡፡ በእርግጥ የአስተዳደር ህግ የጥናት ወሰኑን አስመልክቶ የሚከሰት ልዩነት ካልሆነ በቀር በመሰረታዊ እሳቤው ላይ የተራራቀ አቋም የለም፡፡ እንደ ህንዳዊው የአስተዳደር ህግ ምሁር አይ.ፒ. ማሴይ አገላለጽ በአስተዳደር ህግ ትርጓሜ ላይ ያለው ልዩነት ምንጩ በየጊዜው እያደገና እየተወሳሰበ የመጣው አስተዳደራዊ ሂደት ሲሆን ይህም ሂደቱን በሙሉ አጠቃሎ የያዘ ወጥ ትርጉም ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡gያም ሆኖ የአስተዳደር ህግ ትርጓሜ ቢያንስ ሁለት መሰረታዊ አላባውያንን ማካተት ይጠበቅበታል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ህግ ከይዘት ይልቅ ስነ ስርዓት ላይ የሚያተኩር ህግ ስለመሆኑ ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ውሳኔው እንዴት ተሰጠ? እንጂ ይዘቱ ትክክል ይሁን አይሁን ፍርድ ቤቶች ሆነ የአስተዳደር ህግ ጣልቃ የሚገባበት ጉዳይ አይደለም፡፡በሁለተኛ ደረጃ ማንኛውም የአስተዳደር ህግ ትርጓሜ የህጉን ዓላማ ግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ አቀራረብ እንዲያቅፍ ይጠበቅበታል፡፡ የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማ ወይም ተግባር ስልጣንን መቆጣጠር ነው፡፡h ያ ሲባል ግን የአስተዳደር አካላት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩና እንዳይላወሱ ማነቆ ሆኖ ያግዳቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የስልጣን ቁጥጥር ሲባል ማንኛውም ባለስልጣን ሆነ መስሪያ ቤት በህግ ተለይቶ ከተቀመጠለት የስልጣን ገደብ እንዳያልፍና ስልጣን ቢኖረውም እንኳን ስልጣኑን ፍትሐዊና አግባብ በሆነ መንገድ እንዲወጣ ያደርጋል ለማለት ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማና ተግባር ስልጣንን በተግባር መቆጣጠር እንደመሆኑ ይህን ባህርዩን ግምት ውስጥ ያላስገባ ብያኔ የተሟላ ተብሎ ሊወሰድ ሆነ ሊወደስ አይችልም፡፡ለንጽጽር እንዲረዳን በመስኩ ባለሙያዎች ለአስተዳደር ህግ የተሰጡ ትርጓሜዎችን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡ቤርናርድ ሺዋሬዝ (Bernard Schwartz) የአስተዳደር ህግን ‘በውክልና ህግ የማውጣትና አስተዳደራዊ ዳኝነት የመስጠት ስልጣን ባላቸው የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ህግ’ በማለት ይገልፀዋል፡፡i ይህ ብያኔ ጠባብ ከመሆኑ በቀር ስለ ህጉ ይዘት ገላጭ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በውክልና ስልጣን ህግ ከማውጣትና ከአስተዳራዊ የዳኝነት ስልጣን በተጨማሪ ይህ ስልጣን በፍርድ የሚታረምበትን የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስነ-ስርዓት እንዲሁም በፖርላማና በተለያዩ ተቋማት የሚደረግ ቁጥጥርንም ያካትታል፡፡ጄኒንግስ በበኩሉ የአስተዳደር ህግ ማለት ‘አስተዳደርን የሚመለከት ህግ ነው፡፡ ይህ ህግ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ግዴታ ይወስናል፡፡’ በማለት ይገልጸዋል፡፡j እንደ አይ.ፒ ማሴይ አስተያየት ይህ ትርጓሜ የአስተዳደር ህግን ከህገ መንግስት በግልጽ አይለይም፡፡ አስተዳደር ወይም ማስተዳደር ማለት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስልጣንን በመጠቀም የህብረተሰቡን ጉዳይ መምራት ማለት ነው፡፡k ለዚህም በዋነኛነት አደራ የተጣለባቸው አካላት የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የእነዚህ ተቋማት ስልጣንና ግዴታ በዝርዝር ህግ ተለይቶ ቢወሰንም የስራ አስፈፃሚው አካል ስልጣን በጠቅላላው የሚቀመጠው በህገ መንግስት ላይ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ሆነ ህገ መንግስት ሁለቱም የመንግስት አስተዳደርን ወይም የግለሰብና የመንግስትን ግንኙነት የሚመሩ ህጐች እንደመሆናቸው በመካከላቸው ያለው መለያ ክር በጄኒንግ ትርጓሜ ላይ በግልጽ ነጥሮ አልወጣም፡፡ታዋቂው የህገ መንግስት ሊቅ ኤ. ቪ. ዲሴይ የአስተዳደር ህግን በሶስት ደረጃዎች ከፋፍሎ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡lየአስተዳደር ህግ የመንግስት ባለስልጣናትን የህግ ስልጣንና ተጠያቂነት የሚወስኑትን የአንድ አገር የህግ ስርዓት የሚመለከት የህግ ክፍል ነው፡፡ግለሰቦች ከመንግስት አካላት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ያላቸውን መብትና ግዴታ ለይቶ ይወስናል፡፡እነዚህ መብቶችና ግዴታዎች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን ስርዓት ይዘረጋል፡፡እንደ ማሴይ ትችት ይህ ትርጓሜ የአስተዳደር ህግ አንድ አካል የሆነውን አጣሪ ዳኝነት (judicial review) ብቻ የሚመለከት እንደመሆኑ በይዘቱ ጠባብ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ከአጣሪ ዳኝነት በተጨማሪ በህግ አውጭውና በተቋማት (ለምሳሌ በእንባ ጠባቂ ተቋምና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን) አማካይነት የሚደረግ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችንም ያካትታል፡፡ ህጉ ከመንግስት ባለስልጣናትና ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ ከፊል የአስተዳደር አካላት ተብለው የሚፈረጁትን መንግስታዊ ኮርፖሬሽኖች፤ ዩኒቨርሲቲዎች እና በከፊል መንግስታዊ ነክ ስልጣን ያላቸውን ማህበራትm በተመለከተም ተፈጻሚነት አለው፡፡በመጨረሻም ታዋቂው የህንድ ምሁር አይ.ፒ. ማሴይ ከላይ ከተሰጡት ሰፋ ያለና የህጉን ባህሪያትና ተግባራት ጠቅልሎ የያዘ ብያኔ እንደሚከተው ያስቀምጣል፡፡የአስተዳደር ህግ የህዝብ አስተዳደር ህግ አካል ሲሆን የአስተዳደርና ከፊል አስተዳደር መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀትና ስልጣን የሚደነግግ፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥበትን ደንብና መርህ የሚያስቀምጥ፣ እንዲሁም ከግለሰቦች መብትና ነፃነት ውሳኔው የሚታረምበትን ስርዓት የሚወስን የህግ ክፍል ነው፡፡nይህ ትርጓሜ ከሞላ ጐደል ሁሉንም የአስተዳደር ህግ ባህርያት አጠቃሎ የያዘ በመሆኑ ተመራጭነት አለው፡፡ ከላይ ከቀረቡት የተለያዩ ትርጓሜዎች የሚከተሉት የጋራ ነጥቦች ይመዘዛሉ::አንደኛ፤ የአስተዳደር ህግ የአስተዳደር እና ከፊል የአስተዳደር አካላት ያላቸውን ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት ያጠናል፡፡o የማንኛውም የአስተዳደር አካል የስልጣን ምንጭ የሚገኘው ከማቋቋሚያ አዋጁ (Enabling Act) ሲሆን አልፎ አልፎ በሌላ ዝርዝር ህግ ይወሰናል፡፡ በአስተዳደር ህግ የመጀመሪያው ጥያቄ ውሳኔ ወይም እርምጃ የወሰደው አካል በህግ የተሰጠው ስልጣን አለው? የሚል ነው፡፡ ከሌለ ድርጊቱ ከስልጣን በላይ ስለሆነ ዋጋ አልባ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከድርጊቱ በስተጀርባ የህግ ስልጣን ካለ ውሳኔ ሰጪው ስልጣኑን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደተገለገለ ይጣራል፡፡ ካልሆነ ስልጣኑን ያለ አግባብ በሚገለገለው አካል ላይ ህጉ ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡ሁለተኛ፤ ህጉ ስልጣንን በመገልገል ሂደት ተፈጻሚ የሚሆኑ መሪ ደንቦችን፤ ስነ ስርዓቶችንና መርሆዎችን ያስቀምጣል፡፡ ህግ አውጭው ለአስተዳደር አካላት ስልጣን ሲሰጥ ስልጣኑ ተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ ህጋዊነቱንና ፍትሐዊነቱን የሚያረጋግጥ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታ አብሮ እንዲደነግግ ይጠበቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል ደንብና መመሪያ በማውጣት ረገድ ከሚመለከተው አካል ጋር የመመካከርና የህትመት ቅድመ ሁኔታዎች፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጥ የመሰማት መብትና የኢ- አድሎአዊነት መርሆዎችን በአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ወይም በዝርዝር ህግ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም በአስተዳደር ሂደቱ ውስጥ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ስፍራ አላቸው፡፡ ስልጣን በዘፈቀደ ሳይሆን በአግባቡ ስራ ላይ ዋለ ለማለት የሚቻለውም ያኔ ነው፡፡ሶስተኛ፤ የአስተዳደር ህግ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችን በተመለከተ የሚያጠና ህግ ነው፡፡p ልጓም የሌለው ስልጣን ለዜጎች መብትና ነፃነት ፀር ነው፡፡ የተጠያቂነት መርሕ እውን እንዲሆን የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችም በግልጽ ተለይተው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ህግ በፍርድ ቤት፤ በአስተዳደር ፍርድ ቤት፤ በህግ አውጭው እና በተቋማት የሚደረጉ የስልጣን መቆጣጠሪያ መንገዶችን በተግባር እየፈተነ ያጠናል፡፡አራተኛ፤ ህጉ በአስተዳደር አካላት ወይም በመንግስት ባለስልጣናት በተወሰዱ እርምጃዎች መብታቸው ለተጣሰና ነፃነታቸው ለተገፋ ዜጎች መፍትሔ ይሰጣል፡፡q መብት ያለ መፍትሔ ‘ላም አለኝ በሰማይ’ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ መብቱ የተጓደለበት ሰው አቤቱታ አቅርቦ መፍትሔ የሚጠይቅበትና የሚያገኝበት የህግ ክፍል ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ግብና ተግባራትየአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማና ተግባር ስልጣንን መቆጣጠር ስለመሆኑ በመስኩ ምሁራን ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሆኖም በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡ እንደ ብዙዎች የአስተዳደር ህግ ሊቃውንት የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ግብ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን ሲሆን የሚከተሉት ተግባራት ይኖሩታል፡፡ስልጣን መቆጣጠር (Control Function)የአስተዳደር ህግ ስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካልና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች፣ ሚኒስትሮች፣ ባለስልጣናትና ሌሎች ሹመኞች በህግ ተለይቶ የተሰጣቸውን ስልጣን አልፈው እንዳይሄዱና ህጋዊ ስልጣናቸውንም አለአግባብ እንዳይገለገሉበት ለመቆጣጠር የሚያስችለን የህግ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም ስልጣን በህገ
ወጥ መንገድ አለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመከላከል እንደ መገደቢያ መሳሪያነት ያገለግላል፡፡rግዴታ ማስፈፀም (Command Function)በአስተዳደሩ በሚፈፀም ድርጊት የዜጋው መብት ከሚጣስበት ሁኔታ ባልተናነስ ህጋዊ ግዴታን አለመወጣት በግል መብትና ጥቅም ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል፡፡ የአስተዳደር ህግ ስልጣን በልኩና በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውል ከመቆጣጠር ባሻገር የአስተዳደር አካላት በህግ ተለይቶ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ አስገዳጅ የስነ ስርዓትና ተቋሟዊ ስልቶችን ይቀይሳል፡፡s አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ከሌለ ግዴታ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ውዴታ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡የአስተዳደር ፍትህ ማስፈንበየትኛውም ህግን ለማስፈፀም ስልጣን በተሰጠው የመንግስት አካል የሚወሰዱ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የህዝብ አመኔታና ተቀባይነት እንዲያገኙ ፍትሐዊነታቸው በተጨባጭ ሊታይ ይገባል፡፡ የአስተዳደር ህግ አይነተኛ ተልዕኮ የአስተዳደር ፍትህን ማስፈን ነው፡፡tግልጽነት ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎየአስተዳደር ህግ በመንግስት አስተዳደር ስራ ውስጥ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ተግባራዊ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ የስልጣን ልኩ ሳይታወቅና ከልክ በላይ የሆነ ስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቱ ሳይቀየስ ስለተጠያቂነት ማውራት የማይመስል ነገር ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን በህግ የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በህዝብ አስተዳደር ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የስነ- ስርዓት ደንቦችን ይዘረጋል፡፡ለተበደለ ወገን መፍትሔ መስጠትየአስተዳደር ህግ ዜጎች ለደረሰባቸው በደል በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ባሉ መንገዶች አቤቱታ አቅርበው በአነስተኛ ወጪ እና በቀላሉ መፍትሔ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ስለ አስተዳደር ህግ በተደጋጋሚ ቢወራ ‘አንጀት ጠብ’ የሚል፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፣ መፍትሔ እስከሌለ ድረስ ረብ የለሽነቱን ያጎላው እንደሆነ እንጂ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የአስተዳደር ህጋቸው በዳበረ አገራት የመንግስት ባለስልጣናት በህዝብ ላይ ለሚፈፅሟቸው አስተዳደራዊ በደሎች በዝርዝር የተቀመጡ የመፍትሔ መንገዶች አሏቸው፡፡በአንድ አገር ውስጥ የአስተዳደር ህግ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተወጥቷል ለማለት ከአገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት፤ ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ዕድገትና የአስተዳደር ህግ ተቋማት መዳበር ከግምት ውስጥ በማስገባት አንፃራዊ በሆነ መልኩ የሚለካ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በአንድ አገር ውስጥ ሁሉን አቀፍ ውጤታማና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የአስተዳደር ህግ ስርዓት አለ ለማለት ከሚከተሉት ሶስት ዋነኛ መርሆዎች አንጻር እየተመነዘረ መገምገም አለበት፡፡የአስተዳደር ፍትህየአስተዳደር በደል በፍርድ የሚታረምበትና አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚገኝበት የፍርድ ሂደትና መንገድ እንዲሁም ተሞክሮ በአገራችን ውስጥ በግልጽ የሚታወቅ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ፍትሕ የአስተዳደር ህግ ‘ልቡ’ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አስተዳደራዊ በደል አለቅጥ በተንሰራፋበት አገር ውስጥ የአስተዳደር ህግ ትንፋሽ ያጠረው ህላዌነቱ የሚያጠራጥር ህግ ነው፡፡ የከለላው መጠን የአስተዳደር ፍትህ ደረጃ አንጻራዊ መለኪያ ነው፡፡የስራ አስፈፃሚው ተጠያቂነትየዚህ መርህ ዋና አላማ ህግ የማስፈፀም ስልጣን ያለው አካል ለሚፈፅመው ድርጊት እና ለሚወስደው እርምጃ በህዝብ ፊት ተጠርቶ እንዲጠየቅና ማብራሪያ እንዲሰጥ ለማስገደድ ነው፡፡ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣንን የተቀበለ አካል ወይም ባለስልጣን የሚፈፅመው ድርጊት የህዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ውሳኔ ሰጭው ለድርጊቱ ትክክለኛነትና ፖለቲካዊ ተገቢነት ህግ አውጭው ፊት ተጠርቶ በመቅረብ ለማብራሪያ የሚገደድበት ስርዓት ከሌለ በቀር ተጠያቂነት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ በዜጎች መብት ለሚያደርሰው ጉዳት በፍርድ ሂደት ለድርጊቱ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፡፡መልካም አስተዳደርበዚህ መርህ መሰረት አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ላገኙ መሪ ደንቦች መገዛት አለበት፡፡ እነዚህም የፍትሀዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ ሚዛናዊነትና የግልፅነት መርሆዎችን ያጠቃልላሉ፡፡ አስተዳደራዊ ውሳኔ በህጉ መሰረት መወሰዱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የውሳኔው መሰረት ከቅን ልቦና የመነጨ፣ ለባለጉዳዩ ግልፅ በሆነ አሰራርና መንገድ ያልተወሰደ ካልሆነ በስተቀር የመንግስት አስተዳደር ወደ መልካምነት ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ የአስተዳደር ህግ እነዚህን መርሆዎች እንዲዳብሩ ከማድረግ አንፃር አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለሆነም የህጉ የእድገት ደረጃ የአንድ አገር የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ጠቋሚ መለኪያ ነው ማለት እንችላለን፡፡

20 Jun 2020

የአስተዳደር ስልጣን።

አስተዳደራዊ ስልጣን


ደንብና መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ህግ አስፈፃሚ አካላት ህግና ፖሊሲን ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው፡፡ የእነዚህ አካላት ዋነኛ ስልጣንና ተግባር ህግ ማውጣት አሊያም ዳኝነት መስጠት ሳይሆን ማስተዳደር ነው፡፡ አስተዳደራዊ ስልጣን ከህግ ማውጣት እና ዳኝነት መስጠት ውጪ ያሉትን ተግባራት በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ይህን የእለት ተእለት የአስተዳደር ስራ በማከናወን ነው፡፡
በዚህ ስልጣን ስር ከሚወድቁ በርካታ ምሳሌዎችን መካከል ሪፖርት ማቅረብ፣ ፓስፖርት መስጠት፣ ፍቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ፀጥታ ማስከበር፣ ክስ መመስረት፣ እድገትና ሹመት መስጠት፣ ምርመራ፤ ቁጥጥርና ክትትል ማካሄድ የምክር ሀሳብ መስጠት ወዘተ ሁሉም የአስተዳደር መ/ቤቶች አስተዳደራዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም የሚያከናውኗቸው ስራዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ተግባራት የህግ መጣስ መኖርን አለመኖሩን ለማረጋገጥ መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የመረጃ አሰባሰብና ጥንቅር ስርዓት የንግድ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የመረጃ አሰባሰብ ስርዓቱ በአካል ተገኝቶ ቀጥተኛ እና የአካባቢ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ እና የማጣራት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የመርማሪነት ስራ ህጉ ልዩ ስልጣን በሰጣቸው መርማሪዎች የሚከናወን ሲሆን የምርመራ ሂደቱም በህግ ማእቀፍ ውስጥ ይመራል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የፖሊስ የምርመራ ተግባር ነው፡፡ ፖሊስ ወንጀል ሲፈጸም ወይም ተፈጽሟል የሚል መረጃ ከደረሰው አሊያም ተገቢ ጥርጣሬ ካደረበት የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ በአካል በመገኘት ተጨባጭ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ እና ተጠርጣሪውን የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ስልጣናት አሉት፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአስተዳደር መ/ቤቶች የመርማሪነት፣ የቁጥጥርና ክትትል ስልጣን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ለፖሊስ ከተሰጠው ስልጣን ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡
በአስረጂነት በተወሰኑ ህጎች ለተቆጣጠሪዎች የተሰጣቸው መጠነ ሰፊ ስልጣን በማጣቀሻነት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
የአካባቢ ተቆጣጣሪዎች ስልጣንa
ሳያሳውቁ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይዙ በማንኛውም ተገቢ መስሎ በሚታያቸው ጊዜ ወደ ማንኛውም ቦታ ወይም ቅጥር ግቢ መግባት
ማንኛውንም ሰው ብቻውን ወይም በምስክር ፊት የመጠየቅ
ከብክለት ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ወረቀት፣ ማህደር ወይም ሌላ ሰነድ መፈተሽ፣ መገልበጥ ወይም ለይቶ መቅዳት
የማንኛውንም ቁስ ናሙናዎች እንደአስፈላጊነቱ ያለክፍያ መውሰድና በአካባቢ ወይም በህይወት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ አለመሆኑን ለመወሰን መመርመር ወይም ማስመርመር
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 300/1995 ወይም ሌላ ህግ መከበሩን ለማረጋገጥ ሸቀጥን፣ የአመራረት ሂደትን ወይም መገልገያን በፍቶግራፍ ማንሳት፣ መለካት፣ መሳል ወይም መፈተሽ
አዋጁን ወይም አግባብ ያለውን ሌላ ህግ በመተላለፍ ጥፋት ተፈጽሞበታል የተባለ መሳሪያን ወይም ሌላ ነገርን መያዝ
የዱር እንስሳት ቁጥጥር ሠራተኛb
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶች ተደብቀዋል ብሎ ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖር ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ማንኛውም ሰው መሬት፣ ህንጻ፣ ድንኳን፣ ተሸከርካሪ፣ የአየር መንኮራኩር ወይም ጀልባ ውስጥ የመግባትና የመፈተሸ እንዲሁም ሻንጣ ወይም እሽግ የመፈተሸ
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶችን እንዲሁም ጥፋቱ የተፈጸመባቸውን መሳሪያዎች እንዲወረሱ ለማድረግ እንዲቻል በቁጥጥር ስር የማድረግና የሚመለከተው አካል ባወጣው የመመዝገቢያ ቅፅ መሰረት ተገቢውን ደረሰኝ ሰጥቶ የመረከብ
የዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ማፅደቂያ አዋጅ ቁ. 541/1999 አንቀጽ 16 ድንጋጌዎች በመተላለፍ ጥፋት ሲፈጽም የተገኘን ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዞ ለሚመለከተው ህግ አስከባሪ አካል ማስረከብ
የደን ውጤት ተቆጣጣሪc
የደን ውጤቶችን የጫነ ወይም ለመጫኑ የሚጠረጠርን ማናቸውንም ማጓጓዣ በደን መግቢያና መውጫዎች እንደአስፈላጊነቱ በሚመረጡ የሀገር ውስጥ እና የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ አስቁሞ መፈተሸ
የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 542/1999 በመተላለፍ ተዘጋጅተው ሲጓጓዙ ወይም ተከማችተው የተገኙ የደን ውጤቶችን ከድርጊቱ ተጠያቂዎች ጋር የመያዝ
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርd
የቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁ. 602/2000 ለማስፈጸም የሚወጡ ደንብና መመሪያዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ቡና ሊገኝበት ይችላል ተብሎ የሚገመትን መጋዘን፣ መኖሪያ ቤት፣ የመንግስት ድርጅት፣ ማጓጓዣ ወይም ማናቸውም ሌላ ቦታ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የመፈተሽ፣ህገ ወጥ ቡና ሲያዝ የማሸግ፣ ምርቱን የማገድ፣ የመያዝ፣ ህገ ወጥነታቸው የማያጠራጥር ሲሆን የቡናው ባለቤት ለፍርድ ቤት ቅሬታ የማቅረብ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የመውረስና የመሸጥ


የፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን


የፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን
የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 79/1/ አጣሪ ዳኝነትን እንደሚጨምር አይጠቁምም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ የፌደራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ከክልሎች ውክልና ጋር በተያያዘ በስም ቢጠቀሱም የስልጣናቸው ምንጭ ህገ መንግስቱ ሳይሆን የተወካዮች ም/ቤት የሚያወጣው ህግ እንደሆነ በአንቀጽ 78/2/ ተመልክቷል፡፡ በአንጻሩ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ የሚመነጨው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን ያላቸው አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ህጋዊነት ለማጣራት ያስችለዋል፡፡ ይህ ስልጣን ከሁሉም የፌደራልና የክልል ፌደራል ፍርድ ቤቶች (የክልል የሰበር ችሎቶችን ሳይጨምር)በዓይነቱ የተለየና ብቸኛ ነው፡፡
የፌደራል ፍ/ቤቶች
መደበኛ ፍርድ ቤቶች የስልጣንን ህጋዊነት በሁለት ዓይነት መንገድ ይቆጣጠራሉ፤ በመደበኛ የፍትሐብሔር ክስ እና በአስተዳደራዊ ይግባኝ፡፡ መንግስት ተከራካሪ በሚሆንባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በርካታ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በተለይም ከውል ውጪ ኃላፊነት፣ ከንብረት ህግ እና በከፊል ከውል ህግ የሚመዘዙ በርካታ የህጋዊነት ጥያቄዎች በተዘዋዋሪም ቢሆን አስተዳደሩ ለህግ እንዲገዛ ያስገዱዱታል፡፡ ፍ/ቤቶች ጠቅላላ ከሆነው መደበኛ ስልጣናቸው በተጨማሪ የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት በይግባኝ እንዲያጣሩ በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፍሬ ነገርና በህግ ጉዳይ ላይ የሚፈቀድ ይግባኝ ከዜጋው መብት አንጻር ከአጣሪ ዳኝነት የበለጠ ጠቀሜታ አለው፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ነገሩን እንደ አዲስ የማየትና ክርክሩ ከተቋጨ በኋላ በራሱ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የተለጠጠ ስልጣን ያጎናጽፈዋል፡፡ አጣሪ ዳኝነት ግን ህጋዊነትን ከማጣራት አይዘልም፡፡ የአስተዳደራዊ ውሳኔን በመቃወም ለፌደራል ፍ/ቤቶች ይግባኝ የማቅረብ መብት ከሚፈቅዱ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት
መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ መረጃ ተጠይቆ መረጃውን የያዘው አካል በመከልከሉ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ ከቀረበ በኋላ እንባ ጠባቂው በሚሰጠው ውሳኔ ላይa
የአካባቢ ተቆጣጣሪዎች በሚሰጡት ውሳኔ እንዲሁም እንዲሁም በአካባቢ ላይ የደረሰ ጉዳትን አስመልክቶ ለአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አቤቱታ ቀርቦ ሚኒስቴሩ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ b
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት
ከጥራት ጋር በተያያዘ ቡና የተያዘበት ወይም መጋዘኑ የታሸገበት ሰው ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ወይ አግባብ ላለው የክልል መንግስት አካል ቅሬታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣc
የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚነሳ ክርክርd
ለሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ አቅራቢነት፣ ላኪነት ወይም አገልግሎት ሰጪነት የብቃት ማረጋገጫ ማመልከቻ ውድቅ ከተደረገ የህግ አተረጓጎምን በተመለከተ ወይም ተፈቅዶለት በዚህ ንግድ የተሰማራ ሰው ከጥራት ጋር በተያያዘ ሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ ተይዞበት ለሚኒስትሩ ወይም አግባብ ላለው የክልል መንግስት አቤቱታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣe
የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት የቀረበ ማመልከቻ ተቀባይነት እንዲያጣ ወይም ፈቃድ የተሰጠው ጠበቃ በዲሲፕሊን ጥፋት ምክንያት ቅጣት በመጣል በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የተወሰደ እርምጃ (በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ)f
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበር ምዝገባ ባለመፍቀድ እንዲሁም ለስራ ውል መታገድ በቂ ምክንያት አለመኖሩን በመግለጽ በሚሰጠው ውሳኔ እና የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወምg
የዕፅዋት አዳቃዮች መብት መስጠትን፣ መከልከልን፣ መሰረዝን ወይም መገደብን በተመለከተ በሚሰጥ ውሳኔ ላይh
የምርት ገበያ ባለስልጣን በሚሰጣቸው በአዋጁ በተመለከቱ ውሳኔዎችi
የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ውድቅ በማድረግ ወይም በመሰረዝ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚሰጥ ውሳኔj
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔ እንዲሁም ባንኩ የሾመው ሞግዚት በሚያስተላልፈው ውሳኔk
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔl
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን በቀጥታ ከህገ መንግስቱ ይመነጫል፡፡ ሆኖም የስልጣኑን ወሰን የሚያሰምረው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ የአማርኛውና እንግሊዝኛው ቅጂ ግልጽ መፋለስ ይታይበታል፡፡ በአማርኛው ንባብ የሰበር ችሎት መሰረታዊ ‘የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ’ የማረም ስልጣን ይኖረዋል፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ) የእንግሊዝኛው ቅጂ ደግሞ Over any final court decision የሚል አገላላጽ በመጠቀም ስልጣኑን ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይገድበዋል፡፡
የድንጋጌውን ይዘት ዝርዝር የሚወስነው ህግ ከእንግሊዝኛው ቅጂ ጋር ይስማማል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1988 አንቀጽ 10 የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን የሚያገኝባቸው ሶስት ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም፤
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
በሶስቱም ጉዳዮች በውሳኔ ሰጭነት የተጠቀሱት ተቋማት መደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ረ ህገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ ሀ የእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ court የሚለው ቃል እንዲሁ ይህንኑ ሀሳብ ያንጸባርቃል፡፡ ሆኖም የአማርኛው ንባብ ውሳኔ ሰጭውን በዝምታ አልፎታል፡፡ ላይ ላዩን ሲታይ ዝምታው ለህገ መንግስታዊ ትርጉም በር የከፈተ አይመስልም፡፡ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ የሚለው አገላለጽ ፍርድ ቤትን ታሳቢ አድርጓል ቢባል ብዙዎችን ያስማማል፡፡
ሆኖም ችግሩ ከቋንቋ አጠቃቀም ያልዘለለ የሚመስለው የአንቀጽ 80/3/ ሀ ድንጋጌ በተግባር ህገ መንግስታዊ ጥያቄ አስነስቶ የሰበር ችሎትን የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አስፍቶታል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 43511m ከአዋጅ ውጪ የተወረሱ ንብረቶችን በተመለከተ ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጠው የፕራይቬይታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ በቀጥታ በሰበር እንዲታይ አቤቱታ ቢቀርብም አጣሪ ችሎቱ ጉዳዩ አስተዳደራዊ መሆኑን በመጠቆም ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሆኖም በመዝገቡ ላይ አመልካች ሆነው የቀረቡት አቤቱታ አቅራቢዎች የውሳኔውን ህገ መንግስታዊነት በመሞገት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ አቤቱታ አስገቡ፡፡ አጣሪውም ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ የመጨረሻ አማራጫቸውን በመጠቀም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አመለከቱ፡፡ ም/ቤቱ የችሎቱን ስልጣን በማረጋገጥ መዝገቡን ወደ ሰበር ችሎት መለሰው፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቦርዱን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው በማረጋገጥ የተሰጠው ይህ የም/ቤቱ ውሳኔ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ በሚል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ ላይ የተቀመጠውን አገላለጽ ከእንግሊዝኛ ቅጂ ፍጹም የተለየ ይዘትና መልዕክት ሰጥቶታል፡፡ በውጤቱም ከፍርድ ቤት ውጭ ያሉ ከፊል የዳኝነት አካላት ላይ የሰበር ችሎት የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል፡፡
የም/ቤቱ ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ስር ነቀልና መሰረታዊ ነው፡፡ የስር ፍ/ቤቶችን የህግ ስህተት በማረም ብቻ ተወስኖ የነበረው የሰበር ችሎት በም/ቤቱ ‘በተጨመረለት’ ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጣቸው የአስተዳደር አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ጭምር የማረም የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ችሎቱም ዳኝነታዊ የአስተዳደር ውሳኔዎችን ማረም ህገ መንግስታዊ ሚናው እንደሆነ በሌሎች ሁለት መዝገቦች በሰጣቸው ውሳኔዎች በተግባር አረጋግጧል፡፡
በሰ/መ/ቁ. 92546n የድሮው ፍትሕ ሚኒስቴር የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የዲሲፕሊን ውሳኔ በቀጥታ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ተሸሯል፡፡ አቤቱታ አቅራቢው በሚኒስትሩ የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደው በዓቃቤ ህግ ላይ ሲሆን ጉዳዩ በሰበር ችሎት ከመስተናገዱ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት አልታየም፡፡ በመዝገቡ ላይ የችሎቱ የዳኝነት ስልጣን አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ባይወጣም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ እና አዋጅ ቁ. 25/88 አንቀጽ 10 ተጠቅሶ የቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ መቀበሉ ሲታይ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣኑ ጠንካራ መሰረት እየያዘ እንደመጣ አስረጂ ነው፡፡ በሰ/መ/ቁ. 61221 ቅጽ 14o የተያዘው አቋም ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ በዚህ መዝገብ በሰፈረው የህግ ትርጉም በፍርድ ቤት እንዳይታዩ በመጨረሻ ማሰሪያ ድንጋጌ (finality clause) ገደብ የተደረገባቸው ውሳኔዎች ሳይቀር በችሎቱ የአጣሪ ዳኝነት ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ ጉዳዩ የታየው አዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 ከመውጣታቸው በፊት ሲሆን ቀድሞ በነበሩት የጡረታ ህጎች የማህበራዊ ዋስትና ጉባኤ ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ በይግባኝ ሆነ በቀጥታ ክስ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሊታይ አይችልም፡፡
በሰ/መ/ቁ. 61221 የሰበር አቤቱታ የቀረበው የጉባዔውን የመጨረሻ ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ ሆኖም በችሎቱ የዳኝነት ስልጣን ላይ በተጠሪ በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ የስልጣን ምንጭ አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ይህንን በማስመልከት ህገ መንግስቱን እና አዋጅ ቁ. 25/88 በማጣቀስ የሚከተለው የህግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡
ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ስራ ላይ በነበረው ሕግ አግባብ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ከተባለ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተመለከተው አግባብ ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ ከማቅረብ የሚከለክል ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡
የከተማ ፍ/ቤቶች
በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ የተቋቋሙት የከተማ ፍርድ ቤቶች በውስን ጉዳዮች ላይ ቢሆንም የማይናቅ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አላቸው፡፡ ስልጣናቸውን በሚወስኑት ህጎች ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትp በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአጣሪ ዳኝነት የሚታዩ ናቸው፡፡
የከተማውን መሪ ፕላን አፈጻጸም የሚመለከት የይዞታ ባለመብትነት፣ የፈቃድ አሰጣጥ ወይም የቦታ አጠቃቀምን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች
ከከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች
በየከተሞቹ ቻርተር ላይ በተመለከቱት የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ክሶች
የከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በከተማው አስተዳደር ባለቤትነት ስር ያሉ ተቋማት የሚገቧቸውን አስተዳደራዊ ውሎች በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች
በከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በስሩ ባሉ ተቋማት መካከል የሚነሱ ክርክሮች
የከተማው አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ቤቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች
በህግ ከተሰጣቸው የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን በተጨማሪ በከፊል ጉዳዮች አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በይግባኝ ያያሉ፡፡ ለምሳሌ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ በሚሰጠው ውሳኔq የመጀመሪያና የይግባኝ ስልጣን አላቸው፡፡
የከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ክልል በህጉ ላይ በወጉ አልተሰመረም፡፡ ህግ አውጭው ‘በተመለከተ…በተያያዘ…’ በሚል የተጠቀመው አገላለጽ መብት ጠያቂውን ሆነ ፍርድ ቤቶችን ያደናግራል፡፡ የዳኝነት ስልጣን ሊወሰን የሚገባው በክስ ምክንያት፣ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው መፍትሄ ወይም በተከራካሪዎች ማንነት ነው፡፡ ለምሳሌ የይዞታ ባለመብትነትን በተመለከተ እንዲሁም ከአስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች እንደ ሁኔታው በፌደራል ወይም በከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር ይወድቃሉ፡፡ ይዞታን የሚመለከት ክስ በሁከት ይወገድልኝ ወይም በመፋለም ክስ አሊያም ደግሞ በይዞታ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ በመጠየቅ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከግንባታ ፈቃድ ወይም ስም ከማዛወር አስተዳደራዊ ግዴታ ጋር በተያያዘም ይዞታን የሚመለከት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ከዚህ አንጻር በደፈናው ‘በተመለከተ…’ በሚል የተደለደለው የዳኝነት ስልጣን የመደበኛ እና የከተማ ፍ/ቤቶችን ድርሻ በአግባቡ አይለይም፡፡
ህጉ ግልጽነት ቢጎድለውም ከሰበር ችሎት አካሄድ እና የህግ አውጭው ሀሳብ በመነሳት የከተማ ፍ/ቤቶች መደበኛ የፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣን እንዳልተሰጣቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ህግ አውጭው እነዚህን ፍ/ቤቶች ሲያቋቁም ከተወሰኑት በግልፅ ከተነገሩት በስተቀር መደበኛውን የፍትሐብሔር ዳኝነት አላስተላለፈላቸውም፡፡ የሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች ያንጸባረቀው አቋም ከዚህ ሀሳብ ጋር ይስማማል፡፡ ይህ ከተባለ በኋላ ግን ከላይ በቀረበው ዝርዝር ውስጥ ህግ አውጭው የወሰነው የዳኝነት ስልጣን ምን መልክ እንዳለው መለየት ያስፈልጋል፡፡
ራሱን የቻለ የአስተዳደር ህግ ስርዓት ባላቸው አገራት በፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮች ሶስት ዓይነት ናቸው፤ የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እና የአስተዳደር፡፡ በፈረንሳይ የአስተዳደር ክርክሮች ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ተለይተው በተቋቋሙ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች አማካይነት ይዳኛሉ፡፡ በጀርመን ራሱን ችሎ በተለይ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ይታያሉ፡፡ ከስልጣን ክፍፍል አንጻር መደባቸው ሲታይ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች በፈረንሳይ በስራ አስፈፃሚው ስር የሚገኙ ሲሆን በጀርመን ግን በዳኝነት አካሉ የታቀፉ ናቸው፡፡ በእንግሊዝ የፍትሐብሔር ክርክሮችን የሚያስተናግዱት መደበኛ ፍ/ቤቶች የአስተዳደር ክርክሮችንም ደርበው ይዳኛሉ፡፡ በእርግጥ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች የሚቀርቡት ለከፍተኛው ፍ/ቤት ቢሆንም ፍ/ቤቱ ራሱን የቻለ የተለየ መዋቅር የለውም፡፡ በሶስቱም አገራት በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚካሄዱ ክርክሮች የሚዳኙበት መንገድ ቢለያያም አንድ ነገር ያመሳስላቸዋል፡፡ ይኸውም የዳኝነት ስልጣናቸው ዓይነት አጣሪነት (supervisory) ነው፡፡ የዚህ ስልጣን ወሰን የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ያለፉ የፍትሐብሔር ክርክሮችን መደበኛ ፍ/ቤቶች ይረከባሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የአስተዳደር ተቋም ከህግ የመነጨ ስልጣኑን በመጠቀም እርምጃ ሲወስድ ክርክሩ በአጣሪነት ዳኝነት ስር ይወድቃል፡፡ እንደማንኛውም ግለሰብ በሚፈጽማቸው የግል ተግባራት ሲከሰስ (ለምሳሌ የተቋሙ መኪና በአካል ወይም ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት ካሳ ሲጠየቅ) ደግሞ መደበኛ ፍ/ቤቶች በፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣናቸው ያዩታል፡፡
በከተማ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር ከተዘረዘሩት መካከል የይዞታ ባለመብትነትን በምሳሌነት ብንወስድ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ጉዳዩ የሚታይበት ፍ/ቤት የሚለየው በክሱ ይዘት ነው፡፡ ከፍትሐብሔር ውጭ በአስተዳደሩ ላይ ሊቀርብ የሚችለው ክስ ህጋዊነት የሚጣራበት ክስ ነው፡፡ ይህም የሚያደርሰን መደምደሚያ የከተማ ፍርድ ቤቶች በህግ የተወሰነላቸው የዳኝነት ስልጣን ዓይነት የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስልጣን እንደሆነ ነው፡፡

Popular posts

Recent Posts

LikeBtn

Type

አስተማሪ የሆኑት የችሎት ድራማ ቪዲዮዎች

DOCUMENT & FILES

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd