13 Aug 2020

መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች

መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች
መልካም አስተዳደር ምንም እንኳን በጥቅሉ ሲታይ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ እንዲሁም የአመራር እና የአሰራር ሂደቶችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ እንደምታዎች ያሉት ቢሆንም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሲታይ ግን ከአስተዳደር ፍትህ ጋር አቻ ሆኖ ሊገለጽ ይችላል፡፡ መልካም አስተዳደር ዋና ግቡ ዜጐች ብቁና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል መቅረፍ እና አስተዳደራዊ ፍትህን እውን ማድረግ እንደመሆኑ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት ያስቸግራል፡፡ መልካም አስተዳደር ሆነ የአስተዳደር ህግ በራሳቸው አቅጣጫና ሂደት ተጉዘው የግባቸው መድረሻ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ ስለሆነም በይዘቱ ሰፊ በሆነ የመልካም አስተዳደር እሳቤ ውስጥ የአስተዳደር ህግ አንድ ቁስ ሆኖ በማገልገል የተቆራኘና የተዛመደ ተግባራዊ እገዛ ያደርጋል፡፡
በመልካም አስተዳደርና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለውን ተዛምዶ በቅጡ ለመቃኘት ህግ በአስተዳደሩ አካሄድ (Administrative behavior) ወይም በስራ አስፈፃሚው እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በተግባር የታገዘ ጥልቅ ጥናት ምላሽ መስጠት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ሚናዎችና ተግባራት ቢያንስ እንደጠቅላላ ሀሳብ በመውሰድ የአስተዳደር ህግ እንደ አንድ የህግ ዘርፍ የራሱ አዎንታዊ ፋይዳ እንዳለው መደምደም እንችላለን፡፡ ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ መልካም እንዲሆን የአስተዳደር ህግ ስልጣን ከመቆጣጠር ባሻገር እንዴት ተቃኝቶ መቀረጽ አለበት? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አጥኚዎች ሆነ ምሁራን የውይይት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የጥናት መሰረት መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር እና የአስተዳደር ህግን ተዛምዶ ለማየት የሁለቱም መድረሻ ከሆነው የአስተዳደር ፍትህ ትርጓሜ እንነሳለን፡፡ የአስተዳደር ፍትህ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው የመንግስት አካላት ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር ፍትሃዊ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ መርህ ነው፡፡ የመንግስት አስተዳደር ፍትሃዊ ሲሆን መልካም ይሆናል፡፡
የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ቁልፍ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ ይኸውም፡-
አንደኛ፦ የመንግስት ባለ ስልጣናት ወይም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት አነስተኛ ለሆኑ የስነ-ስርዓት ደንቦች እና ተቀባይነት ላላቸው መርሆዎች መገዛት አለባቸው፡፡ ከአነስተኛ የስነ-ስርዓት ደንቦች በተጨማሪ የመንግስት አስተዳደር ተቀባይነት ባላቸው የህግ፣ የአስተዳደርና የፍትህ መርሆዎች መመራት አለበት፡፡
ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የህጋዊነት መርህ (ህጋዊ ስልጣን ሳይኖር አንዳችም እርምጃ አለመውሰድ፤ በህጉ መሰረት መወሰን)
የሚዛናዊት መርህ (የአስተዳደር አካላት ውሳኔ ወይም እርምጃ እንደየሁኔታው ብዙ ነገሮች ግምት ያስገባ እንጂ ፍርደገምድል መሆን የለበትም፡፡)
የተመጣጣኝነት መርህ (የሚወሰደው እርምጃ ተፈጸመ ከተባለው ጥፋት አንፃር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡)
የእኩልነት መርህ (ተመሳሳይ በሆኑ ሁኔታዎች ወይም ጉዳዮች አስተዳደሩ የተለያየ ውሳኔ ላይ መድረስ የለበትም፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተመሳሳይ መንገድ መወሰን አለባቸው፡፡)
ለውሳኔ በቂ ምክንያት መስጠት (አስተዳደራዊ ውሳኔ የተወሰደበት ምክንያት በግልጽ መጠቀስ አለበት፡፡ ውሳኔውም ፈጽሞ የማያሳምንና ኢ- ምክንያታዊ መሆን የለበትም፡፡)
ሁለተኛ፦ ከላይ የተመለከቱትን ደንቦችና መርሆዎች በመጻረር በህግ ከተወሰነው ስልጣን በላይ እርምጃ ከተወሰደ መብታቸው የተጐዳ ዜጐች አቤቱታ አቅርበው ፍትህ (መፍትሄ) የሚያገኙበት መንገድ መኖር አለበት፡፡ በአስተዳደር አካላት መብታቸው የተጣሰ ሰዎች ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት አቤቱታ አቅርበው ቀልጣፋ መፍትሔ የሚያገኙበት አሰራር ወይም መንገድ ከሌለ የአስተዳደር ፍትህ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አካልን ነፃ የማውጣት መብት በህገ-ወጥ መንገድ ከ48 ሰዓት በላይ የታሰረ ሰው ራሱ በቀጥታ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን በቀላሉ አቤቱታ አቅርቦ ነፃ የሚለቀቅበት ፈጣን ስነ-ስርዓት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በህገ ወጥ መንገድ ንብረቱን በአስተዳደደሩ የተቀማ ወይም ፈቃዱ አለአግባብ የተሰረዘበት ሰው ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት መፍትሔ የሚያገኝበት የህግ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ነው የአስተዳደር ህግ መኖር ለአስተዳደራዊ ፍትህ ሆነ ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሳሪያ ነው የሚባለው፡፡ የአቤቱታው ስርዓት እንዳለ ሆኖ የአስተዳደራዊ ፍትህ የሚገኝበት ተቋም ገለልተኛ፣ ተደራሽ እና ነፃ ሆኖ ቀልጣፋና ውጤታማ ግልጋሎት መስጠት መቻሉ የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ዋናውና መሰረታዊው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

10 Aug 2020

ተጠያቂነት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና


ተጠያቂነት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና
የተጠያቂነት መርህ ይዘትና ገፅታው


የተጠያቂነት መርህ ውሳኔ ሰጪዎች በአንድ ጠያቂ አካል ፊት ቀርበው የድርጊታቸውን ህጋዊነት፣ ፍትሀዊነት እና ትክክለኛነት እንዲያስረዱ የሚጠየቁበት መንገድ ነው፡፡ ይህም በህግ ወይም በፓለቲካዊ የስልጣን ቁጥጥር ስልቶች ይተገበራል፡፡ ፖለቲካዊ ቁጥጥር በህግ አውጭው አማካይነት የሚደረግ ቁጥጥር ሲሆን ትኩረቱ የመንግስት ውሳኔዎች፣ ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች ፖለቲካዊ ተገቢነት መመርመርና በቅርበት መከታተል ነው፡፡a በዚህም መሰረት የመንግስት ባለስልጣናት በህግ አውጭው ፊት ቀርበው ውሳኔያቸው ወይም ድርጊታቸው ከፖሊሲ አቅጣጫዎች አንጻር ትክክለኛ እና አስፈላጊ መሆኑን ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ህጋዊ ቁጥጥር በአንጻሩ በመደበኛ ፍ/ቤቶች እና በተወሰነ መልኩ በአስተዳደር ፍ/ቤቶች የሚደረግ የስልጣን ቁጥጥርን ይመለከታል፡፡ ህጋዊ ቁጥጥር የስልጣንን ህጋዊነትና ፍትሀዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ የውሳኔውን ይዘት ማለትም ትክክለኛነት ወይም ተገቢነት አስመልክቶ ፍተሻ የሚደረግበት የቁጥጥር ስልት አይደለም፡፡ ፍ/ቤቶቸ የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ የሚወስኑ ከሆነ በስራ አስፈፃሚ የስልጣን ክልል ውስጥ በመግባት የስልጣን ክፍፍል መርህን በመጣስ ለስልጣናቸው ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያጣሉ፡፡
‘ተጠያቂነት’ የሚለው ቃል የሶስት ንዑስ ሀሳቦች ድምር ውጤት ነው፡፡ እነዚህም ጠያቂ፣ ተጠያቂ እና ጥያቄ ብሎ መከፋፈል ይቻላል፡፡ በአንድ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ተጠያቂነት አለ ለማለት፤
ጠያቂው አካል የቱ ነው?
ተጠያቂው አካል ማን ነው?
መጠየቅ ምንድነው? የመጠየቂያ መንገዱስ?
ብለን ራሳችንን መጠየቅና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ማግኘት ይገባናል፡፡ ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመሻት የምናደርገው ትንተና በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለውን ህገ መንግስታዊ ስርዓት መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡
የዲሞክራሲ አንደኛው ገጽታ መንግስት ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆንበት ስርዓት ነው፡፡ ሆኖም በተግባር ደረጃ ሙሉ በሙሉ ቀጥተኛ ህዝባዊ ተጠያቂነትን ማሳካት የማይቻል በመሆኑ በምርጫ የህዝብ ውክልና የተሰጣቸው እንደራሴዎች ስለህዝቡ ሆነው በመንግስት ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ በአጭር አነጋገር ጠያቂው አካል በተለምዶ ህግ አውጪ ወይም ፓርላማ ተብሎ የሚጠራው ተቋም እንደሆነ እናያለን፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት መንግስትን የመቆጣጠር እና ተጠያቂነቱን የማረጋገጥ ስልጣንና ግዴታ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ስለመሆኑ በማያሻማ አነጋገር አስቀምጦታል፡፡
ጠያቂው ከታወቀ በቀጣይነት የሚነሳው ጥያቄ ተጠያቂ የሚሆነው አካል ማነው? የሚለው ይሆናል፡፡ ተጠያቂነት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ከስራ አስፈፃሚው ባሻገር የፓርላማውንና የፍ/ቤቶችን ተጠያቂነት ጭምር የሚወክል ቢሆንም የእነዚህ ተጠያቂነት ከአስተዳደር ህግ የጥናት ወሰን ውጪ በመሆኑ ትኩረታችንን በመንግስት ተጠያቂነት ማለትም በስራ አስፈፃሚው ተጠያቂነት ላይ ብቻ እንገድባለን፡፡
በአገራችን በፌደራል መንግስት ደረጃ የስራ አስፈፃሚነት ስልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ም/ቤት እንደመሆኑ የመንግስት ተጠያቂነት የሚኒስትሮችን የነጠላ እና የወል ተጠያቂነት ያመለክታል፡፡ በህዝብ ተመርጠው የአስፈፃሚነት ስልጣን የተሰጣቸው ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግስት መ/ቤት ባለስልጣናት ለሚያስፈጽሙት ህግና ፖሊሲ የነጠላ ተጠያቂነት እንዲሁም በሚኒስትሮች ም/ቤት አባልነታቸው (የሚኒስትሮች ም/ቤት አባል ከሆኑ) የጋራ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሚኒስትር በስሩ ላሉት የአስተዳደር መ/ቤቶች የስራ አፈፃፀም እንዲሁም ራሱ ለሚመራው ሚኒስትር መ/ቤት እንቅስቃሴ በግል ቀጥተኛ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር ሚኒስትሩ በሚኒስትሮች ም/ቤት አባልነቱ ም/ቤቱ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች የጋራ ተጠያቂነት አለበት፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 72/2/ ግልፅ ሆኖ እንደተደነገገው፤
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግስት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በመጨረሻም የመጠየቅ ይዘትና ትርጓሜ እንዲሁም የተጠያቂነት መንገዱና ስልቱ ሊዳሰስ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ ለመሆኑ መጠየቅ ማለት ምን ማለት ነው?
መጠየቅ የሚለው ቃል ተጠያቂነትን (Responsibility) እና ኃላፊነትን (Accountability) ያመለክታል፡፡ ተጠያቂ (Respond-ability) መሆን ማለት መግለጫ ወይም ማብራሪያ የመስጠት እንዲሁም ትክክለኛነቱን ማስረዳት ማለት ነው፡፡ ይህም በዋነኛነት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት በአካል ቀርቦ ከምክር ቤቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት፣ ለምክር ቤቱ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ የመስጠት ግዴታን ይጨምራል፡፡
ተጠያቂነት መግለጫ በመስጠት ብቻ አያበቃም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተጠያቂው ለቀረቡለት ጥያቄዎች አሳማኝ እና በቂ ምላሽ ሳይሰጥ ሊቀር ይችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ለም/ቤቱ የተሳሳተ መረጃ ሊያቀርብ ወይም የተፈለገውን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆንበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች ምክንያት የተጠያቂው ስህተት እና ድክመት በግልጽ ከታየ ተጠያቂነት በማዕቀብ (sanction) መታገዝ አለበት፡፡
ስለሆነም ሁለተኛው የተጠያቂነት ገጽታ ኃላፊነት የመውሰድ ግዴታ ነው፡፡ ኃላፊነት ሲወሰድ ህገ-ወጥ እርምጃ ወይም ተግባር ከተፈጸመ፣ ህግና ፖሊሲውን የማስፈጸም ድክመትና ቸልተኝነት ከታየ የሚመለከተው ሚኒስትር ወይም ባለስልጣን ስህተቱና ድክመቱ የሚያስከትለውን ውጤት መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ኃላፊነትን የመቀበል ውጤት በገዛ ፈቃድ ስልጣን መልቀቅ ወይም አለፈቃድ ከስልጣን የመወገድ እርምጃ ያስከትላል፡፡
በገዛ ፈቃድ ስልጣን መልቀቅ በብዙ ዲሞክራሲያዊ አገራት የተለመደ ቢሆንም መልካም አስተዳደር ባልሰፈነበት አገር በመንበረ ስልጣን ላይ መጣበቅና ሙጭጭ ማለት በተግባር ይከሰታል፡፡ እዚህ ላይ በገዛ ፈቃዱ ስልጣን መልቀቅ ያለበት ሚኒስትር ኃላፊነት ሳይወስድ ቢቀር ‘አላየሁም! አልሰማሁም!’ ቢል የሚከተለው ማዕቀብ ምንድ ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሚኒስትር ግዙፍ ስህተትና ጥፋት መስራቱ ተረጋግጦ እያለ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ካልለቀቀ የተወካዮች ምክር ቤት ምን ማድረግ ይችላል? የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 55/17/ የም/ቤቱን የመጠየቅና የመመርመር ስልጣን በግልጽ ዕውቅና በመስጠት መውሰድ የሚችላቸውን እርምጃዎች በዝምታ አልፎታል፡፡ ከዚህ አንጻር ግዙፍ ግድፈት የታየበትን ሚኒስቴር ወይም ባለስልጣን ከስልጣኑ ለመሻር የሚችልበት ህገ መንግስታዊ ብቃት የለውም፡፡

Popular posts

Recent Posts

LikeBtn

Type

አስተማሪ የሆኑት የችሎት ድራማ ቪዲዮዎች

DOCUMENT & FILES

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd