በዚህ መጽሐፍ ‘አጣሪ ዳኝነት’ የሚለው የአማርኛ ቃል ለእንግሊዝኛው Judicial Review አቻ ትርጉም ሆኖ የቀረበ ሲሆን የአስተዳደር ስነ- ስርዓት አዋጁ ደግሞ ‘የክለሳ ስርዓት’ የሚለውን አገላለጽ መጠቀም መርጧል። ወደ ቋንቋ ክርክር መግባት ሳያስፈልግ ከዚህ በፊት ቃሉ በፍርድ ቤት ውሳኔዎች ላይ ሆነ በህግ ስነ-ጽሑፍ በአማርኛ የሚታወቅበት መደበኛ ስያሜ ያልነበረው እንደመሆኑ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ነው። ሆኖም አንባቢ እንዳይደናገር ሁለቱም ገላጭ መሆናቸው የሚያስማማ ነጥብ ነው። ስለሆነም በዚህ መጽሐፍ ‘አጣሪ ዳኝነት’ እና በአዋጁ ‘የክለሳ ስርዓት’ መካከል የይዘት ልዩነት ባለመኖሩ ሁለቱም በዚህ መጽሐፍ ላይ በአማራጭ ጥቅም ላይ ውለዋል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ መጽሐፍ ‘አጣሪ ዳኝነት’ የሚለው ቃል ለምን እንደተመረጠ ጥቂት ነጥቦችን ማውሳት ያስፈልጋል። Judicial Review ፍርድ ቤቶች ካላቸው መደበኛው የፍትሐብሔር እና የወንጀል ዳኝነት ስልጣን የተለየ የዳኝነት ስልጣን ነው። አንድ ፍርድ ቤት አንድን ጉዳይ በ Judicial Review ስርዓት ሲያይ የስልጣኑ ዓይነት አጣሪ ማለትም Supervisory Jurisdiction ነው። የስልጣኑ ወሰን ህጋዊነትን ከማጣራት አያልፍም። በአንጻሩ ‘የፍርድ ክለሳ’ ጉዳዩን በፍሬ ነገር እና ህግ ጉዳይ እንደገና የመከለስ እንደምታ አለው። በዚህ የተነሳ በጸሐፊው አረዳድ ‘አጣሪ ዳኝነት’ ተመራጭ ሆኖ ተገኝቷል።
ምንነትና ህገ-መንግስታዊ ፋይዳው
የአጣሪ ዳኝነት (Judicial Review) ትርጓሜ ከህገ መንግስት ወይም ከአስተዳደር ህግ አንጻር ሊቃኝ ይችላል። በህገ መንግስታዊነት ማዕቀፍ አጣሪ ዳኝነት ማለት በህግ አውጭው የሚወጡ ህጐች ህገ መንግስታዊ ባለመሆናቸው በመደበኛ ፍ/ቤት፣ በህገ መንግስታዊ ፍ/ቤት ወይም በሌላ ራሱን የቻለ ተቋም አማካይነት የሚሻሩበት ስርዓት ነው።a በአስተዳደር ህግ ውስጥ አጣሪ ዳኝነት ማለት በህግ አስፈፃሚው ወይም በአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወሰዱ ውሳኔዎች፣ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እና በውክልና የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ህጋዊነት በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚጣራበት ስርዓት ነው።b ምንም እንኳን በህገ መንግስታዊነት እና በህጋዊነት መካከል ጥርት ያለ መለያ መስመር ማበጀት አዳጋች ቢሆንም የዚህ መጽሐፍ በተለይም የዚህ ምዕራፍ ወሰን ህገ መንግስታዊ አጣሪ ዳኝነትን አያካትትም።
የአጣሪ ዳኝነትን ፅንሰ ሀሳብ በሚገባ ለመረዳት እንዲያስችለን በመስኩ ምሁራን የተሰጡ ሁለት ትርጓሜዎችን እንጠቅሳለን። በእንግሊዝ አጣሪ ዳኝነት ማለት በህግ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ስልጣናቸውን በመገልገል የሚፈጽሙት ድርጊት ወይም አልድርጊት (inaction) በከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚጣራበት ስርዓት ነው።
Judicial review can be defined as the procedure through which the High Court supervises the public law actions and inactions of public authorities and other bodies that are exercising statutory powers, performing public duties, and/or taking decisions on matters of public interest.c
በሌላ አነጋገር አጣሪ ዳኝነት ማለት የአስተዳደር መ/ቤቶች እና ሌሎች የማስተዳደር ስልጣን የተሰጣቸው አካላት በህግ አውጪነት (rule-making) እና ዳኝነት ሰጪነት (adjudicatory power) ስልጣናቸው የሚያወጧቸው ደንብና መመሪያዎች ወይም የሚሰጧቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ህጋዊነት በመደበኛ ፍ/ቤቶች የሚታረምበት ስነ-ስርዓት ነው። በማጣራቱ ሂደት የፍ/ቤቶች ሚና ህጋዊነትን ከማረጋገጥ አያልፍም። የሚከተለው ትርጓሜ ህጋዊነት የስርዓቱ አንኳር ባህርይ እንደሆነ ያሳየናል።
Judicial review is essentially a procedure whereby the courts are able to determine the lawfulness of the exercise of executive power. It is concerned with the legality of the decision-making process as opposed to the merits of the actual decision.d
መደበኛ ፍ/ቤቶች አንድን አስተዳደራዊ ውሳኔ በአጣሪ ዳኝነት በሚያዩበት ወቅት የውሳኔውን ህጋዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ትክክለኛነቱን የማየት ስልጣን የላቸውም። የውሳኔው ይዘት በጉዳዩ ላይ ልዩ እውቀት ላላቸው የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚተው እንጂ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ጣልቃ ገብተው የሚመረምሩት ጉዳይ አይደለም።
በኮመን ሎው ሆነ በሲቪል ሎው አገራት የአጣሪ ዳኝነት ጽንሰ ሀሳብ በዳኞች መስመር ቀያሽነት የለመለመና ያደገ፤ መሰረቱ በዳኞች የተተከለ ህግ ነው። በእንግሊዝ የዳኞችን ሚና አንድ የመስኩ ጸሐፊ እንደሚከተለው ይግለጸዋል።
Judicial review is in effect a judge-driven process as it stems from the common law. In other words, it is the courts themselves which have developed, expanded and refined the principles, grounds and remedies available in judicial review proceedings. In effect, the courts determine who can seek judicial review, against whom and on what grounds.e
የኮመን ሎው የህግ ስርዓት በሚከተሉ አገራት ብቻ ሳይሆን በተጻፈ ህግ ብቻ በምትመራው በፈረንሳይ ሳይቀር የአስተዳደር ህግ በተለይም አጣሪ ዳኝነት የዳኞች ህግ ነው።f
ይህ መሆኑ ዳኞች ወሰኑን (scope of judicial review) እንደየአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ የግለሰቦችን መብትና ነፃነት ከውጤታማ አስተዳደር ጋር እያመዛዘኑ ህጋዊነት የማስፈን ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ያስችላቸዋል። በአንድ በኩል ህገ-ወጥ በሆነ አስተዳደራዊ ድርጊት ምክንያት የግለሰቡ መብት እንዳይጣስ ፍ/ቤቶች ለተበደለ ወገን መፍትሄ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። በሌላ በኩል በረባ ባልረባው በሚቀርብ ክስ ውጤታማ አስተዳደር ሊሰናከልና የመንግስት እጆች ሙሉ በሙሉ በፍ/ቤቶች ተጠፍንገው ‘አስተዳደራዊ መኮላሸት’ ሊሰፍን አይገባም።
የአጣሪ ዳኝነት መሰረታዊ ግብ የስልጣን ባለቤት የሆኑ አካላት ተግባራቸውን በህግ ተለይቶ በተሰጣቸው የስልጣን ገደብ ውስጥ ማከናወናቸውን እንዲሁም በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ መወጣታቸውን ማረጋገጥ ነው።g በህገ መንግስት መነፅር ካየነው ፍርድ ቤቶች በአጣሪ ዳኝነት ሚናቸው የህግ የበላይነትን ያስከብራሉ። ሎርድ ሆፍማን የተባሉ የእንግሊዝ ዳኛ በአንድ ውሳኔ ላይ ይህንን ሲያብራሩ እንደተናገሩት፤
The principles of judicial review give effect to the rule of law. They ensure that administrative decisions will be taken rationally in accordance with a fair procedure and within the powers conferred by Parliament.
ወደ አማርኛ ሲመለስ፤
የአጣሪ ዳኝነት መርሆዎች አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች በህግ አውጭው በተፈቀደ የስልጣን ገደብ ውስጥ ምክንያታዊ ይዘት ኖሯቸው በፍትሐዊ መንገድ መወሰዳቸውን ያረጋገጣሉ። በዚህም የህግ የበላይነት ፅንሰ ሀሳብን በተጨባጭ ይተገብራሉ።
የፅንሰ ሀሳቡ አፈጻጸም በአገራችን
ስለ አገራችን ፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ከመወራቱ በፊት መጀመሪያ የጽንሰ ሀሳቡ ይዘትና አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ጥቂት መንደርደሪያ ነጥቦችን መሰንዘር ያስፈልጋል። አጣሪ ዳኝነት በአገራችን የህግና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ያለውን ቦታ፣ አሁን የሚገኝበት ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫዎች ጥርት ያለ ስዕል እንዲኖረን ለፅንሰ ሀሳቡ አገራዊ ፍቺ በመስጠት መጀመር ይኖርብናል። አጣሪ ዳኝነት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ ወይም በሌላ አገር ያለው ትርጓሜ መነሻ ሀሳብ ከመፈንጠቅ በስተቀር በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለጥያቄው ምትክ ምላሽ አይሆንም። ይህም ከሁለት ነገሮች ይመነጫል። አንደኛ፤ የአስተዳደር ህግ ከሌሎች አገራዊ ህጎች (domestic laws) በበለጠ የአንዲት አገር የህዝብ አስተዳደር፣ የፖለቲካና የህገ መንግስት ስርዓትና ታሪክ ነፀብራቅ ነው። በዚህም የተነሳ የአጣሪ ዳኝነት ሆነ ሌሎች የአስተዳደር ህግ መርሆዎችና ፅንሰ ሀሳቦች ከአገር አገር የጎላ ልዩነት ይታይባቸዋል። የዚህ ሀሳብ ተጓዳኝ የሆነው ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ለአጣሪ ዳኝነት የሚቀርብ ማናቸውም ትርጓሜ በፅንሰ ሀሳቡ ይዘትና አፈጻጸም ለሚነሱ መሰረታዊ ጭብጦች በከፊል ምላሹን ይሰጣል። ስለሆነም ፍቺውን ከእንግሊዝ ሆነ ከፈረንሳይ በመቅዳት በእኛ አገር በውሰት ወይም በተሞክሮ ስም ተፈጻሚ ለማድረግ ብንሞክር ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የአጣሪ ዳኝነት ምንነትና አፈፃፀም በተመለከተ ከብዥታ የጠራ አመለካከት የሌለ ከመሆኑም በላይ ለፍ/ቤት የቀረቡ በጣት የሚቆጠሩ ውሱን ጉዳዮች እንደሚያሳዩን ብዥታው በፍ/ቤቶቻችንም ላይ በእጅጉ ይንፀባረቃል። ይህም ጽንሰ ሀሳቡ ወጥነት እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።
ከመነሻው ብንጀምር ‘ኢትዮጵያ ውስጥ አጣሪ ዳኝነት አለ?’ የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል። ለዚህ ወሰኑን ያልለየ ጥቅል ጥያቄ በደፈናው መልስ መስጠት አይቻልም። ቢሰጥም ትክክለኛ አይሆንም። የጥያቄውን ድፍንነት ገልጦ በጥልቀት ለመፈተሸ ወደ ንዑስ ጥያቄዎች መሰንጠቅና አፈጻጸሙንም በነጠላ ማጤን የሚያስማማ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስችላል። በዚህ መልኩ ህላዌነቱም በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመስርቶ ይወሰናል።
መመለስ ያለባቸው ንዑስ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው።
የአገራችን ፍ/ቤቶች በአስተዳደሩ የተፈጸሙ ተግባራትን ህጋዊነት የማጣራትና የማረም የዳኝነት ስልጣን አላቸው? አላቸው ከተባለ የስልጣናቸው ህጋዊና ህገ መንግስታዊ መሰረቱ ምንድነው?
በአጣሪ ዳኝነት ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? በሌላ አነጋገር ፍ/ቤቶች የትኞቹን አስተዳደራዊ ተግባራት ነው ማጣራት የሚችሉት?
አስተዳደራዊ ውሳኔዎች (administrative acts) በፍ/ቤት ሊታዩ ወይም ሊመረመሩ የሚችሉት በየትኞቹ የምርመራ ምክንያቶች (grounds of judicial review) ነው?
አንድ ባለጉዳይ አቤቱታው በአጣሪ ዳኝነት እንዲታይለት ሲጠይቅ ከጥያቄ አቀራረብ ጀምሮ እስከ ክስ መሰማትና ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ተፈፃሚ የሚሆነው ስነ-ስርዓት የትኛው ነው?
ፍርድ ቤቶች በአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ ሲቀርብላቸው ምን ዓይነት ውሳኔ ማስተላለፍ ይችላሉ? ማለትም በአስተዳደራዊ እርምጃ ጉዳት የደረሰበት ወገን ከፍ/ቤቱ ምን አይነት መፍትሄ ማግኘት ይችላል?
እንግዲህ አጣሪ ዳኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከተባለ ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ ማግኘት ይገባል። አንዳንዴ ለከፊል ጥያቄ መልስ ቢኖርም ለተቀሩት ግን ምላሽ ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ባይሆንም ያስቸግራል። እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ሂደት በመጨረሻ ሊደረስበት የሚችለው ድምዳሜ የአጣሪ ዳኝነት ጽንሰ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የዳኞች ጀብደኝነት (judicial activism) እንኳን ባይሆን ብርታት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ነው። በአንድ በኩል ዳኞች ለግለሰቦች መብትና ነፃነት ዘብ በመቆም በሌላ በኩል በስራ አስፈፃሚው ስራ ጣልቃ ከመግባት በመቆጠብ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ እሴቶች በማመዛዘንና በማጣጣም ህጋዊነት የማስፈን ሚናቸውን በብቃትና በብርታት መወጣት ይኖርባቸዋል።
የአጣሪ ዳኝነት ፅንሰ ሀሳብ በአጠቃላይ ይዘቱና ወሰኑ በተለየ መልኩ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የያዘው መልክ በቀጣይ ንዑስ ምዕራፎች በጥልቀት የተዳሰሰ ቢሆንም እንደ መነሻ ያህል አንድ ቁልፍና መሰረታዊ ነጥብ ሁሌ መዘንጋት የለበትም። ይኸውም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ህግ ገና ከህገ መንግስትና ከፍትሐብሔር ህግ ጉያ አልተላቀቀም። በአስተዳደሩ የሚፈጸሙ ተግባራት ህጋዊነታቸው የሚጣራው ራሱን ችሎ በቆመ የአስተዳደር ህግ ወይም የአጣሪ ዳኝነት ስርዓት አይደለም። ህግ አውጭው በህግ ነጥብ ላይ ይግባኝ ከፈቀደባቸው ውስን ጉዳዮች በስተቀር አስተዳደሩን ለተግባራቱ ተጠያቂ የሚያደርግ ከፍትሐብሔር የተለየ የአስተዳደር ፍትሕ ስርዓት (የፍትሐብሔርና የወንጀል ፍትሕ ስርዓት እንደምንለው) የለም።
የፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን
የዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 79/1/ አጣሪ ዳኝነትን እንደሚጨምር አይጠቁምም። በህገ መንግስቱ ላይ የፌደራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ከክልሎች ውክልና ጋር በተያያዘ በስም ቢጠቀሱም የስልጣናቸው ምንጭ ህገ መንግስቱ ሳይሆን የተወካዮች ም/ቤት የሚያወጣው ህግ እንደሆነ በአንቀጽ 78/2/ ተመልክቷል። በአንጻሩ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ የሚመነጨው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን ያላቸው አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ህጋዊነት ለማጣራት ያስችለዋል። ይህ ስልጣን ከሁሉም የፌደራልና የክልል ፌደራል ፍርድ ቤቶች (የክልል የሰበር ችሎቶችን ሳይጨምር) በዓይነቱ የተለየና ብቸኛ ነው።
የፌደራል ፍ/ቤቶች
መደበኛ ፍርድ ቤቶች የስልጣንን ህጋዊነት በሁለት ዓይነት መንገድ ይቆጣጠራሉ፤ በመደበኛ የፍትሐብሔር ክስ እና በአስተዳደራዊ ይግባኝ። መንግስት ተከራካሪ በሚሆንባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በርካታ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በተለይም ከውል ውጪ ኃላፊነት፣ ከንብረት ህግ እና በከፊል ከውል ህግ የሚመዘዙ በርካታ የህጋዊነት ጥያቄዎች በተዘዋዋሪም ቢሆን አስተዳደሩ ለህግ እንዲገዛ ያስገዱዱታል። ፍ/ቤቶች ጠቅላላ ከሆነው መደበኛ ስልጣናቸው በተጨማሪ የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት በይግባኝ እንዲያጣሩ በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። በፍሬ ነገርና በህግ ጉዳይ ላይ የሚፈቀድ ይግባኝ ከዜጋው መብት አንጻር ከአጣሪ ዳኝነት የበለጠ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ነገሩን እንደ አዲስ የማየትና ክርክሩ ከተቋጨ በኋላ በራሱ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የተለጠጠ ስልጣን ያጎናጽፈዋል። አጣሪ ዳኝነት ግን ህጋዊነትን ከማጣራት አይዘልም። የአስተዳደራዊ ውሳኔን በመቃወም ለፌደራል ፍ/ቤቶች ይግባኝ የማቅረብ መብት ከሚፈቅዱ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት
መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ መረጃ ተጠይቆ መረጃውን የያዘው አካል በመከልከሉ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ ከቀረበ በኋላ እንባ ጠባቂው በሚሰጠው ውሳኔ ላይi
የአካባቢ ተቆጣጣሪዎች በሚሰጡት ውሳኔ እንዲሁም እንዲሁም በአካባቢ ላይ የደረሰ ጉዳትን አስመልክቶ ለአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አቤቱታ ቀርቦ ሚኒስቴሩ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ j
በጥራጥሬ ምርቶች ግብይት ተቆጣጣሪ የጥራጥሬ ምርት የተያዘበት ወይም የጥራጥሬ ምርቶች ማከማቻ መጋዘኑ የታሸገበት ሰው ለግብርና ሚኒስቴር ተቃውሞ አቅርቦ ሚኒስቴሩ ተቃውሞውን ባለመቀበል በሚሰጠው ውሳኔ ላይk
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት
ከጥራት ጋር በተያያዘ ቡና የተያዘበት ወይም መጋዘኑ የታሸገበት ሰው ለግብርና ሚኒስቴር ወይ አግባብ ላለው የክልል መንግስት አካል ቅሬታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣl
የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚነሳ ክርክርm
ለሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ አቅራቢነት፣ ላኪነት ወይም አገልግሎት ሰጪነት የብቃት ማረጋገጫ ማመልከቻ ውድቅ ከተደረገ የህግ አተረጓጎምን በተመለከተ ወይም ተፈቅዶለት በዚህ ንግድ የተሰማራ ሰው ከጥራት ጋር በተያያዘ ሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ ተይዞበት ለሚኒስትሩ ወይም አግባብ ላለው የክልል መንግስት አቤቱታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣn
የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት የቀረበ ማመልከቻ ተቀባይነት እንዲያጣ ወይም ፈቃድ የተሰጠው ጠበቃ በዲሲፕሊን ጥፋት ምክንያት ቅጣት በመጣል በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የተወሰደ እርምጃ (በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ)o
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበር ምዝገባ ባለመፍቀድ እንዲሁም ለስራ ውል መታገድ በቂ ምክንያት አለመኖሩን በመግለጽ በሚሰጠው ውሳኔ እና የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወምp
የዕፅዋት አዳቃዮች መብት መስጠትን፣ መከልከልን፣ መሰረዝን ወይም መገደብን በተመለከተ በሚሰጥ ውሳኔ ላይq
የምርት ገበያ ባለስልጣን በሚሰጣቸው በአዋጁ በተመለከቱ ውሳኔዎችr
የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ውድቅ በማድረግ ወይም በመሰረዝ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚሰጥ ውሳኔs
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔ እንዲሁም ባንኩ የሾመው ሞግዚት በሚያስተላልፈው ውሳኔt
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔu
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን በቀጥታ ከህገ መንግስቱ ይመነጫል። ሆኖም የስልጣኑን ወሰን የሚያሰምረው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ የአማርኛውና እንግሊዝኛው ቅጂ ግልጽ መፋለስ ይታይበታል። በአማርኛው ንባብ የሰበር ችሎት መሰረታዊ ‘የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ’ የማረም ስልጣን ይኖረዋል። (ሰረዝ የተጨመረ) የእንግሊዝኛው ቅጂ ደግሞ Over any final court decision የሚል አገላላጽ በመጠቀም ስልጣኑን ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይገድበዋል።
የድንጋጌውን ይዘት ዝርዝር የሚወስነው ህግ ከእንግሊዝኛው ቅጂ ጋር ይስማማል። በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1988 አንቀጽ 10 የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን የሚያገኝባቸው ሶስት ጉዳዮች ተዘርዝረዋል። እነዚህም፤
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች
በሶስቱም ጉዳዮች በውሳኔ ሰጭነት የተጠቀሱት ተቋማት መደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ ናቸው። በኢ.ፌ.ዲ.ረ ህገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ ሀ የእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ court የሚለው ቃል እንዲሁ ይህንኑ ሀሳብ ያንጸባርቃል። ሆኖም የአማርኛው ንባብ ውሳኔ ሰጭውን በዝምታ አልፎታል። ላይ ላዩን ሲታይ ዝምታው ለህገ መንግስታዊ ትርጉም በር የከፈተ አይመስልም። ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ የሚለው አገላለጽ ፍርድ ቤትን ታሳቢ አድርጓል ቢባል ብዙዎችን ያስማማል።
ሆኖም ችግሩ ከቋንቋ አጠቃቀም ያልዘለለ የሚመስለው የአንቀጽ 80/3/ ሀ ድንጋጌ በተግባር ህገ መንግስታዊ ጥያቄ አስነስቶ የሰበር ችሎትን የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አስፍቶታል። በሰ/መ/ቁ. 43511v ከአዋጅ ውጪ የተወረሱ ንብረቶችን በተመለከተ ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጠው የፕራይቬይታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ በቀጥታ በሰበር እንዲታይ አቤቱታ ቢቀርብም አጣሪ ችሎቱ ጉዳዩ አስተዳደራዊ መሆኑን በመጠቆም ውድቅ አድርጎታል። ሆኖም በመዝገቡ ላይ አመልካች ሆነው የቀረቡት አቤቱታ አቅራቢዎች የውሳኔውን ህገ መንግስታዊነት በመሞገት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ አቤቱታ አስገቡ። አጣሪውም ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ የመጨረሻ አማራጫቸውን በመጠቀም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አመለከቱ። ም/ቤቱ የችሎቱን ስልጣን በማረጋገጥ መዝገቡን ወደ ሰበር ችሎት መለሰው። የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቦርዱን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው በማረጋገጥ የተሰጠው ይህ የም/ቤቱ ውሳኔ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ በሚል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ ላይ የተቀመጠውን አገላለጽ ከእንግሊዝኛ ቅጂ ፍጹም የተለየ ይዘትና መልዕክት ሰጥቶታል። በውጤቱም ከፍርድ ቤት ውጭ ያሉ ከፊል የዳኝነት አካላት ላይ የሰበር ችሎት የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል።
የም/ቤቱ ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ስር ነቀልና መሰረታዊ ነው። የስር ፍ/ቤቶችን የህግ ስህተት በማረም ብቻ ተወስኖ የነበረው የሰበር ችሎት በም/ቤቱ ‘በተጨመረለት’ ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጣቸው የአስተዳደር አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ጭምር የማረም የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል። ችሎቱም ዳኝነታዊ የአስተዳደር ውሳኔዎችን ማረም ህገ መንግስታዊ ሚናው እንደሆነ በሌሎች ሁለት መዝገቦች በሰጣቸው ውሳኔዎች በተግባር አረጋግጧል።
በሰ/መ/ቁ. 92546w የድሮው ፍትሕ ሚኒስቴር የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የዲሲፕሊን ውሳኔ በቀጥታ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ተሸሯል። በመዝገቡ ላይ የችሎቱ የዳኝነት ስልጣን አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ባይወጣም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ እና አዋጅ ቁ. 25/88 አንቀጽ 10 ተጠቅሶ የቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ መቀበሉ ሲታይ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣኑ ጠንካራ መሰረት እየያዘ እንደመጣ አስረጂ ነው። በሰ/መ/ቁ. 61221 ቅጽ 14x የተያዘው አቋም ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል። በዚህ መዝገብ በሰፈረው የህግ ትርጉም በፍርድ ቤት እንዳይታዩ በመጨረሻ ማሰሪያ ድንጋጌ (finality clause) ገደብ የተደረገባቸው ውሳኔዎች ሳይቀር በችሎቱ የአጣሪ ዳኝነት ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ጉዳዩ የታየው አዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 ከመውጣታቸው በፊት ሲሆን ቀድሞ በነበሩት የጡረታ ህጎች የማህበራዊ ዋስትና ጉባኤ ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ በይግባኝ ሆነ በቀጥታ ክስ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሊታይ አይችልም።
በሰ/መ/ቁ. 61221 የሰበር አቤቱታ የቀረበው የጉባዔውን የመጨረሻ ውሳኔ በመቃወም ነው። ሆኖም በችሎቱ የዳኝነት ስልጣን ላይ በተጠሪ በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ የስልጣን ምንጭ አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ወጥቷል። ይህንን በማስመልከት ህገ መንግስቱን እና አዋጅ ቁ. 25/88 በማጣቀስ የሚከተለው የህግ ትርጉም ተሰጥቷል።
ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ስራ ላይ በነበረው ሕግ አግባብ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ከተባለ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተመለከተው አግባብ ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ ከማቅረብ የሚከለክል ሕጋዊ አግባብ የለም።
የከተማ ፍ/ቤቶች
በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ የተቋቋሙት የከተማ ፍርድ ቤቶች በውስን ጉዳዮች ላይ ቢሆንም የማይናቅ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አላቸው። ስልጣናቸውን በሚወስኑት ህጎች ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትy በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአጣሪ ዳኝነት የሚታዩ ናቸው።
የከተማውን መሪ ፕላን አፈጻጸም የሚመለከት የይዞታ ባለመብትነት፣ የፈቃድ አሰጣጥ ወይም የቦታ አጠቃቀምን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች
ከከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች
በየከተሞቹ ቻርተር ላይ በተመለከቱት የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ክሶች
የከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በከተማው አስተዳደር ባለቤትነት ስር ያሉ ተቋማት የሚገቧቸውን አስተዳደራዊ ውሎች በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች
በከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በስሩ ባሉ ተቋማት መካከል የሚነሱ ክርክሮች
የከተማው አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ቤቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች
በህግ ከተሰጣቸው የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን በተጨማሪ በከፊል ጉዳዮች አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በይግባኝ ያያሉ። ለምሳሌ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ በሚሰጠው ውሳኔz የመጀመሪያና የይግባኝ ስልጣን አላቸው።
የከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ክልል በህጉ ላይ በወጉ አልተሰመረም። ህግ አውጭው ‘በተመለከተ…በተያያዘ…’ በሚል የተጠቀመው አገላለጽ መብት ጠያቂውን ሆነ ፍርድ ቤቶችን ያደናግራል። የዳኝነት ስልጣን ሊወሰን የሚገባው በክስ ምክንያት፣ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው መፍትሄ ወይም በተከራካሪዎች ማንነት ነው። ለምሳሌ የይዞታ ባለመብትነትን በተመለከተ እንዲሁም ከአስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች እንደ ሁኔታው በፌደራል ወይም በከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር ይወድቃሉ። ይዞታን የሚመለከት ክስ በሁከት ይወገድልኝ ወይም በመፋለም ክስ አሊያም ደግሞ በይዞታ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ በመጠየቅ ሊቀርብ ይችላል። ከግንባታ ፈቃድ ወይም ስም ከማዛወር አስተዳደራዊ ግዴታ ጋር በተያያዘም ይዞታን የሚመለከት ጥያቄ ይነሳል። ከዚህ አንጻር በደፈናው ‘በተመለከተ…’ በሚል የተደለደለው የዳኝነት ስልጣን የመደበኛ እና የከተማ ፍ/ቤቶችን ድርሻ በአግባቡ አይለይም።
ህጉ ግልጽነት ቢጎድለውም ከሰበር ችሎት አካሄድ እና የህግ አውጭው ሀሳብ በመነሳት የከተማ ፍ/ቤቶች መደበኛ የፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣን እንዳልተሰጣቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን። ህግ አውጭው እነዚህን ፍ/ቤቶች ሲያቋቁም ከተወሰኑት በግልፅ ከተነገሩት በስተቀር መደበኛውን የፍትሐብሔር ዳኝነት አላስተላለፈላቸውም። የሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች ያንጸባረቀው አቋም ከዚህ ሀሳብ ጋር ይስማማል። ይህ ከተባለ በኋላ ግን ከላይ በቀረበው ዝርዝር ውስጥ ህግ አውጭው የወሰነው የዳኝነት ስልጣን ምን መልክ እንዳለው መለየት ያስፈልጋል።
ራሱን የቻለ የአስተዳደር ህግ ስርዓት ባላቸው አገራት በፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮች ሶስት ዓይነት ናቸው፤ የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እና የአስተዳደር። በፈረንሳይ የአስተዳደር ክርክሮች ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ተለይተው በተቋቋሙ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች አማካይነት ይዳኛሉ። በጀርመን ራሱን ችሎ በተለይ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ይታያሉ። ከስልጣን ክፍፍል አንጻር መደባቸው ሲታይ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች በፈረንሳይ በስራ አስፈፃሚው ስር የሚገኙ ሲሆን በጀርመን ግን በዳኝነት አካሉ የታቀፉ ናቸው። በእንግሊዝ የፍትሐብሔር ክርክሮችን የሚያስተናግዱት መደበኛ ፍ/ቤቶች የአስተዳደር ክርክሮችንም ደርበው ይዳኛሉ። በእርግጥ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች የሚቀርቡት ለከፍተኛው ፍ/ቤት ቢሆንም ፍ/ቤቱ ራሱን የቻለ የተለየ መዋቅር የለውም። በሶስቱም አገራት በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚካሄዱ ክርክሮች የሚዳኙበት መንገድ ቢለያያም አንድ ነገር ያመሳስላቸዋል። ይኸውም የዳኝነት ስልጣናቸው ዓይነት አጣሪነት (supervisory) ነው። የዚህ ስልጣን ወሰን የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት ማረጋገጥ ብቻ ነው። ከዚህ ያለፉ የፍትሐብሔር ክርክሮችን መደበኛ ፍ/ቤቶች ይረከባሉ። ለምሳሌ አንድ የአስተዳደር ተቋም ከህግ የመነጨ ስልጣኑን በመጠቀም እርምጃ ሲወስድ ክርክሩ በአጣሪነት ዳኝነት ስር ይወድቃል። እንደማንኛውም ግለሰብ በሚፈጽማቸው የግል ተግባራት ሲከሰስ (ለምሳሌ የተቋሙ መኪና በአካል ወይም ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት ካሳ ሲጠየቅ) ደግሞ መደበኛ ፍ/ቤቶች በፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣናቸው ያዩታል።
በከተማ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር ከተዘረዘሩት መካከል የይዞታ ባለመብትነትን በምሳሌነት ብንወስድ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ጉዳዩ የሚታይበት ፍ/ቤት የሚለየው በክሱ ይዘት ነው። ከፍትሐብሔር ውጭ በአስተዳደሩ ላይ ሊቀርብ የሚችለው ክስ ህጋዊነት የሚጣራበት ክስ ነው። ይህም የሚያደርሰን መደምደሚያ የከተማ ፍርድ ቤቶች በህግ የተወሰነላቸው የዳኝነት ስልጣን ዓይነት የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስልጣን እንደሆነ ነው።
የአጣሪ ዳኝነት ስነ-ስርዓት
የአጣሪ ዳኝነት ስርዓት ሲባል አቤቱታው ከሚቀርብበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ያሉ ሂደቶች የሚመሩበትን የክርክር ስነ-ስር ዓት ይመለከታል። የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ በክፍል አራት (አንቀጽ 48-59) የአስተዳደር መመሪያዎችና ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበትን ስርዓት ዘርግቷል። አዋጁ ባልሸፈናቸው የስነ-ስርዓት ጉዳዮች አግባብነት ያላቸው የፍትሐ-ብሔር ስነ-ስርዓት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ።a የድንጋጌዎቹ ይዘት በዝርዝር ከመፈተሻቸው በፊት የአጣሪ ዳኝነት ወይም የክለሳ ስርዓት ከይግባኝ እና ከመደበኛው የክርክር ስርዓት የሚለዩትን ነጥቦች መዳሰስ አስፈላጊ ይሆናል።
አጣሪ ዳኝነት እና ይግባኝ
አጣሪ ዳኝነትን በዝርዝር ከመተንተናችን በፊት ከይግባኝ ጋር ያለውን ልዩነት አንጥረን ልንረዳ ይገባል። ይግባኝ በመሰረቱ በአንድ ተለይቶ በተቀመጠ ህግ መሰረት አንድ ውሳኔ ከነሙሉ ይዘቱ እንደገና እንዲጣራ አቤቱታ የማቅረቢያ ስርዓት ነው።
በሰ/መ/ቁ. 59025b የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለቃሉ በሰጠው ትርጓሜ ‘ይግባኝ’ ማለት፤
በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከራካሪ የነበረና በተሰጠው ፍርድ ቅር የተሰኘ ወገን ይህንኑ ቅሬታውን ለበላይ ወይም ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቅርቦ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ እንዲሻሻል፣ እንዲለወጥ፣ ወይም በጠቅላላው ውድቅ እንዲሆንና ዳኝነቱ ለእሱ እንዲሰጠው ለመጠየቅ የሚያስችል ስርዓት ነው።
ይህ ትርጓሜ በፍ/ስ/ስ/ህጉ ላይ የተመለከተውን መደበኛውን የይግባኝ ስርዓት ማለትም የበታች ፍ/ቤት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሚጣራበትን ስርዓት ይወክላል። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሰው መዝገብ ችሎቱ የቃሉን ይዘት በማስፋት በአስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ለሚቀርብ ይግባኝም ተፈጻሚ አድርጎታል። በዚሁ መሰረት ይግባኝ ማለት በበታች አካል የተሰጠ ውሳኔን በመቃወም ለበላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ ውሳኔው እንደገና የሚታይበት ወይም እንዲጣራ የሚደረግበት ወይም ሊለወጥ የሚችልበት ስርዓትን ይጨምራል። በዚህ በሁለተኛው ትርጓሜ መሰረት አንድ አስተዳደራዊ ውሳኔ በይግባኝ እንዲታረም በልዩ ህግ ሲፈቀድ አቤቱታው የሚስተናገደው በይግባኝ ሰሚው ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። በሌላ አነጋገር በአስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን ይግባኝ የማቅረብ መብት እንዳለው በልዩ ህግ ከተመለከተ አቤቱታው በይግባኝ አቀራረብ ስርዓት እንጂ በመደበኛው የክስ ስርዓት መቅረብ የለበትም።
በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የህግ ምሁራን መካከል ፒተር ኬን በይግባኝ እና በአጣሪ ዳኝነት መካከል ሁለት መሰረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ ይጠቁማል። አንደኛውን ልዩነት እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
The first relates to the remedial powers of the court or tribunal: in appeal proceedings the court or tribunal may vary the decision under appeal or make a substitute decision (‘remake’ the decision). In judicial review proceedings, on the other hand, the court or tribunal’s basic power is to set aside (or ‘quash’) the challenged decisionc
በመርህ ደረጃ የይግባኝ መኖር ይግባኙን ለመስማት ስልጣን የተሰጠው አካል ይግባኝ የተባለበትን ጉዳይ እንደገና ማለትም እንደ አዲስ መርምሮ ተገቢ ብሎ የገመተውን ውሳኔ እንዲሰጥ ይፈቅድለታል። የውሳኔው ይዘት በአጠቃላይ በይግባኝ ሰሚው አካል በጥልቀት ይፈተሻል። ከዚህ በተቃራኒ አጣሪ ዳኝነት የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓቱን መርምሮ በህግ የተቀመጡ የስልጣን ገደቦችንና ቅድመ ሁኔታዎችን መከበራቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ውሳኔው ራሱ የሚገመገምበት ስርዓት አይደለም። ወሰኑ አንድ የአስተዳደር ተግባር እንዴት ተፈፀመ? የሚለውን ጥያቄ እስከመመለስ ድረስ ሲሆን ይግባኝ ግን ከዚህ በሰፋ መልኩ ለምን እንደተፈጸመ? ጭምር በመሞገት ትክክለኛነቱንና ተገቢነቱን አስመልክቶ ማጣራትና ፍተሻ እንዲደረግ ይፈቅዳል። በዚሁ መሰረት ይግባኝ ሰሚው አካል በውሳኔ ሰጪው እግር ስር በመተካት የራሱን አዲስ ውሳኔ የመስጠት ሰፊ ስልጣን አለው።
ሆኖም ፍ/ቤት በአጣሪ ዳኝነት ስልጣኑ በአስተዳደሩ ምትክ ገብቶ የራሱን አዲስ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም። የስልጣን ክፍፍል መርህ የፍ/ቤቱን ሚና የህዝብ አስተዳደር በህግ ማእቀፍ ውስጥ መከናወኑን በማረጋገጥ ላይ እንዲገደብ ያደርገዋል። ሁለተኛው ልዩነት ደግሞ የሚከተለው ነው።
The second main distinction between appeal and review relates to the substantive basis on which the remedial powers of the court or tribunal may be exercised. An application for judicial review will be successful only if the decision under review is ‘illegal’ or ‘unlawful’. By contrast, an appeal not so limited (which we may call a ‘general appeal’) may succeed provided the decision under appeal is ‘wrong’d
ሁለተኛው ልዩነት ይግባኝ የተባለበት ውሳኔ የሚነቀፍበትን መመዘኛ ይመለከታል። በአጣሪ ዳኝነት ስርዓት አንድ ውሳኔ የሚሻረው ህጋዊነትን ካልተከተለ ማለትም ከህግ ውጭ ከሆነ ብቻ ነው። ይግባኝ በአንጻሩ የውሳኔው ትክክለኛነት የሚጣራበት ስርዓት ነው።
የፍትሐብሔር ሙግት እና አጣሪ ዳኝነት
በአጣሪ ዳኝነት እና በፍትሐብሔር ሙግት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ የፊተኛውን ጽንስ ሀሳብ በቅጡ ለመረዳት ወሳኝ ነጥብ ነው። ከስነ-ስርዓቱ አንጻር በአጣሪ ዳኝነት የሚታይ ጉዳይ በአቤቱታ (petition) መቅረብ ያለበት ሲሆን ፍትሐብሔርን መሰረት ያደረገ ጥያቄ ግን የክስ አቤቱታ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል። በክስ መልክ የሚቀርብ ክርክር ለመደበኛው የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ደንቦች ተገዢ ሲሆን ይህም የአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ ከሚስተናገድበት ስርዓት ይለያል።
በተለይ የከሳሽነት ብቃት (standing)፣ የጉዳዩ መብሰል (ripeness)፣ አስተዳደራዊ መፍትሄ በቅድሚያ ማሟጠጥ (exhanstion of remedies)፣ ጉዳዩ በፍርድ ሊዳኝ የሚችል መሆኑ (justicicability) እና የጊዜ ገደብ በመደበኛው የፍትሐብሔር ክስ ጥብቅ ተፈጻሚነት የላቸውም። በፍ/ቤቱ ከሚሰጠው መፍትሄ አንጻር አጣሪ ዳኝነት ከስልጣን በላይ የሆነውን ተግባር ከመሻር፤ እንዳይፈጸም ከማገድ እና ጥያቄው ግዴታን ካለመወጣት ጋር የተያያዘ ከሆነ የማስገደዳ ትዕዛዝ ከማስተላለፍ አይዘልም። ምንም እንኳን በፍ/ብሔር በሚቀርብ ክስ ላይም ድርጊቱን የመሻር፤ የማገድ እና የማስገደድ ውጤት ያለው ውሳኔ ሊሰጥ ቢችልም በዋነኝነት የሚሰጠው ዳኝነት ግን በድርጊቱ ጉዳት የደረሰበትን ወገን መካስ ነው።
ለምሳሌ ከለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 1161/2011 አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የይዞታ ማስለቀቅና የካሳ ክፍያ ጉዳዮች በአስተዳደር ህግ ወሰን ውስጥ ይወድቃሉ። ሆኖም እንደ ሁኔታው የፍትሐብሔር ጥያቄዎችም ይነሳሉ። ሁለቱ በአግባቡ ካልተለዩ የዳኝነት ስልጣን እና የካሳ ክፍያ አወሳሰን ላይ ግራ መጋባት ያስከትላል። የማስለቀቅ እርምጃው ‘የህዝብ ጥቅም ትርጓሜን አያሟላም’ በሚል የሚቀርብ አቤቱታ የእርምጃውን ህጋዊነት የሚሞግት እንደመሆኑ በአስተዳደር ህግ ውስጥ ይመደባል። ለምሳሌ በሊዝ በተላለፈ ይዞታ ላይ የሚካሄድ ግንባታ ‘የሌላ ባለሀብት ሆቴል ይጋርዳል’ በሚል ምክንያት ይዞታን የማስለቀቅ ውሳኔ ለአጣሪ ዳኝነት ከሚያበቁ ምክንያቶች ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ዓላማ በሚለው ስር የሚሸፈን በስልጣን አለአግባብ የመገልገል ተግባር ነው።e የካሳ መጠንን አስመልክቶ የሚካሄድ ክርክር በአስተዳደር ጉባዔ የዳኝነት ስልጣን ስር እንዲወድቅ በልዩ ህግ ተወስኗል።f ጥያቄው በካሳው አለመከፈል ወይም በመዘግየቱ ምክንያት ለደረሰ ጉዳት የተቋረጠ ጥቅም እንዲከፈል ከሆነ ግን በመደበኛ ፍርድ ቤት ስልጣን ስር የሚወድቅ የፍትሐብሔር ክርክር ነው።g
ይዞታ ማስለቀቅ በአዋጅ ቁ. 1161/2011 የሚመራው ይዞታው ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊነቱ ታምኖበት ተገቢው አካል ውሳኔ ሲያስተላልፍ ነው። የይዞታ ማስለቀቅ ስርዓት ሳይከተል በይዞታ ላይ ተጓዳኝ ጉዳት ከደረሰ ግን የካሳ አወሳሰኑ የሚመራው በፍትሐብሔር ህጉ እንጂ በአዋጁ አይደለም። ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ የድሮውን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 455/1997 መሰረት በማድረግ በሰ/መ/ቁ. 59979h የነበረ ክርክርና ውሳኔ ማየቱ ተገቢ ይሆናል። በዚህ መዝገብ ተጠሪ የሆኑትና በስር ከሳሽ የነበሩት ግለሰብ በአመልካች (የስር ተከሳሽ) በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ላይ ባቀረቡት ክስ አመልካች የገጠር መንገድ ሲጠግን አለአግባብ በእርሻ ይዞታቸው ላይ በመግባት የተለያዩ ቋሚ አትክልቶች፣ የሰብል ምርትና ሣር ቤት እንዳወደመባቸውና በቆፈረው ጉድጓድም በሬ ገብቶ እንደሞተባቸው በመግለጽ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።
ችሎቱ ይህን የአመልካችን ጥያቄ ከውል ውጭ ኃላፊነትን የሚመለከት ክስ ሆኖ አላገኘውም። የተጠሪን ጥያቄ የተረዳው አመልካች ለህዝብ ጥቅምና ግልጋሎት የሚውል መንገድ ለመጠገን የተጠሪን ይዞታ እንደወሰደ ነው። የክሱን ይዘት በሚዘግበው የውሳኔው መጀመሪያ ክፍል ላይ ግልጽ ሆኖ እንደሰፈረው ተጠሪ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ይዞታቸውን እንዲለቁ አልተደረገም። ሆኖም አመልካች መንገድ ሲሰራ አለአግባብ በይዞታቸው ላይ ገብቶ በንብረታቸው ላይ ጉዳት አድርሷል። በተገቢው አካል የይዞታ ማስለቀቅ ውሳኔ እስካልተላለፈ ድረስ በግንባታ ሂደት በሶስተኛ ወገን ይዞታ ላይ መግባት ከውል ውጪ ኃላፊነት የሚያስከትል ተግባር እንጂ በአዋጅ ቁ. 455/1997 የሚሸፈን ጉዳይ አይደለም።
የአቤቱታ አቀራረብ ስርዓት
የአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ የሚስተናገድበት ስርዓት ከመደበኛው የፍትሐብሔር የክስ አቤቱታ አቀራረብ ስርዓት ይለያል። አንድ የመስኩ ጸሐፊ ይህን የተለየ የሚያደርገውን ባህርይ እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
A claim for judicial review is something out of the ordinary: the court decides the dispute without a trial. The point of a trial in an ordinary claim is to resolve the issues of fact on which a claim is based. The summary process in a claim for judicial review is designed on the assumption that resolving issues of fact is not the point of the litigation. The point is for the court to review the lawfulness of a public authority’s conduct, and there is often no dispute as to what the public authority has done or proposes to doi
በእንግሊዝ የአስተዳደር ህግ የአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ ማለት፤
[A] claim to review the lawfulness of (i) an enactment; or (ii) a decision, action or failure to act in relation to the exercise of a public functionj
በእንግሊዝ አጣሪ ዳኝነት አቤቱታ እንደ መደበኛ ክስ በቀጥታ አይቀርብም። መጀመሪያ የፍርድ ቤቱ ይሁንታ ያስፈልገዋል።k ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን መርምሮ ጉዳዩ በፍርድ ክለሳ መልክ እንዲስተናገድ ካልፈቀደ በቀር አቤቱታው ለተቃራኒው ወገን እንዲደርስ አይደረግም። ይህ የፈቃድ ቅድመ ሁኔታ የአጣሪ ዳኝነት አንዱና ዓይነተኛው መገለጫ ነው። አቤቱታው የሚቀርብበት ጊዜ በገደብ መታጠሩ ደግሞ ሁለተኛው አንኳር ባህርይ ነው። ክስ የማቅረቢያ ጊዜን በተመለከተ በመደበኛ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የይርጋ ደንብ ነው። ይርጋ ከጊዜ ገደብ ይለያል። ይርጋ በተከራካሪው ወገን እስካልተነሳ ድረስ ፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነት ተፈጻሚ አያደርገውም። በተጨማሪም ከጊዜ መጠኑ አንጻር በዓመታት እንጂ በወራት አይለካም።
በአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ ላይ የሚቀመጠው የጊዜ ገደብ የተንዛዙ ክርክሮች በውጤታማ አስተዳደር ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማስወገድ ያለመ ነው። ስለሆነም ፍርድ ቤት ጊዜው ያለፈበትን አቤቱታ በራሱ አነሳሽነት አይቀበልም። የጊዜው መጠንም በአማካይ ከሶስት ወራት አይበልጥም። የሶስት ወራት ጊዜው ቢኖርም አቤቱታው ሳይውል ሳያድር ወዲያኑ መቅረብ ይኖርበታል። አቤቱታ አቅራቢው እስከ ጊዜ ገደቡ ማብቂያ ድረስ ተኝቶ እንዲቆይ አይፈቀድለትም። ይህም ማለት አቤቱታው በጊዜ ገደቡ ውስጥ ቢቀርብም አለአግባብ ከዘገየ ውድቅ ሊደረግ ይችላል።l
የመደበኛው የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ተፈጻሚነት
በአዋጁ ክለሳ የሚመራበትን ስርዓት የሚገዙ ድንጋጌዎች ውስን በመሆናቸው የተነሳ ክፍተቱን ለመሙላት ‘አግባብነት ያላቸውን’ የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ማድረግ እንደ አማራጭ ተወስዷል። የክለሳ ስርዓት ከፍትሐብሔር ሙግት ተለይቶ ራሱን ችሎ የቆመ እንደመሆኑ ይሄ አማራጭ አስተዳደራዊ ክርክሮች ያለ ባህርያቸው ፍትሐ-ብሔራዊ መልክ ያላብሳቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ያልተገባ መደበላለቅ የአስተዳደር ህግን በፍትሐብሔር ህግ ጉያ ውስጥ ይከተዋል። የሁለቱ የህግ ክፍሎች መነሻ ምክንያት እና መድረሻ ግብ ለየቅል ነው፤ ስነ-ስርዓቱም እንዲሁ።
አስተዳደራዊ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን የመከለስ ሂደት ውጤታማ አስተዳደር ላይ ሊከሰት የሚችለውን ያልተፈለገ አሉታዊ ውጤት በተቻለ መጠን የሚቀርፍ መሆን ይኖርበታል። ክርክሮች በቶሎ ሳይቋጩ በተንዛዙ ቁጥር የአስተዳደር ተቋማት በህግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር ውጤታማ እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ እንዳይወጡ ሰንካላ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ከአስተዳደራዊ ክርክሮች ባህርይ አንጻር ጥብቅ የሆነው መደበኛ ስነ-ስርዓት ለክለሳ ስርዓት ምትክ ሆኖ አያገለግልም። ከዚህ አንጻር የአንድ አገር የከለሳ ስነ-ስርዓት ከአቤቱታ አቀራረብ እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ያሉ መሰረታዊ የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎችን በመደንግ ዳኞች በዝርዝር እና ልዩ ሁኔታዎች እንደየአግባቡ ከመደበኛው የላላ አካሄድ በመከተል ስነ-ስርዓቱን እንዲመሩ ሰፊ ስልጣን ማጎናጸፍ ይኖርበታል።
የክለሳ አቤቱታ የስነ-ስርዓት ጉደለት ያለበት ወይም ከስልጣን በላይ የሆነ መመሪያ ወይም ውሳኔ ህጋዊነቱ በፍርድ ቤት እንዲጣራ የሚቀርብ አቤቱታ እንደመሆኑ መሰረታዊ የፍሬ ነገር ክርክር አያስነሳም። በተጨማሪም ፍሬ ነገርን በማጣራት ረገድ ፍርድ ቤት ስልጣኑ የተገደበ ነው። በልዩ ሁኔታ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ፍርዱ መሰረት የሚያደርገው የአስተዳደር ክርክር የተካሄደበት መዝገብ ነው። ስለሆነም በፍትሐብሔር ህጉ የተመለከቱት የማስረጃ አቀራረብ ደንቦች በክለሳ ስርዓት ተፈጻሚ ሊሆኑ አይገባም። የክስ መሰማት እንዲሁ እንደየጉዳዩ ክብደት እና ውስብስብነት ለክለሳ ክርክር አመቺ እና አስፈላጊ በሆነ መጠን የሚፈጸም እንጂ በመደበኛው የክስ መስማት ስርዓት መመራት አይኖርበትም።
በጥቅል ሲታይ መደበኛው የስነ-ስርዓት ህግ ለክለሳ ክርክር አመቺ አለመሆኑና በውጤታማ አስተዳደር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ በርካታ ጉዳዮች የስነ-ስርዓት ህጉ በወጉ ሊፈታቸው እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የዳኝነት ክፍያን በተመለከተ የክለሳ አቤቱታ ሲከፈት መከፈል ያለበትን የገንዘብ መጠን የሚወስን ህግ የለም። በ1940 ዓ.ም. የወጣው የዳኝነት ክፍያ ታሪፍ ህግ በክለሳ ስርዓት አቤቱታ ሲቀርብ ሊከፈል ስለሚገባው የዳኝነት ገንዘብ መጠን አይናገርም፤ ምክንያቱም ክለሳን የሚመለከት ህግ የወጣው የዳኝነት ታሪፍ ህጉ ከወጣ ከ70 ዓመት በኋላ በ2012 ዓ.ም. ነው። እዚህ ላይ የክለሳ ክርክር “በገንዘብ የማይተመን” ነው የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል። አስተዳደራዊ መመሪያ ወይም ውሳኔ እንዲሻር የሚቀርብ አቤቱታ በገንዘብ የማይተመን ቢሆንም አሁን ያለው የዳኝነት ታሪፍ የተፈጻሚነት ወሰኑ ለፍትሐብሔር ጉዳዮች ብቻ እንደሆነ መረሳት የለበትም። በአስተዳደር ክርክሮች መከፈል ያለበት የዳኝነት ታሪፍ በአንድ በኩል በሆነ ባልሆነው አቤቱታ እየቀረበ በአስተዳደሩ ላይ ያልተፈለገ ጫና እንዳይፈጥር በሌላ በኩል ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው በማረጋገጥ ሁለቱን ተቃራኒ እሴቶች በሚያስታርቅ መልኩ ራሱን ችሎ መወሰን ይኖርበታል።
በፍርድ ከለሳ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ በተመሳሳይ ክርክሮች ላይ “አስቀድሞ የተወሰነ” ስለመሆኑ ተቃውሞ ቢቀርብ የፍ/ስ/ስ/ስ ህጉ አንቀጽ 5 ድንጋጌ የተሟላ መፍትሔ አይሰጥም። መመሪያ እንዲሻር አቤቱታ ቀርቦ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ካደረገው በኋላ ይህንኑ መመሪያ ለማሻር ሌሎች ወገኖች አቤቱታ ማቅረብ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ መፈታት ያለበት ከአስተዳደር ህግ አንጻር ነው። በክለሳ ክርክር የጣልቃ ገብነት እና መቃወም የሚመለከቱ ጉዳዮች የሚያስነሱት ጥያቄ እና የሚፈቱበት መንገድ በፍትሐብሄር ተፈጻሚ ከሚሆነው ፈጽሞ የተለየ ነው።
ለምርመራ የሚያበቁ ምክንያቶች
የግል ባንክ ተረክቦ የሚያስተዳድር ሞግዚት በብሔራዊ ባንክ ሲሾም ሹመቱ በግዴለሽነትና በዘፈቀደ ከሆነ ፍርድ ቤት ሹመቱ እንዲቋረጥ ያዛል።m
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም ማናቸውም የግብይት ውል እንዲሰረዝ፣ በግብይት ውል ላይ ዕገዳ እንዲጣል እንዲሁም በማናቸውም የግብይት ውል ላይ ጊዜያዊ አስቸኳይ የመያዣ መጠን እንዲወሰን ለምርት ገበያው መመሪያ የመስጠት ስልጣን አለው። የባለስልጣኑን ውሳኔ በይግባኝ ለማየት ስልጣን የተሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔው በዘፈቀደ ከተሰጠ፣ በማስረጃ ካልተደገፈ ወይም ሕግን ያልተከተለ ከሆነ እንዲታገድ ለማዘዝ ይችላል።n
ከጥብቅና ዲሲፕሊን ወይም ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የሚሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ከሆነ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በህግ ነጥብ ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ለጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ይመልሰዋል።o
በጂኦተርማል ስራ ለመሰማራት ፈቃድ በተሰጠው ሰው እና በፈቃድ ሰጪው አካል መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በጋራ ውይይት ካልተፈታ በግልግል ዳኝነት ስርዓት ታይቶ ውሳኔ ያገኛል። በግልግል ዳኝነት በሚሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኙን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።p
በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ስምምነት ወይም ልዩ ፈቃድ በመከልከል፣ በማገድ ወይም በመሰረዝ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በሰጠው ውሳኔ ላይ በህግ አተረጓጎም ስህተት ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኙን ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።q
ከላይ በምሳሌነት በተዘረዘሩት የህግ ድንጋጌዎች ላይ የተጠቀሱት የይግባኝ ምክንያቶች በዋነኛነት የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ስልጣን ይወስናሉ። በመርህ ደረጃ ይህ እውነት ቢሆንም በተግባር ግን የስልጣኑን ወሰን የሚያጠበውና የሚያሰፋው ራሱ ፍርድ ቤቱ ነው። የምክንያቶቹ አገላለጽ ፍርድ ቤት አስተደደሩን የመቆጣጠሪያ ገመዱን እንዲያሳጥር አሊያም እንዲያስረዝም ሰፊ ዕድል ይሰጣል። ለምሳሌ አንድ ውሳኔ ‘በዘፈቀደ የተሰጠ’ የሚያስብለው ምን ዓይነት ግድፈቶች ሲታዩበት ነው? የህግ ስህተት እና የህግ አተረጓጎም ስህተት ልዩነታቸው ምንድነው? በህግ እና በፍሬ ነገር ስህተት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ሁለቱንስ ሁልጊዜ መለየት ይቻላል? ለምሳሌ ምንም ማስረጃ ሳይኖር የተሰጠ ውሳኔ ስህተቱ የህግ ነው ወይስ የፍሬ ነገር? ህጉ የይግባኝ ምክንያት ሳያስቀምጥ የይግባኝ መብት ሲያጎናጽፍ ፍርድ ቤት ውሳኔውን የሚመዝነው በምን መለኪያ ነው?
እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በእኛ አገር ቀርቶ የዳበረ የአስተዳደር ህግ ባላቸው አገራት አሁንም ቁርጥ ያለ ምላሽ አላገኙም። በየአገሩ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩን ለመቆጣጠር የየራሳቸውን መለኪያ ይጠቀማሉ። መለኪያዎቹ በስያሜና በአገላለጽ ወጥነት የላቸውም። ይህ ደግሞ በንጽጽሮሽ ጥናት ዳሰሳ ለማድረግ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ለአጣሪ ዳኝነት አፈፃፀም አንዱ አስቸጋሪ ጉዳይ የምርመራ ምክንያቶች (grounds of judicial review) ተብለው የሚዘረዘሩት ሁኔታዎች በተለያየ ቃላት መጠራታቸው ሲሆን ይህም አንድ ውሳኔ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ማዕዘናት እየተመረመረ እንዲዋልልና አስተዳደሩ እጅና እግሩ ታስሮ በስልጣኑ እንዳይጠቀም ምክንያት ይሆናል። ከላይ የሌላ ግለሰብ ሆቴል ይጋርዳል በሚል የሚወሰድ የይዞታ ማስለቀቅ እርምጃ ከአዋጁ ዓላማ ውጪ ብቻ ሳይሆን በዘፈቀደ የተሰጠ ውሳኔ ነው። ከዚያም አልፎ ኢ-ሚዛናዊ ነው። እርምጃውን ኢ-ምክንያታዊ ብሎ መፈረጅም ይቻላል። በሌላ መልኩ ካየነው ውሳኔ ሰጭው አካል የህዝብ ጥቅም መኖሩን ለመወሰን በአንድ ግለሰብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባቱ እርምጃው ተገቢ ያልሆኑ ሁነታዎችን ከግምት በማስገባት የተሰጠ ነው። ከህግ አተረጓጎም ብቻ ካየነው ደግሞ እርምጃው የህግ ስህተት የተፈጸመበት እርምጃ ነው።፡ እስካሁን የተጠቀሱት ምክንያቶች ሁሉ ራሳቸውን ችላ ለአጣሪ ዳኝነት የሚያበቁ ናቸው።
ከዚህ እንደምንረዳው ፍርድ ቤቶች የስልጣን አለግባብ መገልገልን በቅጡ ለመቆጣጠር እንደየአገሩ ነባራዊ ሁኔታ አደናጋሪ ፍቺ የሌላቸው ውስን ቃላትን በወጥነት መጠቀም ይኖርባቸዋል። ቅጥ ያጣ የአጣሪ ዳኝነት ምክንያት የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ በእንግሊዝ ፍ/ቤት በቀረበ አንድ ጉዳይ ዳኛ ሎርድ ሎውሪ (Lord Lowry) ተጠቃሽ ፍርድ ሰጥተው ነበር። የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ፀሀፊ (Home secretary) በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ (BBC) እና አይ.ቢ.ኤ (IBA) ከተወሰኑ በሚኒስትሩ በስም ከተጠቀሱ የአሸባሪ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ቃለ ምልልስ እንዳያደርጉ በመከልከላቸው የሚኒስትሩ ውሳኔ በተጨባጭ ከሚታየው ችግር ጋር ሲመዛዘን ተመጣጣኝ ስላሆነ አለአግባብ በስልጣን መገልገል ተብሎ እንዲሻርላቸው ሁለቱም ድርጅቶች ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ። ዳኛ ሎርድ ግሪን አቤቱታውን ውድቅ ሲያደርጉ እንዲህ ብለው ነበር።
በእኔ እምነት ተመጣጣኝነት የሚለው ቃል የፍርድ ቤቱን ትኩረት ተቀባይነት ካላቸው የአጣሪ ዳኝነት ምክንያቶች በማሸሽ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ የሚገባበትን መሰረት አለቅጥ ለማስፋት የታለመ ነው። ይህም መረጋጋትና እርግጠኝነትን አደጋ ላይ ይጥላል። ምክንያቱም በማንኛውም አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ላይ ቢያንስ አንድ እንከን ማውጣት ይቻላልና።
የዳኛ ሎርድ ግሪን ስጋት የምርመራ ምክንያቶች በበዙ ቁጥር ዳኞች ባልተጨበጠ መነሻ አስተዳደሩ የሚሰጠውን ውሳኔ ይዘት ከስልጣናቸው ውጪ እንዲመረምሩት ያደርጋል የሚል ሲሆን በተያያዥነትም ‘የክስ ጎርፍ’ በማስከተል የፍርድ ቤቶችንና የአስተዳደሩን ወርቃማ ጊዜና ገንዘብ ማባከኑ አይቀሬነቱን አስምረውበታል። ተመሳሳይ ሃሳብ በምሁራኑ ዘንድ እንዲህ ተገልጿል።
አጣሪ ዳኝነት የስልጣን አለግባብ መገልገል መገደቢያ ብቻ ሳይሆን የዳኞች አለግባብ በስልጣን መገልገል መንስኤም ሊሆን ይችላል።
ጠቅለል ባለ መልኩ የአጣሪ ዳኝነት ምክንያቶችን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሰንጥቀን መተንተን እንችላለን። የመጀመሪያው ህጋዊነት ሲሆን በስሩ ከስልጣን በላይ (በአውስትራሊያ ከስልጣን በላይ በጠባቡ (simple or narrow ultravires)፣ የዳኝነት ስልጣን ስህተት (jurisdictional error)፣ የህግ ስህተት (error of law) እና የስነ-ስርዓት ጥሰት (procedural impropriety) ያቅፋል። በሁለተኛው ክፍል የሚወድቀው የስልጣን አለአግባብ መገልገል (abuse of power or discretion) ሲሆን አንዳንዴ ከስልጣን በላይ በሰፊው (Broad ultravires) እየተባለ ይጠራል። የስልጣን መገልገል የአግባብነቱ መለኪያ በባህርዩ ህሊናዊ (subjective) በመሆኑ በአግባብና አለአግባብ የስልጣን መገልገል መካከል ያለውን ትክክለኛ መስመር ወጥነትና እርግጠኛነት ባለው መንገድ ለማስመር አዳጋች አድርጐታል።
ህጋዊነት
በአገራችን ከስልጣን በላይ መርህን የሚደነግገው የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 401 ንዑስ ቁጥር 1 እንደሚከተለው ይነበባል።
በሕግ የታወቀላቸው የተግባር ስልጣን ከሚዘረጋበት ውጭ ወይም በህጉ የተገደዱትን ሁኔታዎች ወይም ፎርም ባለመፈጸም…የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች የሚፈጽሟቸው ስራዎች ፈራሾች ናቸው።
በድንጋጌው ላይ የሚስተዋለው ከቋንቋ አገላለጽ የመነጨ ብዥታ የእንግሊዝኛው ቅጂ ያጠራዋል። እንደሚከተለው ይነበባል።
Acts performed by … bodies ... in excess of the powers given to them by law or without the observance of the conditions or formalities required by law shall be of no effect
በአማርኛው ላይ ‘በሕግ የታወቀላቸው የተግባር ስልጣን ከሚዘረጋበት ውጭ’ የሚለው አገላለጽ በእንግሊዝኛው ቅጂ in excess of the powers given to them by law በሚል ተተርጉሟል።
አስተዳደራዊ ውሳኔ፣ መመሪያ፣ ደንብ ወይም ሌላ ማናቸውም ድርጊት ለውሳኔ ሰጪው ወይም የውክልና ህግ አውጭው አካል በህግ ከፈቀደለት ስልጣን በላይ ከሆነ እንዲሁም አንዳችም የህግ ስልጣን ከሌለው ከስልጣን በላይ ነው። የስልጣን ምንጩ ህግ ነው። ስልጣን ገደቡን አልፏል የሚለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አንዳንዴ ብርሀንን ከጨለማ የመለየት ያክል ቀላል ነው። አንድንድ ጊዜ ደግሞ ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ከህግ፣ ከፖሊሲ እና ከህገ መንግስታዊ መርሆዎች ብሎም ከህግ አተረጓጎም መሰረታዊ ደንቦች አንጻር ጥልቅ ፍተሻ ማድረግ ይጠይቃል። ከዚህ በታች የቀረበው ዳሰሳ ከስልጣን ገደብ እና ህጋዊነት ጋር በተያያዘ የሰበር ችሎትን አቋም ያስቃኛል።
ካርታ ማምከን
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የባለቤትነት ማረጋገጫ የመስጠት ስልጣን ያላቸው አካላት ‘ካርታ ማምከን’ የሚሉት አዲስ ፈሊጥ አምጥተዋል። ፍርድ ቤቶችም ቃሉን በተውሶ እያዘወተሩት ወደ ህግ ቃል እየቀየሩት ነው። ይህ የማምከን እርምጃ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በተደጋገሚ ሲስተዋል የነበረ አሳዛኝ ክስተት ነው። ህገ መንግስታዊ ንብረት የማፍራት መብትን አደጋ ውስጥ የከተተው ‘ከመሬት ተነስቶ’ ካርታ የማምከን ተግባር በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠረው በመጥፋቱ የተነሳ አስተዳደሩ ከህገ ወጥነት ወደ ጋጠ ወጥነት ተሸጋግሯል። በአስረጂነት ከሚጠቀሱ የሰበር ችሎት መዝገቦች መካከል የሰ/መ/ቁ 17712r አንደኛው ነው። በዚህ መዝገብ አመልካች ሆኖ የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ሲሆን ተጠሪ የወሮ ሳድያ እስማኤል ወራሾች ናቸው። የጉዳዩ አመጣጥና በሰበር የተሰጠው ውሳኔ በአጭሩ እንዲህ ይተረካል።
ክርክሩ የተጀመረው በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን መልስ ሰጭዎች በውርስ የተላለፉላቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት የንግድ ቤቶችን ተከራይተው የሚሰሩባቸው ግለሰብ ቤቶቹን እንዲያስረክቧቸውና ያልተከፈለ ኪራይም እንዲከፍሉ በማለት ክስ ያቀርባሉ። ፍርድ ቤቱም መብታቸውን በማረጋገጥ ወሰነላቸው። ከውሳኔ በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳደር ቤቶቹ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሱና ከዚህ ቀደም ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ የተሰረዘ መሆኑኑ በመግለፅ በክርክሩ ውስጥ በተቃውሞ ገብቶ የባለቤትነት ጥያቄ ያነሳል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ እና በይግባኝ ያዩት የስር ፍ/ቤቶች ‘ቤቶቹ ስለመወረሳቸው የሚያረጋግጥ የመረካከቢያ ቅፅ አልቀረበም’ በሚል የአስተዳደሩን ጥያቄ ውድቅ አደረጉት። አስተዳደሩ የሥር ፍርድ ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ስላለባቸው ይታረምልኝ በማለት የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ የሰበር ችሎት የሚከተለውን ውሳኔ በድምፅ ብልጫ ሰጠ።
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍል ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃ ለተሰጠው ሰው ለዚሁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብት እንደሆነ እንደሚያስቆጥረው ተመልክቷል። በአንፃሩ ማስረጃው የተሰጠው ከደንብ ውጭ በሆነ አሰራር መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ …በፍትሐብሔር ቁጥር 1195 ላይ የተመለከተው የሕሊና ግምት ፈራሸ እንደሚሆን የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) ይደነግጋል። በያዝነው ጉዳይ በሕግ አግባብ ስልጣን ተሰጥቶት ይህን መሰሉን የባለሃብትነት ማስረጃ የሚሰጠው ክፍል ቁጥር 5127386 የሆነው የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት የሰረዘው መሆኑ ተረጋግጧል። በተሰረዘ የባለሃብትነት ምስክር ወረቀት ደግሞ የሚገኝ የባለሃብትነት መብት አይኖርም። የተጠሪ ወራሾችም አውራሻቸው ያልነበራቸውን መብት ሊወርሱ አይችሉም።
ለንፅፅር እንዲረዳ በሓሳብ ልዩነት የተሰጠውን አስተያየትና ምክንያት ማየቱ ተገቢ ነው።
አመልካች የአዲስ አበባ መስተዳደር በቤቶቹ ላይ መብት አለኝ የሚለው በመንግስት የተወረሱ ናቸው በሚል መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል። ይሁን እንጂ ቤቶቹ በመንግስት የተወረሱ መሆናቸውን የሚያሳይለት ማስረጃ አላቀረበም። ለተጠሪዎች አውራሸ ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር ተሰርዟል ማለቱ ብቻውን ለእርሱ መብት የሚሰጠውና አቤቱታውም በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 አግባብ እንዲሰተናገድለት ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። በኔ እምነት የሥር ፍርድ ቤቶች ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰው ክርክሩን እንደገና መመርመር ሳያስፈልጋቸው አመልካቹን ወደ ክርክሩ ለመግባት የሚያስችልህ መብት መኖሩን አላስረዳህም በሚል ከወዲሁ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው የፈፀሙት የሕግ ስህተት የለም።
የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ግምት በፍ/ሕ/ቁ 1196 በተደነገገው መሠረት ፈራሸ ሊሆን ይችላል። የባለቤትነት ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ ከሆነ መሰረዙን ህግ ይፈቅዳል። ሆኖም የመሰረዝ ስልጣን ያለው አካል የካርታው አሰጣጥ ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ የማስረዳት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። የአዲስ አበባ መስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ ካርታውን ሲሰርዝ ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ መሆኑን የማሳየትና የማስረዳት ግዴታ አለበት። ይህን ካላደረገ እርምጃው ከሥልጣን በላይ እንደመሆኑ በሕግ ፊት ዋጋ አይኖረውም። አመልካች ካርታው ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ ወይም ቤቶቹ በአዋጅ ስለመወረሳቸው በክርክሩ ቢጠቅስም ከአባባል ያለፈ በተጨባጭ ማስረዳት አልቻለም። ስለሆነም የመሰረዝ ድርጊቱ የሕጋዊነት መርህን የሚጥስ፣ የሕግ የበላይነትን የሚጻረር፣ ከስልጣን በላይ የሆነ ድርጊት ነው።
የአብላጫው ድምፅ ይህን መሠረታዊ ጭብጥ አላነሳውም። ከዚህ በተጨማሪ ካርታው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) መሠረት ተሰርዞ በምትኩ ለሌላ 3ኛ ወገን ሲተላለፍ ሶስተኛው ወገን የቤቱ ሕጋዊ ባለቤት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ባለቤትነቱ የተሰረዘውን የንግድ ቤት የራሱ ሃብት ሲያደርገው በሕጉ መሠረት የባለቤትነት መብት የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። በአዋጅ ቁ 47/67 ተወርሷል የሚል ከሆነ እንደተወረሰ በበቂ ማስረጃ ማሳየት አለበት። አመልካች የቤቱ ባለቤት ስለመሆኑ አሁንም በአብላጫው ድምፅ ላይ ጭብጥ ሆኖ ተነስቶ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰበትም። በእርግጥ በተሰረዘ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የሚገኝ የባለሀብትነት መብት አይኖርም። ከዚህ ድምዳሜ በፊት ግን የህግ የበላይነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት።
ተጠሪዎች እየሞገቱ ያሉት የመሰረዙን ሕጋዊነት ነው። የተጠሪዎች ሙግት በአብላጫው ድምፅ ሰሚ አላገኘም። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ካርታው ከደንብ ውጭ ለአመልካች እንደተሰጠ ስላላስረዳ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ወይም ከስልጣን በላይ ነው። በቤቱ ላይ በሕጉ መሠረት ባለቤት እንደሆነ ስላላስረዳም ‘ከመሬት ተነስቶ’ በሌላ ሰው ሀብት ላይ መብት አይችልም። ይህን ሀሳብ በአነስተኛ ድምፅ አስተያየት ስንቋጨው፤
አመልካች እንኳንስ መብት ሊኖረው ቀድሞውኑ በተቃውሞ ወደ ክርክር ውስጥ እንዲገባ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር።
በሌላ ተመሳሳይ መዝገብ እንዲሁ ፍርድ ያረፈበትን የባለቤትነት መብት አስተዳደሩ ስላመከነው መና ሆነ ቀርቷል። በሰ/መ/ቁ. 22719s ተጠሪ በሁለት የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር /ካርታ/ የተመዘገቡ ሶስት የቤት ቁጥር የተሰጣቸው ቤቶች የራሳቸው መሆናቸው ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ውሳኔ አርፎባቸው በአፈጻጸም መዝገብ ቤቶቹን ተረክበዋል። የፍርድ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ አመልካች የቤት ማረጋገጫ ደብተሮቹን በመሰረዙ ተጠሪ ክስ አቀረቡ። በሰበር ችሎት በነበረው ክርክር ችሎቱ ተጠሪ መብታቸውን በፍርድ ቤት አስከብረውና አረጋግጠው የተፈጸመባቸው ዓይን ያወጣ ህገ ወጥ ተግባር ከማረምና የህግ የበላይነትን ከማስከበር ይልቅ ክስ የማቅረብ መብታቸውን ነፍጓቸዋል። ችሎቱ ለማመዛን እንደሞከረው፡
አመልካች የተጠሪን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶች ከሰረዘ ተጠሪ አስቀድሞ በተጠቀሱት ቤቶች ላይ ባለመብት መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን በእጁ ማስገባት ይኖርበታል። ይህ መሠረታዊ ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ማስረጃ ሳይኖረው ፍ/ቤት ሰነድ እንዲሰጠው እንዲወሰንለት መጠየቅ አይቻልም።
በአጭር አነጋገር ቤቱን በአስተዳደሩ ህገ ወጥ ተግባር የተነጠቀ ሰው ቤቱ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት እንኳን የለውም።
የሰበር ችሎት ዘግይቶም ቢሆን የሰ/መ/ቁ 17712 እና 22719 ውሳኔ ካገኙ ከሰባትና አምስት ዓመታት በኋላ ፍጹማዊ በሆነውና ፍጹማዊነቱንም ችሎቱ ይሁንታ በሰጠው የአስተዳደሩ ካርታ የማምከን ስልጣን ላይ ገደብ ለማበጀት ተገዷል። በሰ/መ/ቁ. 42501t ፍርድ ባረፈበት ጉዳይ ካርታ ማምከን ህገ ወጥነቱን ጠንከር ባሉ ቃላት እንደሚከተለው ገልጾታል።
አንድ የአስተዳደር አካል በፍርድ ቤት ክርክር መረታቱን ከተረዳ በኃላ በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መነሻ በማድረግ ለፍርዱ መሰጠት መሠረት የሆነውን ማስረጃ ዋጋ በማሣጣቱ ምክንያት የፍርድ አፈፃፀም ዋጋ እንዲያጣ የማድረግ ውጤት በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 78/1/ እና 79/1/ እና /4/ ስር የተረጋገጠውንና የተከበረውን የነፃ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነት ስልጣን ትርጉም አልባ የሚያደርገው ነው።
የስልጣን ተዋረድ
በፌደራል መንግስቱ የስራ አስፈፃሚ አካል የስልጣን ተዋረድ ከላይ ወደ ታች የተዋቀረ ነው። በላይኛው ጫፍ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው። በተዋረዱ ቀጥሎ የሚገኘው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከፍተኛ የአስፈፃሚነት ስልጣን ይጋራል። ዝቅ ሲል የሚኒስቴር እና ሌሎች የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በተቋቋሙበት ዘርፍ ህግና ፖሊሲ ያስፈጽማሉ። በህግ በተሰጣቸው የስልጣን ክልል ህግና ፖሊሲውን ወደ መሬት ያወርዱታል። የመንግስት አስተዳደር ህያው ሆኖ የሚታየው በእነዚህ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ነው። ከታች እስከ ላይ ያሉት የስልጣን አካላት አንዱ ለአንዱ ተጠሪ በመሆን እርስ በእርስ ተሳስረዋል። ስለሆነም በከፊል ልዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እያንዳንዱ ሚኒስትር መ/ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ አንድ ወይም ከዛ በላይ የሆኑ የአስተዳደር መ/ቤቶች ከበላያቸው ለሚገኝ ሚኒስትር መ/ቤት ተጠሪ ናቸው።
ለመሆኑ ተጠሪነት ማለት ምን ማለት ነው? ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ታች የአስተዳደር መ/ቤቶች ድረስ ያለው የህግ ግንኙነት ምንድነው? የበላይ የበታቹን የሚቆጣጠረው እንዴት ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ከህግ ዕውቀት በላይ በሌሎች የጥናት መስኮች ትንተናና ማብራሪያ የሚጠይቅ ውስብስብ ጉዳይ በመሆኑ እዚህ ላይ የሚነሳ አይሆንም። ሆኖም የስልጣን ተዋረዱ በህግ መነጽር ሲታይ የህጋዊነት ጥያቄን ለመመለስ ውስብስብነቱ ሊያደናግረን አይገባም። አንድ ድርጊት ወይም ውሳኔ በስልጣን ገደብ ውስጥ የሚወድቅ መሆኑን/አለመሆኑን ድምዳሜ ላይ የሚደረሰው የስልጣኑን ምንጭ በማመሳከር ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስልጣን በቀጥታ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ መንግስት ይመነጫል። የሚኒስቴሮችን ጨምሮ ሁሉም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣን የሚያገኙት ከተወካዮች ምክር ቤት ነው። እያንዳንዱ መ/ቤት በተቋቋመበት ህግ እና በሌሎች ልዩ ህጎች ስልጣኑ ተሸንሽኖ ይደለደላል። ምንም እንኳን ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚኒስቴር በታች ያሉ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚቋቋሙት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢሆንም የስልጣኑ ዓይነት ውክልና እንደመሆኑ ዞሮ ዞሮ ዋናው የስልጣን ባለቤት እና ምንጭ የተወካዮች ምክር ቤት ነው። ስለሆነም የላይኛው የታችኛውን ውሳኔ ለማረም መንገዱ በህግ ካልተሰመረለት በስተቀር ውሳኔውንና እርምጃውን ሊሽረው አይችልም።
ሆኖም ይህን መሰረታዊ የህገ መንግስታዊነትና የህጋዊነት መርህ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት ገና በቅጡ አልተረዳውም። በሰ/መ/ቁ. 16195u ተጠሪዎች በመንግስት ለተወረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው አበል እንዲከፈላቸው የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር በወሰነላቸው መሰረት ይከፈላቸው ዘንድ በአመልካች ላይ ክስ አቀረቡ። ከክርክሩ በኋላ ክሱ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ያለው አበል እንዲከፈላቸው ተፈረደላቸው። ፍርዱም በከፍተኛው ፍ/ቤት ፀና። ሆኖም የሰበር ችሎት ሻረው። በመዝገቡ ላይ የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር ውሳኔ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እንደተሻረ ተመልክቷል። በዚህ መልክ መሻሩ ችሎቱም የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ለመሻር ምክንያት ሆኖታል። ችሎቱ ህገ መንግስቱን በማጣቀስ ለማብራራት እንደሞከረው፤
[በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.] ህገ-መንግስት አንቀጽ 74/4/ ሁሉም ሚኒስቴሮች የሚገኙበትን የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚመራ፣ እንደሚያስተባብርና እንደሚወክል ተመልክቷል። እንዲሁም…የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አ/ቁ 4/87 አንቀጽ 11/1/ ሥር እያንዳንዱ ሚኒስትር፣ የሚመራውን ሚኒስቴር መ/ቤት የሚመለከቱ ሥራዎች ፕሮግራሞችና ህጎች አፈፃፀም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት መሆኑ ተገልጿል። ከነዚህ ህጎች አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስቴር መ/ቤቶችን በበላይነት የመምራትና ስራቸውንም የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል። በመሆኑም ሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የፈፀሙትን ስህተት ማረምና ማስተካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ስር የሚወድቅ ነው።
በበላይነት መምራትና መቆጣጠር የበታች ውሳኔዎችን የመሻር ስልጣን አያጎናጽፍም። ህገ መንግስቱ ይህን የመሻር ስልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጓዳኝ አልሰጠም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሾመውን ባለስልጣን የመሻር ስልጣኑ የተጠበቀ ቢሆንም መ/ቤቱ እንደ ተቋም የወሰነውን ውሳኔ ሊሽረው፣ ሊለውጠው ሆነ ሊያሻሽለው ግን ህገ መንግስታዊ ስልጣኑ አይፈቅድለትም። እንዲህ ዓይነት የስልጣን ባለቤት ከሆነ በእርግጥ እርሱ ንጉስ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስቴር አይደለም። በታሪክ መለስ ብለን ወደ ኋላ ስናይ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ህገ መንግስታት ንጉሱ ማናቸውንም ውሳኔዎች የመሻር፣ የመቀየር፣ የመተካት፣ መ/ቤቶችን የማቋቋምና ስልጣናቸውን መጥኖ የመስጠትና መልሶ የመንጠቅ ፍጹማዊ ስልጣን ጨብጠው ነበር።v በህግ የተቋቋመ መ/ቤት ለአንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት መብት በማጎናጸፍ ወይም በመንሳት የሚሰጣቸው ውሳኔዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሆነ ተጠሪ በሆነለት ሚኒቴር መ/ቤት እንዲሻሩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ መንግስት አይፈቅድም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
በተለምዶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት (አንዳንዴ ቢሮ) እየተባለ የሚታወቀው አካል ስልጣንና ተግባሩ በህግ ተወስኖ አልተቋቋመም። በአቋሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ቢሮ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በአግባቡ እንዲያከናውን ለማገዝ የሚረዱ የቢሮ ስራዎችን ከማከናወን በስተቀር በማናቸውም መንግስታዊ ሆነ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የመወሰን ሆነ ለበታች አካላት መመሪያ የማስተላለፍ ስልጣን የለውም።
ጽ/ቤቱ በታሪካዊ አቋሙ ከነበረው የቆየ ስም እንዲሁም የደርግ መውደቅን ተከትሎ በሽግግሩ መንግስት ጊዜ በዘልማድ በሚያከናውናቸው መንግስታዊ ተግባራት (በተለይ ቅሬታ ሰሚ በመሆን) የተነሳ በህግ ሳይሆን በዕውቅና (de facto) ህልውና ያገኘ የመንግስት ተቋም ለመሆን በቅቷል። ከላይ በተጠቀሰው የሰ/መ/ቁ. 16195 የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር ውሳኔን የሻረው ጽ/ቤቱ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይደለም። ሆኖም የሰበር ችሎት የውሳኔውን ህጋዊነት ያጣራው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህገ መንግስታዊ ስልጣን በማመሳከር ነው። ሁለቱ እንደ አንድ አምሳል፣ አንድ አካል ተቆጥረዋል።
ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር የግል ቢሮ ነው። የግል የሆነበት ምክንያት እንደ አገሪቱ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በህግ አልተቋቋመም። የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 131/1991 ጽ/ቤቱን ህጋዊ ሰውነት አላብሶ አቋቁሞታል። ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ግን ተመሳሳይ የህግ መሰረት የለም። በስልጣኑ ላይ የሚነሳው ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄ የማቋቋሚያ አዋጅ አለመኖሩ ብቻ አይደለም። ከጊዜ በኋላ ጽ/ቤቱን የሚያቋቁም አዋጅ ቢወጣም እንኳን ከጽህፈት (ከቢሮ) ስራ የዘለለ በማናቸውም መንግስታዊ ጉዳዮች ውሳኔ የማስተላለፍ ሚናና ተግባር ሊኖረው አይችልም።
ከህገ መንግስቱ የሚመነጩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናት ወደ ሌላ አይተላለፉም። ከምክትል ጠ/ሚኒስትሩ በቀር ሚስት/ባል፣ ልጅ፣ ወላጅ፣ ጽ/ቤት ሆነ ሌላ ማናቸውም አካል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን መጋራት አልተፈቀደላቸውም። በህግ የተቋቋመ የሚኒስቴር መ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ጽ/ቤቱ መሻር ይችላል ማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ ተመሳሳይ የመሻር ስልጣን አለው የማለት ያክል ነው።
የሰበር ችሎት ይህን ግዙፍ ህገ መንግስታዊ በሰ/መ/ቁ. 34665w ላይም ደግሞታል። በመዝገቡ ላይ የተነሳው የህግ ጥያቄ የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት (ደብተር) የመሰረዝ ስልጣን ህጋዊነት ሲሆን የፍሬ ነገር መነሻ ታሪኩ አስደማሚና አስገራሚ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። በወቅቱ ማለትም በ1991 ዓ.ም. ላይ የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር በመስሪያ ቤቱ ይገኙ የነበሩ የቤት ጉዳዮችን ከሰራተኞቹ ጋር ለአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ስራና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲያስረክብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ትእዛዝ ደረሰው። በትዕዛዙ መሰረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጉዳዮቹንና ሰራተኞቹን አስረከበ። የአ/አበባ መስተዳድ ምክር ቤት ስራና ከተማ ልማት ቢሮ ከየካቲት 1 ቀን 1991 ዓ.ም ጀምሮ የቤት ጉዳዮቹን ተረክቦ ማስተዳደር ጀመረ። ቢሮው በዚህ ሁኔታ የአመልካቾችን ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በመሰረዙ ምክንያት በስር ፍ/ቤት ክስ አቅርበው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አጣ። ይግባኝ ቢሉም አቤቱታቸው ውደቅ በመደረጉ ጉዳዩ ወደ ሰበር ችሎት አመራ። አመልካቾች በሰበር ክርክራቸው ደብተሩ ስልጣን በሌለው አካል እንደተሰረዘ በመጥቀስ የቢሮውን ተግባር ህጋዊነት ሞግተዋል።
በህግ የተቋቋመ የመንግስት መ/ቤት ስልጣን፣ መብትና ግዴታ ወደ ሌላ የሚተላለፈው ህግ አውጭው አምኖበት በአዋጅ ሲያጸድቀው ብቻ ነው። አንድ መ/ቤት በበላይ ትዕዛዝ (ያውም በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት) የሚበተን ከሆነ፣ ስልጣኑ ተቀምቶ ወደ ሌላ የሚተላለፍ ከሆነ ያኔ ህጋዊነትና ስርዓት አልበኝነት አንድ ሆነው ተዋህደዋል። የሰበር ችሎት ይህ አስደንጋጭ አውነት አልታየውም። (ወይም አልተገለጠለትም።) የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሲያጸና በሰ/መ/ቁ. 16195 ያሰፈረውን (የተሳሳተ) ትንተና በመድገም ነገሩን በአጭሩ ቋጭቶታል። በሰ/መ/ቁ. 34665 የተለየ የተለየ ነጥብ የሚስተዋለው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጽ/ቤቱ ቦታ ተቀያይረዋል። ለንፅፅር ይረዳ ዘንድ ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ እንደሚከተለው ይነበባል።
የጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስራ የመከታተልና በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ያለው እንደመሆኑ መጠን የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር ቤቶችን የሚመለከት ጉዳይ ለአ/አበባ ስራና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲያስተላልፍ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ስራውንና ሰራተኞቹን ለቢሮው አስተላልፏል። (ሰረዝ የተጨመረ)
የህግና የፍሬ ነገር ስህተት
በአመልካች የአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ንግድና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት እና ተጠሪ ሃምሳ አለቃ ታምራት ከበደ መካከል በሰ/መ/ቁ. 81934 (የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 15) በነበረው ክርክር ተጠሪ ህጋዊ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩበት የነበረውን የመኪና ማቆሚያ ንግድ ስራ ከፀጥታና ከአካባቢ ብክለት አንጻር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው በሚል በአመልካች በመታገዱ ተጠሪ ሁከት እንዲወገድላቸው ክስ አቅርበው የአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች የንግድ ስራው በአካባቢው የጤናም ሆነ የብክለት ችግር ስለማድረሱ አመልካች በማስረጃ እንዳላስደገፈ በመጠቆም ሁከቱ እንዲወገድ ውሳኔ ሰጥተዋል። ሆኖም የሰበር ችሎት በወቅቱ ጸንቶ የነበረውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁ. 686/2002 በመጥቀስ ጉዳዩ ፍሬ ነገርን እንደሚመለከት በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች ሽሯቸዋል። በአዋጁ አንቀጽ 61 መሰረት በአስተዳደራዊ እርምጃ ላይ ቅሬታ ሲኖር በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመደበኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ሊቀርብ ይችላል። አመልካች ለእርምጃው ምክንያት የሆነውን ፍሬ ነገር ማለትም የጤና እና የብክለት ችግር መከሰቱን ከመግለጽ ውጪ ይህንን አባባሉን የሚደግፍለት ማስረጃ አላቀረበም። ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይቀርብ በግምት ላይ ብቻ ተንተርሶ መወሰን የህግ እንጂ የፍሬ ነገር ስህተት አይደለም። ማስረጃ ሳይኖር የሚወሰድ አስተዳደራዊ እርምጃ የህግ እንጂ የፍሬ ነገር ጭብጥ አያስነሳም።
በሰ/መ/ቁ. 82061x አመልካች በግብር ገማች ኮሚቴ የተወሰነበትን የግብር መጠን እና የተጨማሪ እሴት ውሳኔ ማስታወቂያ በመቃወም ያቀረበው የሰበር አቤቱታ የፍሬ ነገር ጉዳይን የሚመለከት በመሆኑ ውድቅ ተደርጎበታል። በአቤቱታው ላይ በአመልካች ከተነሱት የመከራከሪያ ነጥቦች መካከል ሁለቱ የተጠሪ ስልጣንን የሚመለከቱ ቢሆንም በችሎቱ ተዘለዋል። በመጀመሪያው አመልካች የቁርጥ ግብር ከፋይ መሆኑን በመጥቀስ ተጠሪ ግብር አስተካክሎ መወሰን የሚችለው በየአምስት ዓመቱ እንደሆነ በመጥቀስ ተከራክሯል። ሁለተኛው ደግሞ አመልካች የሚሰራው የችርቻሮ ንግድ ሆኖ ሳለ ጅምላ ነጋዴ ተብሎ ከህግ ውጭ መፈረጁን በመጥቀስ የግብር ውሳኔውን ተቃውሟል። እነዚህ ሁለት ነጥቦች በህግ ምላሽ የሚያሻቸው ቢሆንም ችሎቱ የገማች ኮሚቴ የአመልካች የገቢ መጠን በተመለከተ በወሰነው ውሳሌ ላይ ብቻ በማተኮሩ የተነሱትን የህግ ክርክሮች ተገቢውን የህግ ትርጉም ሳያሳልፍባቸው ዘሏቸዋል።
በአስተዳደራዊ ክርክር ፍሬ ነገር የሚረጋገጥበት መንገድ በይሆናል እና በግምት ሳይሆን ተቀባይነት ባላቸው የማስረጃ ዓይነቶች ነው። በአመልካች የጅማ ከተማ የአካባቢ አስተዳደር ጽ/ቤት እና ተጠሪ አቶ ሸዋረገድ አባድር መካከል በሰ/መ/ቁ. 22297y በነበረው ክርክር ተጠሪ የወራሽነት መብት ያገኘበትን የእናቱን ቤት አመልካች እንደሸጠበት በመግለጽ ሁከት እንዲወገድለት ዳኝነት ጠይቋል። አመልካችም ቤቱ በአዋጅ ቁ. 47/67 የተወረሰ በመሆኑ የተፈጠረ ሁከት የለም ሲል ተከራክሯል። የአመልካች እርምጃ የህጋዊነትን መለኪያ ያሟላ ዘንድ ቤቱ በእርግጥ መወረሱን የሚያሳይ ማስረጃ ሊያቀርብ ይገባል። በሰበር ውሳኔው ላይ እንደተዘገበው አመልካች የቤቱ ካርታ በ1954 ዓ.ም. መሰጠቱን ከመግለጽ ውጪ መወረሱን የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረበም። አንድ የመንግስት አካል በአዋጅ 47/67 ያልተወረሰ ቤት ከሸጠ ድርጊቱ ከስልጣን በላይ ስለመሆኑ ጥያቄ አያስነሳም።
የሰበር ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ስናይ በአጭሩ ‘ፍርደገምድል’ የሚባል ዓይነት ነው። ይህ ግነት ስላለመሆኑ በሐተታው ክፍል የሰፈረውን አስተያየት ማየቱ ተገቢ ነው።
አመልካች የንብረቱ ባለቤትነት ማረጋገጫ የተሰጠው አዋጅ ቁ. 47/67 ከመውጣቱ በፊት ሲሆን ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ ግን ተወርሷል በማለት ይህንኑ ሕግ መሰረት አድርጎ ላቀረበው ክርክር ተጠሪ አልተወረሰም በማለት ተከራክሯል። የቤቱ ካርታ የተሰጠበት ጊዜ እና አዋጁ የወጣበት ጊዜ እንደ መነሻ ፍሬ ነገር በመያዝ ንብረቱ የተወረሰ መሆኑን የግምት መነሻ በመስጠት አመልካች ያስረዳ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ ይህ ንብረት ያልተወረሰ መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ ማስረጃ በማቅረብ አላረጋገጠም። (ሰረዝ የተጨመረ)
ይህን ውሳኔ ፍርደገምድል የሚያደርገው ማስረጃን ከግምት ማደበላለቁ ብቻ አይደለም። አመልካች የቤቱን መወረስ ማስረዳት እንዳልቻለ የስር ፍርድ ቤቶች የደረሱበትን ድምዳሜ ሰበር ችሎቱ ሲቀይረው በህግና በህገ መንግስቱ ተመጥኖ የተሰጠውን የዳኝነት ስልጣን ገደብ አልፏል። የፍሬ ነገር ስህተት መሰረታዊ ቢሆን እንኳን በሰበር አይታረምም። ምንም እንኳን በውሳኔው ማሳረጊያ ላይ በክርክሩ የተነሳውን መሰረታዊ ጭብጥ የህግ መልክ ለማላበስ የተሞከረ ቢሆንም ሙከራው አሳማኝት ርቆታል። ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ፈጽሟል በማለት የተቸው በሚከተለው መልኩ ነበር።
…ንብረቱ ተወርሷል ወይስ አልተወረሰም የሚለውን ነጥብ በሚመለከት ማን ክርክሩን መጀመርና ማስረዳት እንዳለበት የሚያመለክተውን ድንጋጌ ባለመከተል እና ይህ ስርዓት ቢዛነፍም እንኳ ከግራ ቀኙ ማን የተሻለ ማስረጃ አቅርቧል የሚለውን ነጥብ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል።
በግለሰብና በመንግስት መካከል በሚካሄድ ክርክር ግለሰቡ ማስረዳት የሚጠበቅበት መብትና ጥቅሙን የሚጎዳ ተግባር እንደተፈጸመበት ብቻ ነው። ለምሳሌ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰረዘበት ነጋዴ የመሰረዝ ተግባር መፈጸሙን ማስረዳት ይኖርበታል። ለስረዛው ምክንያት የሆኑትን ፍሬ ነገሮች ማስረዳት እርምጃውን የወሰደው አካል ግዴታ ነው። ‘ህገ ወጥ እርምጃ ተወሰደብኝ’ በሚል አቤቱታ ሲቀርብ ውሳኔውን ያስተላለፈው አካል በህጉ አግባብ የተባለውን እርምጀ ለመውሰድ ስልጣን እንደተሰጠው፣ እርምጃውም በህግ በተደነገገ በቂ ምክንያት መሆኑንና ይህም በማስረጃ መረጋገጡን ካላስረዳ በቀር እርምጃው ህጋዊ መሰረት ያጣል።
ምንም ዓይነት ደጋፊ ማስረጃ በሌለበት የህጉን ድንጋጌ መጥቀስ ብቻውን የህጋዊነት መስፈርትን አያሟላም። ይህ አንደኛው የህግ ስህተት የሚገለጽበት መንገድ ነው። ሁለተኛው ዓይነት የህግ ስህተት ደግሞ የዚህ ግልባጭ ገጽታ ነው። በመጀመሪያው ለህጉ ተፈጻሚነት ቅድመ ሁኔታ የሆነው ፍሬ ነገር የለም። በሁለተኛው ደግሞ ፍሬ ነገሩ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የህግ ቅድመ ሁኔታ የለም። ፍሬ ነገሩ በማስረጃ ተረጋግጧል ወይም ደግሞ በፍሬ ነገሩ ላይ አከራካሪ ጭብጥ የለም። ሆኖም ከፍሬ ነገሩ የሚነሳው ድምዳሜ የህጉ ቅድመ ሁኔታ ላይ አያደርስም። ለምሳሌ ፈቃድ በተሰጠው ጠበቃ ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ሊወሰድ የሚችለው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁ. 199/1992 ወይም በአዋጁ መሰረት የሚወጣውን ስነ ምግባር ደንብ ወይም መመሪያ ተላልፎ ሲገኝ ነው።z በጠበቃው የተፈጸመው ድርጊት በማስረጃ የተረጋገጠ ወይም ክርክር ያልተነሳበት ከሆነ የጠበቆች ዲሲፕሊን ጉባዔ ድርጊቱ የስነ ምግባር ጥሰት ሊባል የሚችል ስለመሆኑ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይኖርበታል። ጉባዔው ድርጊቱን ከህጉ ጋር ሲያዛምድ በባህርዩ የስነ ምግባር ግድፈት ያልሆነውን ድርጊት እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር የቅጣት ሀሳብ ቢያስተላልፍና ይህም በጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ቢጸድቅ የህግ ስህተት ነው።
በሰ/መ/ቁ. 84446a አመልካች ጠበቃ ሆኖ በተወከለበት መዝገብ በፍርድ ያለቀውን ጉዳይ የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 5 ከሚያዘው ውጪ አቤቱታ አቅርቦ የተለየ ዳኝነት እንዲሰጥ አድርጓል በሚል በገንዘብ እንዲቀጣ ተወስኖበት ይግባኝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። የጉዳዩ አመጣጥ እንደሚያሳየው በዋናው መዝገብ ላይ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ከተቻለ በዓይነት ካልተቻለ ንብረት በሐራጅ ተሸጦ በድርሻ ልክ ክፍፍል እንዲደረግ ፍርድ ተሰጥቶ ፍርዱን ለማስፈጸም የአፈጻጸም መዝገብ ተከፍቷል። አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት ንብረቱ በዓይነት ሊከፋፈል የሚቻል ስለመሆኑ አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ ለፍርድ አፈጻጸም መምሪያ ትዕዛዝ ሰጥቶ መምሪያው ንብረቱ በዓይነት ሊካፈል እንደሚችል ሆኖም ከአተማመን አኳያ እኩል ማካፈል እንደማይቻል በገለጸው መሰረት ንብረቱ በሐራጅ እንዲሸጥ የአፈጻጸም ትዕዛዝ ሰጥቷል። በትዕዛዙም ላይ ይግባኝ ቀርቦ ፀንቷል። ከዚህ ሂደት በኋላ አመልካች ደንበኛውን በመወከል ባቀረበው አቤቱታ ተጎጂ ቢሆኑም ንብረቱ በሐራጅ ከሚሸጥ ይልቅ አነስተኛው ድርሻ በዓይነት እንዲሰጣቸው ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ ትእዛዝ ሰጥቷል። አመልካች ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣው ባቀረበው አቤቱታ መነሻነት ሲሆን ጥፋቱም በፍርድ ያለቀውን ጉዳይ ከፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 5 ውጪ እያወቀ አዲስ አቤቱታ በማቅረብ ዳኝነት እንዲሰጥ በማድረጉ የሙያ ስነ ምግባር ጉድለት ፈጽሟል የሚል ነው።
የሰበር ችሎት የስር ፍርድ ቤትንና የሚኒስትሩን ውሳኔ ሲሽር እንዳመለከተው ከአመልካች አቤቱታ አንጻር የፍርድ አፈጻጸም መምሪያ ሪፖርት አንደኛው ወገን ያነሰ ድርሻ ወስዶ ተጎጂ ካልሆነ በቀር ክፍፍሉ እኩል በእኩል ሊፈጸም እንደማይችል የሚገልጽ በመሆኑ ፍርዱን ተገቢ በሆነ መንገድ በማስፈጸም ረገድ ፍርድ ቤቱ በተሰጠው ስልጣን የተስተካከለ ዳኝነት እንዲሰጥ አመልካች ያቀረበው ጥያቄ ለደንበኛው ተገቢውን ድጋፍ የመስጠት ግዴታውን መወጣቱን ከሚያሳይ በቀር የሙያ ስነ ምግባር ጥሰት ሊባል አይችልም።
የዳኝነት ስልጣን ስህተት
መደበኛ ፍርድ ቤት ሆነ የአስተዳደር ጉባዔ ዳኝነት መስጠት የሚችሉት በህግ በተቀመጠላቸው የስልጣን ክልል ውስጥ ብቻ ነው። ውሳኔ ያሳረፉበት ጉዳይ በስልጣቸው ስር የማይወድቅ ከሆነ የዳኝነት ስልጣን ስህተት ፈጽመዋል። ከስልጣን በላይ ድርጊት (ultraviers act) እና የዳኝነት ስልጣን ስህተት (jurisdictional error) የይዘት ባይሆንም የቅርጽ ልዩነት እንዳላቸው ልብ ይሏል። ስልጣን (power) የሚለው ቃል የሚቆራኘው ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ጋር ሲሆን ቃሉ ለፍርድ ቤት ወይም ለአስተዳደር ፍርድ ቤት ጥቅም ላይ ሲውል የዳኝነት ስልጣንን (jurisdiction) ይወክላል። ስለሆነም ከስልጣን በላይ (Ultra vires) የሚለው ቃል ከስልጣን በላይ የሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲያመለክት የዳኝነት ስልጣን ስህተት (jurisdictional error) ደግሞ ከዳኝነት ስልጣን ውጭ በመደበኛ ፍርድ ቤት ወይም በአስተዳደር ጉባዔ የተሰጠ ፍርድ ወይም ውሳኔን ያመለክታል።
የዳኝነት ስልጣን ስህተት በሁለት መልኩ ይገለጻል፤ በህግ እና በፍሬ ነገር። መደበኛ ፍርድ ቤት ሆነ የአስተዳደር ጉባዔ በዳኝነት ስልጣኑ አይቶ መወሰን ከሚችላቸው ጉዳዮች ውጪ አከራክሮ ከወሰነ በዳኝነት ስልጣኑ ላይ የህግ ስህተት (jurisdictional error of law) ሰርቷል። ይህ አይነቱ ስህተት በቀጥታ የማቋቋሚያ አዋጁን በማመሳከር ይለያል።
ለምሳሌ በአሠሪና ሠራኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156/2011 መሰረት በመደበኛ ፍርድ ቤት እና በአሰሪና በሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቁ የስራ ክርክሮች ተለይተዋል። ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ቦርዱ በዲሲፕሊን ምክንያት የተባረረ ሰራተኛ የሚያቀርበውን ክስ የማየት የዳኝነት ስልጣን የለውም። በተጨማሪም የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ለጡረታ መብት ብቁ መሆን ያለመሆናቸውን አይቶ ለመወሰን የሚያስችለው የዳኝነት ስልጣን አልተሰጠውም።b
ሁለተኛው ዓይነት የዳኝነት ስልጣን ስህተት በፍሬ ነገር ረገድ የተፈፀመ የዳኝነት ስህተት (jurisdictional error of fact) ተብሎ ይጠራል። የአስተዳደር ጉባዔ የዳኝነት ስልጣኑን ሲወስን የስልጣኑ ቅድመ ሁኔታ በሆኑት ፍሬ ነገሮች ላይ ስህተት ከሰራ በዳኝነት ስልጣኑም ላይ ስህተት ይሰራል። የፍሬ ነገር ጥያቄው ከህግ ጥያቄው ሙሉ በሙሉ የተለየ አይደለም። የአስተዳደር ጉባዔ በቀረበለት ጉዳይ ላይ ዳኝነት እንዳለውና እንደሌለው የመወሰን ስልጣን ቢኖረውም እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት የፍሬ ነገር ድምዳሜ የተሳሳተ ከሆነ በህጉ የተሰመረለት የስልጣን ገደብ ላይም ስህተት ይሰራል።
ለምሳሌ በአዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 143(1) ሸ መሰረት የሰራተኞች ቅነሳን የሚመለከት ጉዳይ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ስልጣን ስር ይወድቃል። እንበልና አንድ ድርጅት ምርታማነቱን ለማሳደግ በማሰብ ባደረገው የመዋቅር ለውጥ ሠራተኞቹን በአዲስ መልክ ሲደለድል ወደ 20 የሚጠጉ ሠራተኞች ድልድሉን በመቃወም ረብሻ በማንሳት ከዚያም አልፈው በድርጅቱ ንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት በማድረሳቸው ካለማስጠንቀቂያ አሰናበታቸው። እነሱም አለአግባብ ከስራ እንደተቀነሱ በመግለጽ ለቦርዱ ክስ አቀረቡ። ቦርዱ የዳኝነት ስልጣንን አስመልክቶ ለቀረበለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ብይን ሲሰጥ የድርጅቱ እርምጃ በአዋጅ ቁ. 1156/2012 አንቀጽ 28/3/ ሐ የተደረገ ቅነሳ እንደሆነ በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት መቃወሚያውን ውድቅ አደረገው። ይሁን እንጂ የሠራተኞቹ ስንብት መነሻው የመዋቅር ለውጥ ቢሆንም የስንብቱ ምክንያት ግን ረብሻ ማስነሳትና በድርጅቱ ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ነው። ቦርዱ በፍሬ ነገሩ ላይ ስህተት በመስራቱ ስልጣኑን በተመለከተ የደረሰበት ድምዳሜ እንዲሁ የተሳሳተ ሆኗል።
ግዴታን አለመወጣት
ህጋዊ ግዴታ የተጣለበት አካል በቸልተኝነትና በንዝልልነት አሊያም ሆነ ብሎ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ግዴታውን ለመፈፀም ፍቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ዜጋው በእርግጥም የአስተዳደር በደል ደርሶበታል። ግዴታውን ያልተወጣው አካል ተገዶ ግዴታውን እንዲፈጽም በማድረግ በደል ለደረሰበት ወገን ፍትህ ማጎናፀፍ የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት ነው። የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት ሕገ መንግስቱን የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት በህግ አውጭና ህግ አስፈፃሚው እንዲሁም በዳኝነት አካላት ላይ ይጥላል። በህገ-መንግስቱ ላይ የተመለከቱት መብቶችና ነፃነቶች በአስተዳደራዊ ድርጊት ብቻ ሳይሆን ግዴታን ባለመወጣት በሚፈፀም በደል ምክንያት እንዳይጣሱና እንዳይገረሰሱ በመጠበቅ ፍርድ ቤቶች ህገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን ሊወጡ የሚችሉት ህገወጡን ድርጊት ሲሰርዙ (ሲሽሩ) እንዲሁም ግዴታውን ያልተወጣውን አካል ማስገደድ ሲችሉ ብቻ ነው።
አንድ የአስተዳደር መስሪያ ቤት ግዴታውን አልተወጣም ተብሎ ከመወቀሱና ፍርድ ቤቱም የማስገደጃ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት መስሪያ ቤቱ ከህግ የመነጨ ግዴታ እንዳለበትና ግዴታው ለአመልካቹ በቀጥታ የሚፈጸም መሆኑ መረጋገጥ የሚኖርባቸው ፍሬ ነገሮች ናቸው። ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል እንበልና የአንድ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት (ስም) የማዛወር እና ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ ተጥሎበታል። ስም የማዛወር ግዴታ በህግ የተቀመጠ ግዴታ ከመሆኑም በላይ ለአመልካቹ በቀጥታ የሚፈፀም ስለሆነ ስም ለማዛወር የሚያበቁ ህጋዊ ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ ማዘጋጃ ቤቱ ዝውውሩን ሊያከናውን ይገደዳል። ፈቃደኛ ሳይሆን ከቀረ ግን በፍርድ ቤት አስገዳጅነት ስም ማዛወር ይኖርበታል። በሰ/መ/ቁ. 91622c አንደኛውን ተከራካሪ ባለመብት የሚያደርግ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ በስሙ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት አካል ውሳኔ ያረፈበትን ቤት በሌላ ሰው ስም እንደተመዘገበ በመግለጽ ከግዴታው ሊያመልጥ እንደማይችል ችሎቱ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።
ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ እንደ መጀመሪያው ለአንድ ግለሰብ የተሰጠ ሳይሆን ህዝባዊ ግዴታ (public duty) ነው። ስለሆነም በግዴታው አለመወጣት መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ወገን ግዴታው እንዲፈጸምለት በፍርድ መጠየቅ አይችልም። አጣሪ ዳኝነት ሆነ የህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ክስ (Public interest litigation) ብዙም ባልተለመደበት በአገራችን ህዝባዊ ግዴታን ማስፈጸም በባህርዩ አስቸጋሪ የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከተማ ለማጽዳት ማዘጋጃ ቤቱ በቂ የሰው ኃይል መቅጠር፣ የደረቅ ፍሳሽ ማስወገጃ መኪኖችን መግዛት ወዘተ…ይጠበቅበታል። ይህን ለማድረግ በቂ በጀት ካልተመደበለት የፍርድ ማስገደጃ ትዕዛዝ ተግባራዊ ፋይዳ አይኖረውም።
ከላይ ከተጠቀሱት የግዴታ ባህሪያት በተጨማሪ የሚፈጸመው ግዴታ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ወይም ሊሟሉ የሚገባቸውን ፍሬ ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ላይ የመድረስ ፈቃደ ስልጣን (discretion) የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። በህጉ መሰረት የንግድ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ ያለበት አካል ግዴታው የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥና ውሳኔ ላይ መድረስ ብቻ ነው። ማመልከቻ ቀርቦለት መርምሮ ተገቢ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ማመልከቻውን አይቶ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ በፍርድ ሊገደድ ይችላል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ከዚህ አልፎ ራሱን በፈቃድ ሰጪው አካል ቦታ በመተካት የማመልከቻውን ትክክለኛነት መርምሮ ለአመልካቹ ፈቃድ እንዲሰጠው የማስገደጃ ትዕዛዝ ከመስጠት መቆጠብ አለበት።
የስነ ስርዓት ጉድለት
የአስተዳደር ህግ ከይዘት (ውሳኔ) ይልቅ በስነ-ስርዓት (የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት) ላይ የሚያተኩር የህግ ክፍል ስለመሆኑ ከዚህ በፊት ተገልጿል። የውሳኔ አሰጣጥ ፍትሐዊነት ሲረጋገጥ የአስተዳደር ፍትህ ይሰፍናል።
ህግ አውጭው አንድ ድርጊት ከመፈጸሙ ወይም ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ወይም ስነ-ስርዓቶች በግልጽ ከደነገገ በስልጣኑ ተጠቅሞ እርምጃ የሚወስድ አካል መሟላታቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። በህግ የተደነገገ የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ፍርድ ቤቶች ሆኑ ውሳኔ ሰጪዎች ሊከተሉት የሚገባ አስገዳጅ ደንብ ነው። ከዚህ በተቃራኒ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት ውሳኔ በህግ ፊት ዋጋ ወይም ውጤት ሊኖረው አይገባም።
በእንግሊዝ፣ አሜሪካና የእነሱን የህግ ስርዓት በሚከተሉ አገራት የሚገኙ ፍ/ቤቶች በግልጽ ከሚደነገገው የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ውጭ የግለሰብን መብትና ጥቅም ሊነካ የሚችል ዳኝነታዊ ባህርይ ያለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በህግ ባይቀመጥም እንኳን ፍትሐዊ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መርሆዎችን ተፈፃሚ ያደርጋሉ። ስለሆነም ስልጣን በሰጠው አዋጅ ላይ ባይጠቀስም በአስተዳደራዊ ውሳኔ መብቱ የሚነካ ወገን ከውሳኔው በፊት ራሱን የመከላከል ዕድል ሊሰጠው ይገባል። ውሳኔ ሰጪውም በተከራካሪዎች የቀረበውን ማስረጃና ህጉን መሰረት አድርጎ ያለ አድልዎ ገለልተኛ ሆኖ ፍትሐዊ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል። የገንዘብ፣ በዝምድና አሊያም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ነገር ግምት ውስጥ ገብቶ የተሰጠ ውሳኔ የተዛባና በህግ ፊት ዋጋ የሌለው ውሳኔ ነው።
በስልጣን አለአግባብ መገልገል
‘የስልጣን አላግባብ መገልገል’ ቃሉ እንደሚያመለክተው በህግ አውጭው በግልጽ የተቀመጠ የስልጣን ገደብ በማለፍ የሚፈፀም ድርጊት ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔ አይደለም። ድርጊቱ ወይም ውሳኔው በስልጣን ገደብ ውስጥ ይወድቃል። ሆኖም ሚዛናዊነት ከጎደለው፣ ከተፈፀመው ጥፋት አንጻር ፈጽሞ ተመጣጣኝ ካልሆነ፣ በየትኛውም መለኪያ ኢ-ምክንያታዊ ከሆነ፣ አግባብነት የሌለውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ወይም አግባብነት ያለውን ፍሬ ነገር በመተው የተሰጠ ከሆነ እንዲሁም በህጉ ከተቀመጠው ዓላማ ውጪ የተሠጠ ከሆነ ስልጣን አለአግባብ አገልግሎት ላይ ውሏል።
ፍርድ ቤቶች ግልጽ ከሆነው የስልጣን ገደብ በተጨማሪ በተወሰኑ ምክንያቶች ግምት የሚወሰድበት የስልጣን ገደብ (implied limits) ያሰምራሉ። ከዚህ አንጻር የስልጣን አላግባብ መገልገል ፍርድ ቤቱ በሚወስናቸው ምክንያቶች የስልጣን አጠቃቀሙ የህጋዊነት መርህን በመጣሱ የተነሳ ድርጊቱ ወይም ውሳኔው የሚሰረዝበት ወይም ዋጋ አልባ የሚደረግበት ሁኔታ ነው። አግባብነት የሚወሰነው የህግ አውጭውን ሃሳብ መሰረት በማድረግ ነው። በተለይ በእንግሊዝ ይህ አስተሳሰብ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። ህግ አውጭው ለአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣን ሲሰጥ ስልጣኑ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ማለትም ኢ-ሚዛናዊ በሆነ መልኩ፣ ተገቢ ላልሆነ ዓላማ ወይም ተመጣጣኝነት በሌለው መልኩ ተግባር ላይ እንዲውል በማሰብ አይደለም። በሌላ አነጋገር የህግ አውጭው ሃሳብ ስልጣኑ አግባብ በሆነ መልኩ ግልጋሎት ላይ እንደሚውል በማሰብ ነው።
በስልጣን አላግባብ መገልገል ስር የሚወድቁ ምክንያቶች በተለያዩ አገራት በተለያየ ስያሜ ይጠራሉ። በዋናነት የሚታወቁት ግን የሚከተሉት ናቸው።
ኢ-ሚዛናዊነት (Unreasonableness)
ተገቢ ያልሆነ ዓላማ (Improper Purpose)
ተገቢ የሆኑና ያልሆኑ ሁኔታዎች (Relevant and Irrelevant Considerations)
ተመጣጣኝነት (proportionality)
ኢ-ሚዛናዊነት
የስልጣን አጠቃቀምን አላግባብ ከሚያሰኙት ምክንያቶች አንዱ ኢ-ሚዛናዊነት ነው። ያም ሆነ ግን ወጥና ግልጽነት ባለው መልኩ ትርጓሜና አፈፃፀሙን መወሰን ለፍርድ ቤቶች አስቸጋሪ ስራ ነው። ሎርድ ሃሪሻም የተባሉ ዳኛ የሚዛናዊነት መስፈርትን አስመልክቶ በሰጡት አንድ ፍርድ ላይ አስቸጋሪነቱን በእንዲህ መልኩ ገልፀውት ነበር።
ሁለት አመዛዛኝ ሰዎች የአመዛዛኝት ማዕረጋቸውን ሳይነጠቁ ተመሳሳይ በሆኑ ፍሬ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ላይ ተቃራኒ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።
የኢ-ሚዛናዊነት ጽንሰ ሀሳብ ህሊናዊ (subjective) መሆኑ ለአፈፃፀሙ አስቸጋሪነት ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ ባህርዩ የተነሳ አንድን ድርጊት ወይም ውሳኔ ኢ-ሚዛናዊ ብሎ ለመፈረጅ በተለያዩ ዳኞች የተለያየ ድምዳሜ ላይ መደረሱ አይቀርም። መጥፎ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም እንኳን ከስልጣን በላይ ተብሎ ሊሰረዝ አይችልም። አንድን ውሳኔ በሚዛናዊነት መስፈርት መመርመር በከፊል ይዘቱን ወይም የውሳኔውም ትክክለኛነት መመርመርን ያስከትላል።d ይህም ዳኞች በውሳኔ ሰጪው ቦታ ተተክተው በራሳቸው አቋምና እምነት መሰረት በፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ እንዲወስኑ በር ይከፍታል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተከሰተ ደግሞ የስልጣን ክፍፍል መርህ ይጣሳል፤ በፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ውጤታማ አስተዳደር ይሰናክላል።
በዚህ የተነሳ ኢ-ሚዛናዊነት የስልጣን አለአግባብ መለኪያ በመሆን ተቀባይነት ያገኘው በጣም በጠባብ ሁኔታዎች ብቻ ነው። ይህ አይነቱ ኢ-ሚዛናዊነት በተለይ በእንግሊዝና በአውስትራሊያ ‘የዌንስበሪ ኢ-ሚዛናዊነት’ (Wendensebery Unreasonableness) የሚል ቅጽል ስያሜ ሲኖረው በአሁኑ ወቅት በአስተዳደር ህግ ባለሙያዎች ዘንድ ከአፍ የማይጠፋ ተጠቃሽ ቃል ሆኗል። ይህ መለኪያ የዳበረው ‘በ’ Associated Provincial Picture Houses እና Wednesbury Corporation መካከል በነበረው ጉዳይ ሲሆን ኢ-ሚዛናዊ ተብሎ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ የሲኒማ ቤት ፈቃድ የሚሰጠው የዌንስበሪ ኮርፖሬሽን ፈቃድ ለማግኘት ከ15 ዓመት በታች የሆናቸው ህፃናት ዕሁድ ቀን ወደ ሲኒማ ቤት እንዳይገቡ የሚከለክል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጡ ነበር። ዳኛ ሎርድ ግሪን (Lord Green) በዚህ ጉዳይ የሰጡት ውሳኔ አሁንም ድረስ የኢ-ሚዛናዊነት መለኪያ ተደርጎ ይወዳል። እንደ እሳቸው አባባል አንድ ውሳኔ ኢ-ሚዛናዊ ተብሎ ሊፈረጅ የሚችለው ውሳኔው ሲበዛ ኢ-ሚዛናዊ ከመሆኑ የተነሳ አንድ አመዛዛኝ ባለስልጣን እንዲህ አይነቱ ውሳኔ ላይ አይደርስም ተብሎ ሲገመት ነው።e
የሚዛናዊ ባለስልጣን መለኪያ ሚዛናዊነትን ከኢ-ሚዛናዊነት በጠራ መልኩ ለመለየት አይረዳም። የመስመሩ አለመጥራት በአስተደደሩ ውስጥ የዳኞች ጣልቃ ገብነት ማስከተሉ አይቀሬ ነው። በመለኪያው መሰረት ዳኛው ሚዛናዊ የተባለ ባለስልጣን ምን እንደሚያስብ የመወሰን ሰፊ ስልጣን ያገኛል። ስለሆነም የዚህ መርህ አፈፃፀም አንድ ጤነኛ አስተዳደር ፈጽሞ ይህን መሰሉን ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም ተብሎ በሚገመትባቸው በጣም ከልክ በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተገደበ ነው።
የዓላማ ተገቢነት
ስልጣን ሲሰጥ ስልጣን ሰጪው ሊያሳካ የፈለገው ዓላማ አለው። ሁሉም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በህግ ስልጣን የሚሰጣቸው የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲያውሉት ነው። ይህ ጥቅል አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዱ መ/ቤት ስልጣኑን እንደሚያስፈጽመው ህግና ፖሊሲ በማቋቋሚያ አዋጁ ወይም በሌላ ህግ ተለይቶ የተቀመጠለትን ዓላማ ለማሳካት ብቻ ሊገለገልበት ይገባል። ለመሆኑ ስልጣን ተገቢ ላልሆነ ዓላማ ውሏል የሚባለው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ነው? በሰ/መ/ቁ. 54697f ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ፍሬ ነገሮች ለጥያቄው በከፊል ምላሽ ይሰጡናል።
ድንቅ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለ ድርጅት ስፋቱ 1194 ካ.ሜ የሆነ ቦታ ላይ ሕንፃ ለመስራት ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት ጋር የሊዝ ውል ፈርሞ ቦታውን በመረከብ ስራ ከጀመረ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ባለስልጣን ‘ለህዝብ ጥቅም’ ሲባል ቦታውን ሌላ ግለሰብ እንዲወስዱና ድርጅቱ ቦታውን መልሶ እንዲያስረክብ ውሳኔ አስተላለፈ። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ድርጅቱ በተረከበው ቦታ ላይ ህንጻ ቢገነባ በስተጀርባ የሚገኘውና መሬቱን ይውሰዱ የተባሉት ግለሰብ ንብረት የሆነውን ሆቴል ስለሚጋርደው በሆቴል ስራቸው ላይ እንቅፋት ይፈጥራል በሚል ነው። በወቅቱ ፀንቶ በነበረው የሊዝ አዋጅ ቁ. 272/1994g አንቀጽ 2/7/ መሰረት የህዝብ ጥቅም ማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ህዝቦች በመሬት ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የከተማ ልማትን በቀጣይነት ለማጎልበት አግባብ ያለው አካል በመሪ ፕላን ወይም በልማት እቅድ የሕዝብ ጥቅም ብሎ የሚወስነው ነው።
የአንቀጽ 2/7/ ድንጋጌ በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ውስጥ ቢገኝም በይዘቱ ግን የህግ ትርጓሜ (Statutory Definition) አይደለም። ምክንያቱም ድንጋጌው የህዝብ ጥቅም ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አይመልስም። ጥያቄው ‘አግባብ ያለው አካል’ በፈቀደ ስልጣኑ (Discretionary Power) እንዲመልሰው ለዚሁ አካል ተትቷል። በመርህ ደረጃ ይህ አካል ‘የህዝብ ጥቅም’ ብሎ የፈረጀው ሁሉ የህዝብ ጥቅም ይሆናል። ከዚህ አንጻር ስልጣኑ ገደብ-የለሽ ይመስላል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ባለስልጣን ‘ለህዝብ ጥቅም’ ብሎ የፈረጀው ውሳኔ በማናቸውም መለኪያ በትርጓሜው ውስጥ እንደማይወድቅ ግልጽ ነው። በህጋዊ መንገድ በሊዝ የተሰጠ ቦታ ቀምቶ ለሌላ የግል ባለሀብት ማስተላለፍ የአዋጅ ቁ. 272/1994 ዓላማ አይደለም። ስለሆነም ባለስልጣኑ ከህዝብ ይልቅ የግለሰብ ጥቅምን በማስቀደም ስልጣኑን ተገቢ ላልሆነ ዓላማ (ከህጉ ዓላማ ውጪ) አለአግባብ ተገልግሎበታል።
በተመሳሳይ መልኩ በሰ/መ/ቁ. 54596h አመልካች በሊዝ ተመርተው የተረከቡትን ቦታ እንዲመልሱ ለሊዝ ቦርድ አቤቱታ ቀርቦ ቦርዱ የሊዝ ውሉ ሊሰረዝ እንደማይገባ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና የፍትሕ ሚኒስቴር (በአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ) ድጋሚ ለቦርዱ አቤቱታ በማቅረባቸው ለህዝብ ጥቅም በሚል ቦታው ለመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እንዲሰጥና ከተጠሪ ጋር የተደረገው የሊዝ ውል እንዲሰረዝ ወስኗል። ከዚህ ውሳኔ በፊት ከቦታው ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎበት ተጠሪ የፍርድ ባለመብት ሆነዋል። አመልካች ለድርጊቱ ህጋዊነት በወቅቱ ፀንቶ የነበረውን አዋጅ ቁ. 272/1994 በመጥቀስ እርምጃው ለህዝብ ጥቅም እንደተወሰደ ቢከራከርም በስር ፍ/ቤቶችና በሰበር ችሎት ተቀባይነት አላገኘም።
‘ተገቢ ያልሆነ ዓላማ’ ሲባል አንድ አስተዳደራዊ ድርጊት ወይም ውሳኔ ህግ አውጭው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ካስቀመጠው ዓላማ ውጪ መሆኑን ያሳያል። ከህግ የመነጨ ስልጣን በህጉ ለተገለጸው ዓላማ ብቻ መዋል አለበት። የህጉ ዓላማ በህጉ መግቢያ አንቀጽ (preamble) ወይም ዓላማውን በሚያትተው ድንጋጌ (objective clause) በግልጽ ወይም አመላካች በሆነ አነጋገር ይገለጻል። ዓላማውን የሚጠቁም ግልጽ ወይም አመላካች ድንጋጌ በማይኖርበት ጊዜ ዳኞች የህጉን መንፈስና ይዘት እንዲሁም የህግ አውጭውን ሀሳብ መሰረት ባደረገ አተረጓጎም መወሰን ይጠበቅባቸዋል።
የዓላማ ተገቢነት በተለይ በፈረንሳይ አስተዳደር ህግ ውስጥ ራሱን እንደቻለ የምርመራ ምክንያት ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። በፈረንሳይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የአስተዳደሩን ተግባራት መሞገት የሚቻልባቸው በቂ ምክንያቶች ከስልጣን በላይ እና የስነ-ስርዓት ጉድለት ነበሩ።i ሆኖም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ የበላይ የአስተዳር ፍርድ ቤት የሆነው ኮንሲል ዴታ (Conseil d'Etat) ህዝባዊ ስልጣን ለህዝብ ጥቅምና ለህጉ ዓላማ ማስፈጸሚያ ብቻ መዋል እንዳለበት በማስረገጥ ጠንካራ አቋም እየያዘ በመምጣቱ አለአግባብ በስልጣን በመገልገል የሚፈጸሙ ተግባራት በህግ የቁጥጥር ማዕቀፍ ስር እንዲወድቁ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚህም የዓላማ ተገቢነት የስልጣን መገልገል አግባብነት መለኪያ ሊሆን በቅቷል።j
አልፎ አልፎ ስልጣን ህጋዊ ግን ተገቢ ላልሆነ ዓላማ ብቻ የግል ጥቅምን ለማሳደድ፣ ድብቅ አጀንዳን ለማራመድ፣ እምነት በማጉደል አላግባብ ለመበልጸግ እንዲሁም ሌላውን ሰው ሆነ ብሎ ለመጉዳት በአጠቃላይ ለህገ-ወጥ ዓላማ ማሳኪያ መሳሪያ ሆኖ ግልጋሎት ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ይኖራል። ስለሆነም አንድ የመንግስት ባለስልጣን በዚህ መልኩ ስልጣኑን በክፉ ልቦና ተግባር ላይ ካዋለ ወይም ለግል ጥቅም ማስኬጃ ከተጠቀመበት ድርጊቱና የህጉ ዓላማ ስለማይጣጣሙ በህግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። ይሁን እንጂ የውሳኔ ሰጪውን ስነ-ልቦናዊ አቋም ወይም ድብቅ ሀሳብ (motive) በማስረጃ ለማረጋገጥ ፈታኝ በመሆኑ የህጉን ዓላማ ከውሳኔ ሰጪው ድብቅ ዓላማ ጋር በማነጻጸር የዓላማ ተገቢነትን መወሰን ከባድና አንዳንዴም የማይቻል ነው።
በአንዳንድ አገራት በክፉ ልቦና (Bad Faith) የተሰጠ ውሳኔ ተገቢ ባልሆነ ዓላማ ስር ሳይጠቃለል ራሱን የቻለ የአጣሪ ዳኝነት የምርመራ ምክንያት ሆኖ ይቆማል። ሆኖም በሁለቱ መካከል ልዩነት መፍጠሩ ከአደናጋሪነቱ በስተቀር ፋይዳው እምብዛም ነው። ለምሳሌ ሆነ ብሎ አንድን ግለሰብ ለመጉዳት በማሰብ የተሰጠ አስተዳዳራዊ ውሳኔ በክፉ ልቦና የተሰጠ ውሳኔ ነው። በሌላ መልኩ ካየነው ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ከህጉ ዓላማ ውጭ ነው። በሁለቱም አካሄድ ዞሮ ዞሮ ተመሳሳይ አቋም ላይ መደረሱ አይቀርም።
የሁኔታ ተገቢነት
ለአስተዳደራዊ ውሳኔ መሰጠት በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጡ በህግ የተዘረዘሩ ሁኔታዎች ሲኖሩና ውሳኔ ሰጪው አካል በውሳኔ አሰጣጡ ሂደት ሁኔታዎቹን ግምት ውስጥ ማስገባት ኖሮበት ሳያስገባ ከቀረ ሁኔታዎቹን ከግምት ባለማስገባት የሰጠው ውሳኔ የስልጣን አላግባብ መገልገል ተብሎ በፍርድ ይሻራል። በተመሳሳይ መልኩ ተገቢ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ከግምት በማስባት የተሰጠ ውሳኔ በህግ ፊት ዋጋ አይኖረውም። ተገቢነትን መሰረት ባደረገ ምክንያት የስልጣን አላግባብ መገልገል መፈፀሙን ለማረጋገጥ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ተገቢነትን ለጉዳዩ አወሳሰን ፋይዳ ካላቸው የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ማዛመድና ማስተያየት ያስፈልጋል።
ተገቢ ሁኔታዎች በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ከግምት ውስጥ አልገቡም ብሎ ለመከራከር ሁኔታዎቹ በህጉ በዝርዝር መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን ውሳኔ ሰጪው ግምት ውስጥ የማስባት ግዴታ እንዳለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ማንኛውንም አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በሚወስንበት ጊዜ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ የህግ ግዴታ ተጥሎበታል።k እነዚህም፤
የጥፋቱን ባህርይ፣ የተፈጸመበትን ከባቢያዊ ሁኔታ፣ ያስከተለው ውጤት መጠንና አስከፊነት
ጥፋቱን የፈጸመው ሰው የጥፋተኝነት ደረጃና ቀደም ሲል የፈጸማቻ ጥፋቶቸ ታሪክ
የገንዘብ መቀጮን የሚመለከት ሲሆን የአጥፊውን የመክፈል ችሎታና ስራውን ለመቀጠል ባለው ችሎታ ላይ የሚያስከትልበትን ተጽዕኖ
ሌሎች ከፍትህ አንጻር መታየት ያለባቸው ሁኔታዎች
ከዝርዝሮቹ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ አስገዳጅነት ባለው መልኩ የተቀመጡ እንደመሆኑ በባለስልጣኑ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በዝምታ ሊታለፉ አይገባም። ሆኖም ከፍትህ አንጻር መታየት ያለባቸው ሁኔታዎች ባለስልጣኑ ለፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ ይረዳሉ ብሎ የሚያምንባቸውና የሚቀበላቸው ጉዳዮች ናቸው። የህጉ አቀራረጽ ለባለስልጣኑ ጠቅለል ያለ መመሪያ ከመስጠት ባሻገር ልዩ ግዴታ አይጥልም። ሆኖም ተገቢነታቸው በባለስልጣኑ የታመነባቸው ሁኔታዎች በህግ ተቀባይነት የሚኖራቸው ‘ከፍትህ አንጻር’ የተቃኙ ከሆነ ብቻ ነው። ከፍትሐዊነት ጋር ተዛማጅነት የሌላቸው ጉዳዮች በአስተዳደራዊ እርምጃው ላይ ታሳቢ ከተደረጉ ግልጽ የሆነ በስልጣን አለአግባብ መገልገል እንደመሆኑ እርምጃው የህጋዊነት ሆነ የፍትሐዊነት መለኪያን አያሟም።
አንዳንድ ጊዜ ህጉ ግምት ውስጥ መግባት የሌለባቸውን ሁኔታዎች ጭምር ይዘረዝራል። በጉምሩክ አዋጅ ቁ. 859/2006 አንቀጽ 105 የዕቃዎች የስሪት አገር ለመወሰን ግምት ውስጥ መግባት ከሌለባቸው ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
በምርት ማጓጓዝ ወይም ክምችት ወቅት ምርቱን ባለበት ሁኔታ ለማቆየት የሚከናወኑ ተግባራት
ዕቃዎችን የማጓጓዝ ሂደት ለማቀላጠፍ ሲባል የሚከናወኑ ተግባራት
ዕቃዎችን ለማሸግ ወይም ለሽያጭ ለማዘጋጀት ሲባል የሚከናወኑ ተግባራት
የተሟላ የምርት ውጤት ለማስገኘት የሚከናወን ቀላል የመገጣጠም ስራ
ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸውና የሌለባቸው ሁኔታዎች በህግ ቢዘረዘሩም ሁኔታው በአግባቡ ካልተገለጸ የስልጣን አለአግባብ መፈጸሙን መወሰን ከባድ ይሆናል። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት አዋጅ ቁ. 768/2004 በተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ የዕቃዎችን ባህርይ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ለተለያየ ዓላማ በህጉ ላይ የተቀመጠ ጊዜ የማስረዘም ስልጣን ተሰጥቶታል። ለመጥቀስ ያህል በአዋጁ አንቀጽ 18/3/ እንደሚከተለው ተደንግጓል።
በቦንድድ ግብዓት አቅርቦት መጋዘን ስርዓት ወደ አገር የገባ ግብዓት ወደ መጋዘን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለአምራች ካልተላለፈ የሥርዓቱ ተጠቃሚ በግብዓቱ ላይ ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥ እና በተጨማሪም የቀረጡን 50 በመቶ እንዲከፍል ይደረጋል። ሆኖም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የግብዓቱን ባህሪ መሰረት በማድረግ የጊዜ ገደቡን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲራዘም ሊፈቅድ ይችላል።
ግብዓት የተለያዩ የራሱ ባህርያት ይኖሩታል። ለአዋጁ አፈጻጸም ባለስልጣኑ የትኛውን ልዩ ወይም ጠቅላላ ባህርይ ከግምት ማስገባት እንዳለበት አልተገለጸም። ድንጋጌው ፈቃደ ስልጣን የሚያጎናጽፍ እንደመሆኑ ባለስልጣኑ ተገቢ ነው ብሎ የወሰነው የግብዓት ባህሪ ተጨማሪ ጊዜ ለመፍቀድ የተገቢ ሁኔታን መለኪያ ያሟላል። ከዚህ አንጻር ባለስልጣኑ በአዋጁ የተሰጠውን ስልጣን አለአግባብ ስለመገልገሉ ለመወሰን ቀርቶ ለማወቅ እንኳን አይቻልም።
ዝርዝር ሁኔታዎች በህጉ ላይ ካልተቀመጡ ከህጉ አጠቃላይ መንፈስ፣ ይዘትና ዓላማ በመነሳት ህጉ በውስጠ ታዋቂነት ያካተታቸው ስለመሆኑ በቅድሚያ መወሰን ይኖርበታል። በአዋጅ ቁ 1156/2012 የደመወዝ አወሳሰንን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ጊዜያዊ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን አለው። ጊዜያዊ የአሠሪና ሠራተኛ ቦርድ ለደመወዝ አወሳሰን ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ሁኔታዎች አልተዘረዘሩም። እነዚህ ሁኔታዎች ከአሰሪና ሰራተኛ ኢንዱስትሪ ሰላም እና ከአጠቃላይ ደመወዝ አወሳሰን መርሆዎች የሚመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለአብነት ያህል የአሰሪውን የትርፍ መጠን ግምት ውስጥ ያላስገባ የደመወዝ አወሳሰን ተገቢ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ነው።
በህግ የተዘረዘሩ ሆነ ያልተዘረዘሩ ሁኔታዎች ለውሳኔ አሰጣጡ ያላቸው ክብደትና ደረጃ ተገቢነትን በመወሰን ረገድ አጋዥነት ያለው ነጥብ ነው። ከብዙ ሁኔታዎች መካከል ውሳኔ ሰጪው በዝምታ ያለፈው ወይም የዘለለው ሁኔታ ለዋናው ውሳኔ ያለው ፋይዳ አናሳ ከሆነ ውሳኔው በአግባቡ የተሰጠ ህጋዊ ውሳኔ ነው።l
ተመጣጣኝነት
ፍትሐዊነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ የተመጣጣኝነት መርህ ነው። ተመጣጣኝነት እንደ ጥፋቱ ክብደትና ዓይነት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። በሌላ አነጋገር አንድ የአስተዳደር መስሪያ ቤት አንድ ችግር ወይም ያልተፈለገ ሁኔታ ለማስወገድ የሚወስደው እርምጃ እንደ ችግሩ ክብደት ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል። ተመጣጣኝነት በብዙ አገራት ራሱን የቻለ የአጣሪ ዳኝነት የምርመራ ምክንያት ቢሆንም በእንግሊዝ አስተዳደር ህግ በሚዛናዊነት ስር ይመደባል። ተመጣጣኝ ያልሆነ ውሳኔ የኢ-ሚዛናዊነትን መስፈርት ካሟላ በዚሁ ስር ውድቅ ይደረጋል። ሆኖም መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከቱ ጉዳዮች አልፎ አልፎ ተፈጻሚ ይሆናል።m
በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ ተመጣጣኝነት በከፊል ጉዳዮች ላይ ራሱን ችሎ ከሚዛናዊነት በበለጠ ተጨባጭ መለኪያ ሆኖ ያገለግላል።n የተመጣጣኝነት መርህ ውሳኔ ሰጪው አንድ ህጋዊ ዓላማ ለማሳካት በአማካይ ሚዛናዊ ከሆነው መንገድ በላይ እንዳይጠቀም ገደብ ያደርጋል። ‘ውጤቱ በመንገዱ ይለካል’ (The means justifies the end) የሚለው መርህ የድርጊቱ ወይም የውሳኔው ተመጣጣኝነት መለኪያ ሆኖ ያገለግላል። አፈፃፀሙ ግን በጣም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተገደበ ነው።
ከእንግሊዝ፣ ከአውስትራሊያ ብሎም ከሌሎች አገራት በበለጠ የተመጣጣኝነት መርህ በጠንካራ መሰረት ላይ የተተከለው በጀርመን የአስተዳደር ህግ ውስጥ ነው። አስተዳደራዊ ተግባራት የህዝብ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ብቻ ሳይሆን በግለሰቡ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አንጻር ተገቢውን ሚዛን የጠበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው የጀርመን የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ሚና ነው። ያም ሆኖ ግን ተመጣጣኝነት ከሚጎድላቸው ግልጽ ሁኔታዎች በስቀር ፍ/ቤቶች በአስተዳደሩ ላይ ጣልቃ አይገቡም። በተለይ የተወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ በህግ ከተፈቀደ ተመጣጣኝነቱ ጥያቄ አይነሳበትም።o
ወደ አገራችን ስንመጣ ተመጣጣኝነት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በግልጽ በህግ ካልተካተተ በቀር ፍ/ቤቶች ጣልቃ የሚገቡበት ቀዳዳ የለም። ለምሳሌ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁ. 980/2008 የንግድ ምዝገባ ከሚሰረዝባቸው ምክንያቶች አንዱ ነጋዴው ሀሰተኛ መረጃ ወይም ሰነድ አቅርቦ የተመዘገበ እንደሆነ ነው። ለምዝገባ ከሚጠየቁት መስፈርቶችና መረጃዎች አንጻር ባለማስተዋል ወይም በቸልተኝነት መረጃ ተሳስቶ የሚቀርብበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡ እነዚህ መረጃዎች ምዝገባ ለማግኘት ያላቸው ፋይዳ ከግዙፍ (material) እስከ ኢምንት ደረጃቸው ይለያያል። ይሁን እንጂ አዋጁ የነጋዴውን የሀሳብ ክፍል እና የቀረበውን መረጃ ፋይዳ በዝምታ አልፎታል። እንበልና ነጋዴው የተሳሳተ ዕድሜ በማስመዝገቡ ምዝገባ ቢሰረዝበት ከጥፋቱ ጋር የማይመዛዘን ፍርደገምድል እርምጃ እንደተወሰደበት ግልጽ ነው። ነጋዴው የተወሰደበትን እርምጀ በመቃወም በአዋጁ አንቀጽ 47 /2/ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቤቱታ ሲያቀርብ በተመጣጣኝነት መለኪያ ሊሻር የሚችልበት ህጋዊ መሰረት የለም። ምክንያቱም የአዋጁ ድንጋጌ ፍትሐዊነት እንጂ ግልጽነት አልጎደለውም። ፍርድ ቤቶች ህግን በመተርጎም ሚናቸው ይህን ግልጽ (ሆኖም ክፍተት የሚታይበትን) ድንጋጌ ማቃናት አይቻላቸውም።p
በአንዳንድ ህጎች አስተዳደራዊ እርምጃ ከጥፋት ደረጃ ጋር ሊመጣጠን እንደሚገባው በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። ለምሳሌ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በሚወስዳቸው አስተዳራዊ እርምጃዎች ከግንዛቤ መግባት ካለባቸው ሁኔታዎች መካከል የጥፋቱ ባህርይ፣ የተፈጸመበት ከባቢያዊ ሁኔታ እንዲሁም ጥፋቱ ያስከተለው ውጤት መጠንና አስከፊነት አንደኛው ነው።q
የተመጣጣኝነት መርህ በዚህ መልኩ በግልጽ ባይደነገግም የጥፋት ደረጃ ክብደት በማያሻማ አነጋገር ከተገለጸ በተዘዋዋሪ ተፈጻሚነት ያገኛል። በመድን ስራ አዋጅ ቁ. 746/2004 በከፍተኛ ደረጃ በተዛባ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለመድን ሰጪ ድርጅት የተሰጠ ፈቃድ በብሔራዊ ባንክ ተሰርዞ ድርጅቱ በሞግዚት አስተዳደር ስር እንዲውል ይደረጋል።r ይህ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ግን ባንኩ በፈቃድ አሰጣጥ ወቅት የቀረበለት ማስረጃ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የተዛባ መሆኑ፣ መረጃው ለፈቃድ መሰጠት ግዙፋዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ እንዲሁም የፈቃድ ሰጪው ህሊና መዛባት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑ ቅድሚያ መረጋገጥ ያለባቸው ሁኔታዎች ናቸው።
አጣሪ ዳኝነትን የሚገድቡ ሁኔታዎች
በዚህ መጽሀፍ ተደጋግሞ እንደተገለፀው የግለሰቦች ነፃነት እና የመንግስት ስልጣን ቅራኔ የአስተዳደር ህግ አጣጥም ሊፈታው የተነሳበት መሰረታዊ ጥያቄ ነው። መደጋገሙ አለምክንያት አይደለም። የአገራችን የአስተዳደር ህግ ገና ከእንጭጭነት ወጥቶ በደንብ ባልዳበረበት ሁኔታ የህጉ መሰረታዊ መርሆዎችና ደንቦች የቅራኔውና ቅራኔው የሚፈታበት ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫ ነጸብራቅ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ደግሞ በዋነኛነት የአገራችንን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ወጥነት ያለው መስፈርት ለይቶ መቅረጽን ይጠይቃል። ከዚህም ባሻገር ተቋማት፣ ፓርላማ፣ መደበኛ ፍ/ቤቶችና የአስተዳደር ጉባዔዎች ስራ አስፈፃሚውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የስልጣንና ፍትህን አስፈላጊነትና ቅራኔ መቼም መዘንጋት የለባቸውም።
በመንግስት ስልጣን እና በግለሰቦች ነፃነት መካከል የሚፈጠረው ቅራኔ በተለይ በአጣሪ ዳኝነት አፈፃፀም ወቅት ጎልቶ ይታያል። በአንድ በኩል መንግስት መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለዜጋው እንዲያቀርብ ውጤታማና ብቁ አስተዳደር መዘርጋት ይጠበቅበታል። በሌላ በኩል በአስተዳደራዊ ሂደቱ የግለሰቦች መብት እና ጥቅም እንዳይጨፈለቅ ከለላ እና ዋስትና እንዲኖር ያስፈልጋል። መደበኛ ፍ/ቤቶች ይህን ከለላ በመስጠት ረገድ ብቻ ሳይሆን የከለላውን ደረጃ ከውጤታማ አስተዳደር ጋር የማጣጠም ትልቅ ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
መደበኛ ፍ/ቤቶች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ መብትን ብቻ መሰረት ያደረገ አመለካከት ብቻ ሳይሆን ከውጤታማ አስተዳደር አስፈላጊነት ጋር በማነፃፀር ሚዛናዊነትን ያማከለ አካሄድ በመከተል ሊሆን ይገባል። በአጣሪ ዳኝነት ላይ የሚሰመረው ገደብ በእያንዳንዱ ፍ/ቤት በቀረበ ጉዳይ ላይ ፍ/ቤት በራሱ የሚወስነው ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን ህግ አውጪው በቀጥታ በህግ ሊገድበው ይችላል።
በአጣሪ ዳኝነት ላይ የሚደረግ የህግ ገደብ ከቀልጣፋና ውጤታማ አስተዳደር አንጻር አስፈላጊነቱ ቢያንስ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት እንዳለው አሳማኝ መከራከሪያ ማቅረብ አይከብድም። ይህም በዋነኛነት ስነ-ስርዓትን ወይም ይዘትን መሰረት ያደርጋል። ከስነ-ስርዓት አንፃር በቂ እውቀትና ክህሎት ባላቸው የአስተዳደር ጉባዔዎችና እና መ/ቤቶች የታየን ጉዳይ በድጋሚ በመደበኛ ፍርድ ቤት ማየት ክርክሮች በአጭር ሳይቋጩ እንዲንዛዙ በማድረግ የመንግስት ሀብት ብክነትን ያስትላል። ከውሳኔው ይዘት አንፃር ካየነው ደግሞ መሰረታዊ የፖሊሲ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ አንዳንድ ጉዳዮች በአስተዳደር መ/ቤቱ ታይተው እልባት ካገኙ በኃላ በድጋሚ ወደ መደበኛ ፍ/ቤት መውሰድ ፍርድ ቤቶች ካላቸው የፖሊሲ እውቀት አናሳነት የተነሳ ለጥያቄዎቹ ተገቢ ምላሽ መስጠት ይሳናቸዋል። ስለሆነም የፖሊሲ ጥያቄዎችን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች መዳኘት ፖሊሲው እንዳይተገበር እክል ይፈጥራል።
በአጣሪ ዳኝነት ላይ የሚደረግ ገደብ ከውጤታማ አስተዳደር አንፃር በቂ አሳማኝ ምክንያቶች ቢኖሩትም መደበኛ ፍርድ ቤቶች በተለይ የኮመን ሎው ፍርድ ቤቶች የህግ አውጭውን ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ አሜን ብለው ለመቀበል ፍቃደኛ ሆነው አልተገኙም። ይልቅስ በስልጣናቸው ላይ የሚቀመጥን ማናቸውንም ገደብ በጠባቡ በመተርም ለህግ የበላይነት መርህ መከበር የፀና አቋም ይዘዋል።
በህግ አውጭው የሚደረገው ገደብ በአንድ በኩል በቀልጣፋና ውጤታማ አስተዳደር በሌላ በኩል ደግሞ በህግ የበላይነትና የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት መካከል ቅራኔ የመፍጠር አዝማሚያ እንዳለው አይተናል። ቅራኔው በተወሰነ ደረጃ በህግ አውጪውና በመደበኛ ፍ/ቤቶች መካከል ፍጥጫ ያስከትላል። ያም ሆኖ ግን የፍጥጫው ይዘት በተግባራዊ አፈጻጸሙ ላይ እንጂ እንጂ የመርህ ጥል አይደለም። ‘በፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ ገደብ ሊጣል አይገባም።’ የሚለው መርህ ህግ አውጪውና መደበኛ ፍ/ቤቶች ሁለቱም እኩል ይጋሩታል። ስለሆነም ገደብ የሚጣለው በጣም በጠባቡና አስፈላጊነቱ የግድ በሚሆንባቸው ውስንና ልዩ ሁኔታዎች ብቻ ነው። በተጨማሪም ህግ አውጪው ገደብ ሲያበጅ በቅድሚያ ዜጎች ከአስተዳደሩ፣ ከአስተዳደር ጉባዔዎች ወይም ከሌሎች ተቋማት በቀላሉ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት በቂ እድል እንዳላቸው በቅድሚያ ያረጋግጣል።
የፈቃድ ቅደመ ሁኔታ
የክለሳ አቤቱታ ከፍትሐብሔር ክርክር ከሚለዩት ከይግባኝ ጋር ደግሞ ከሚያመሳስሉት የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው በቅድሚያ የፍርድ ቤቱ ይሁንታ ማግኘት ያለበት መሆኑ ነው። አስተዳደራዊ መመሪያ ወይም ውሳኔ ይሻርልኝ ጥያቄ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱ አቤቱታ የቀረበበትን ወገን መጥራት ሳያስፈልግ ውድቅ ሊያደርገው ይችላል። ለፈቃድ የሚቀመጠው መመዘኛ ቢለያይም የኮመን ሎው ሆነ የሲቪል ሎው የህግ ስርዓት በሚከተሉ አገራት ህጋዊነትን በመሞገት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በፍርድ ቤት ቅድመ ማጣራት ይደረግባቸዋል። ዓላማው በረባ ባልረባው ጉዳይ አስተዳደሩ ላይ ክስ እየቀረበ የአስተዳደር ተቋማት ወርቃማ ጊዜ በከንቱ እንዳይባክን ለመከላከል በሚል ነው። ሆኖም የፈቃድ ቅድመ ሁኔታ የዜጎች የአስተዳደር ፍትሕ የማግኘት መብት የማጣበብ ውጤት ሊያስከትል እንደ መቻሉ (በተለይ በእንግሊዝ) ጠንካራ ተቃውሞ ሲገጥመው ቆይቷል። በጀርመን የአስተዳደር ህግ ዳኞች አቤቱታውን ውድቅ የሚያደርጉት በህግ ተለይተው በተቀመጡ ውስን ምክንያቶች ብቻ ሲሆን ለዜጋው የጎላ ስነ-ስርዓታዊ መሰናክል አይደለም። በእንግሊዝ ግን ዳኞች አስቀድመው እንዲፈቅዱ ስልጣን የሚሰጠው ህግ ፈቃድ የሚከለከልባቸውን ሁኔታዎች በግልጽ ያልለየ በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አለአግባብ ከፍርድ ቤቱ ደጃፍ እንዲመለሱ ያደርጋል።
በአዋጁ አንቀጽ 54 መሰረት የክለሳ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤት አቤቱታው ሊመረመር ይገባል ብሎ ሲያምን ቅሬታው የቀረበበት የአስተዳደር ተቋም በ15 የሥራ ቀናት ዉስጥ የጽሑፍ መልስ እንዲሰጥ ያዛል። ፍርድ ቤቱ ካላመነ ሁሉም ነገር እዛው ላይ ያበቃለታል። “ካላመነ” የሚለው አገላለጽ ለፍርድ ቤቱ ገደብ የሌለው ስልጣን እንደሚያጎናጽፍ ልብ ይሏል። ይባስ ብሎ ደግሞ አቤቱታው የማይመረመርባቸው ምክንያቶች በአዋጁ በጥቅል ሆነ በዝርዝር አልተጠቀሱም። ከዚህ አንጻር ፍርድ ቤቱ አቤቱታው ሊመረመር አይገባም ሊል የሚችለው በምን ምክንያት ነው? የድንጋጌው ይዘት ሲታይ ፍርድ ቤቱ የግድ ምክንያት መስጠት ያለበት አይመስልም።
ለዳኞች ልክ-የለሽ ስልጣን የሚሰጠው የአንቀጽ 54 ድንጋጌ ብዙ ተስፋ የተጣለበትን የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ በአጭር እንዳይቀጨው ያሰጋል። ከሌሎች አገራት ህግ ጋር ቢነጻጸር የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህጋችን በመመሪያ አወጣጥ ሆነ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ የዘረጋው ስርዓት አስገዳጅ እና ጥብቅ ነው። ይህ በመልካም አስተዳደር ላይ በተወሰነ መልኩ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል ቢችልም ለዜጎች መብት መከበር ላቅ ባለ ደረጃ ከለላ እና ዋስትና ማበጀቱ ግን አያጠራጥርም። በተመሳሳይ መልኩ በክለሳ ስርዓቱ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩን በመቆጣጠር ረገድ ሰፊ ስልጣን እንዲኖራቸው ተደርጓል። ስልጣናቸውን በአግባቡ ከተገለገሉበት ህገ-መግስታዊ ሚናቸውን በስኬት እንዲወጡ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል። ሆኖም ጠባቡን የፍርድ ቤት በር ይባስ ብሎ ዳኞቹ “ሲያምኑ” እንዲዘጉት መፈቀዱ ሲታይ ነገሩ ሁሉ “ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ…” እንደተባለው ዓይነት እንዳይሆን ያሰጋል። አንቀጽ 54 አቤቱታን ውድቅ ለማድረግ በቂ ምክንያቶችን (ቢያንስ ዋና የሚባሉትን) መዘርዘር ነበረበት።
በቂ የሚባሉ ምክንያቶች በአዋጁ ባይዘረዘሩም ከድንጋጌው ዓላማ አንጻር የሚያግባባ ሀሳብ ላይ መድረስ አይከብድም። በመጀመሪያ ደረጃ በአንቀጽ 54 መሰረት አቤቱታ ውድቅ የሚደረግበት አግባብ እና ምክንያት በይግባኝ ክርክር ወቅት ፍርድ ቤቱ “ያስቀርባል/አያስቀርብም” በሚል ይግባኙን መርምሮ ከሚሰርዝበት አግባብ እና ምክንያት በመሰረታዊነት እንደሚለይ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የክለሳ አቤቱታ በዋነኛነት ፍርድ ቤት ላይቀበል የማይችለው በአዋጁ አንቀጽ 51 (አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ የመጨረሻ መሆን አለበት)፤ አንቀጽ 52 (አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን ማሟጠጥ)፤ አንቀጽ 53 (የክለሳ አቤቱታ ማቅረቢያ ጊዜ ማለፍ) እና ተያያዥ በሆኑ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ ነው። ያም ማለት ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክሩ ገብቶ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እስኪቀርብለት ድረስ መጠበቅ ሳያስፈልገው በራሱ አነሳሽነት አቤቱታውን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል።
‘የመጨረሻ’ ማሰሪያ ድንጋጌ
የኮመን ሎው የአስተዳደር ህግ ስርዓትን በሚከተሉ አገራት (በተለይ በእንግሊዝ) ህግ አውጪው የፍርድ ቤቶችን ስልጣን በህግ ከሚገድብባቸው መንገዶች ዋነኛው በአስተዳደር መስሪያ ቤት ወይም በአስተዳደር ጉባዔ የተሰጠን ውሳኔ የመጨረሻ አድርጎ በማሰር ሲሆን ይህም መደበኛ ፍ/ቤቶች ጥያቄ የተነሳበትን ጉዳይ ድጋሚ እንዳያዩት ስልጣናቸውን ይገድባል። ያም ሆኖ ግን የእንግሊዝ ፍ/ቤቶች እንደ ማሰሪያ ድንጋጌው (Finality Clause) አገላለጽ ከፊል የአቋም ልዩነት ቢያሳዩም በመርህ ደረጃ ግን በህግ የበላይነት ላይ እንደተደረገ ገደብ በመቁጠር የመጨረሻ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ህጋዊነት ከማጣራትና ከመመርመር አልተቆጠቡም።s
ህግ አውጪው አንዳንድ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የመጨረሻ እንዲሆኑ ሲደነገግ በህጉ ላይ የተለያዩ አገላለጾች ይጠቀማል። የአገላለጽ መንገዱ መለያየት በተለይ በእንግሊዝ የተለመደ ሲሆን የፍ/ቤቶች ምላሽና ትርጓሜም የህጉን የቋንቋ አጠቃቀም መሰረት ያደርጋል። በጣም የተለመደው አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የመጨረሻ እንዲሆኑ የማድረግ ዘዴ ‘ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል’ (Shall be final) ወይም ‘ውሳኔው የመጨረሻና የጸና ይሆናል’ (Shall be final and conlusive) የሚል ማሰሪያ ድንጋጌ በማስቀመጥ ነው።
በእንግሊዝ ፍ/ቤቶች ይህን መሰሉ የመጨረሻ ድንጋጌ በአፈፃፀም ወይም በአተረጓጎም ረገድ ቀላል እና የማያሻማ ስለመሆኑ ወጥ ተቋም ተይዞበታል። በዚህ መሰረት ‘የመጨረሻ’ የሚል ማሰሪያ ድንጋጌ ውጤት የይግባኝ መብትን ከማስቀረት ባለፈ የውሳኔውን ህጋዊነት ከመመርመር አያግድም። ይህም ማለት ውሳኔው ከይዘት አንፃር እንጂ ህጋዊነቱን በተመለከተ የመጨረሻ ሊሆን አይችልም።
ይህን ሀሳብ የበለጠ ግልለማድረግ ከአገራችን ህግ ጋር በማነጻጸር እናያለን። በመንግስትና የግል ሠራተኞች የጡረታ አዋጆች ላይ እንደተመለከተው የመንግስት እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲዎች ከጡረታ መበትና ጥቅም ጋር በተያያዘ በየፊናቸው በሚሰጡት ውሣኔ ቅር የተሰኘ ሠራተኛ ቅሬታውን ለማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ የማቅረብ መብት አለው። የጉባኤው ውሣኔ በፍሬ ነገር ረገድ የመጨረሻ ሲሆን በውሣኔው መሠረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ቅሬታ ያለው ሠራተኛ የይግባኝ አቤቱታ የሚያቀርበው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ነው።t
የጉባኤው የፍሬ ነገር ውሳኔ የመጨረሻ ተብሎ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት የማይመረመረው በህጉ የስልጣን ገደብ ውስጥ የተሰጠ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። ለምሳሌ ሚስትነት/ባልነት አስመልክቶ ኤጀንሲው ሆነ ጉባኤው የሚደርስበት መደምደሚያ ከስልጣን በላይ እንደመሆኑ የመጨረሻ አሳሪ ውጤት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም ከባልነት/ ሚስትነት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ለማሳለፍ ህጉ ስልጣን አልሰጣቸውም። ይህ የሚያደርሰን ድምዳሜ ‘የመጨረሻ ይሆናል’ የሚል ድንጋጌ ውሳኔው በህግ ከተሰመረው የስልጣን ገደብ ስላለማለፉ ከመመርመር አያግድም።
በአገራችን የመጨረሻ የሚያደርጉ ማሰሪያ አንቀጾች በስፋት የተለመዱ ናቸው። ለአብነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
የደህንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን የውጭ አገር ዜጋን ከአገር ለማስወጣት በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ ቅሬታ የሚቀርበው የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እና የባለስልጣኑ ተወካዮች ለሚገኙበት አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ሲሆን ኮሚቴው ቅሬታውን መርምሮ ለባለስልጣኑ የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበ በኋላ ባለስልጣኑ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው።u
በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006 የተቋቋመው ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ክስ ሰሚዎች (Hearing Examiners) የሚሰጡትን ውሳኔ በይግባኝ አይቶ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው።v
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን አሠሪ፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ወኪል ወይም ሠራተኛ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁ. 923/2008 እንዲሁም በአዋጁ መሠረት የወጣ ደንብና መመሪያ በመጣሳቸው ምክንያት የሚነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመስማትና የመወሰን ሥልጣን ያለው ሲሆን በውሳኔው ቅሬታ ያደረበት ወገን ይግባኙን የሚያቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው።w
የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የምስክር ጥበቃ ተጠቃሚ የሆነ ወይም ያመለከተ ሰው የሚያቀርበውን ቅሬታ ሰምቶ የሚሰጠው ውሳኔ ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማይቀርብበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው።x
የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጭ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ ያለበት ሰው የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምለት ለስነ ምግባር መከታተያ ክፍል አቤቱታ አቅርቦ ውድቅ ከተደረገበት ቅሬታውን ለስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቅረብ የሚችል ሲሆን ኮሚሽኑ በቅሬታው ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው።y
የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የሚወስደውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመቃወም አቤቱታ የሚቀርበው ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ሲሆን የሚኒስቴሩ ውሳኔ የመጨረሻ ነው።z ይኸው ሚኒስቴር መ/ቤት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ በፈቃድ ሰጪው አካል በመታገዱ ወይም በመሰረዙ ምክንያት የሚቀርብለትን አቤቱታ ምርምሮ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው።a በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር ማፅደቂያ አዋጅ ቁ. 549/199 አንቀጽ 16/ሀ/ ላይ እንዲሁ የሚኒስቴሩ ውሳኔ የመጨረሻ እንዲሆን ተደርጓል።b
ለማንኛውም እንቅስቃሴ ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት (advance informed agreement) በመከልከሉ ምክንያት እንደገና እንዲታይ የሚቀርብ ማመልከቻ በአዲስ ሳይንሳዊ መረጃ ከተደገፈ እንደ አዲስ ማመልከቻ በድጋሚ ሊታይ ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ክልከላው የፀና (በእንግሊዝኛው ቅጂ final) ይሆናል።c
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበውን ቅሬታ ሰምቶ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው አካል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ቦርድ ሲሆን የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ጉዳዩ በይግባኝ እንዲታይለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል። ይህን መብት በሚፈቅደው አዋጅ ላይ የውጭ አገር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተነጥለው ቀርተዋል።d ስለሆነም እነዚህን አካላት በተመለከተ የቦርዱ ውሳኔ በዝምታ የመጨረሻ ስለተደረገ ወደ ፍርድ ቤት የመሄጃውን መንገድ ተዘግቷል።
የመጨረሻ የሚለው ቃል በተለያዩ ህጎች ላይ መካተቱ ብቻውን ወደ ፍርድ ቤት ወይም የአስተዳደር ጉባዔ አቤቱታ እንዳይቀርብ አይከለክልም። የቃሉ አጠቃቀምና አገባብ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል። ለምሳሌ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቦርድ ከስልጣንና ተግባራቱ መካከል አንዱ በተቋሙ ውሳኔ (ለምሳሌ በመምህራን ላይ የሚወሰድ የዲሲፕሊን እርምጃ) ላይ ቅሬታ ሲቀርብ መመርመርና የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ነው።e የመጨረሻ መሆኑ ግን ውሳኔው በመንግስት ሠራተኞች የአስተዳደር ፍርድ ቤት እንዳይታይ አይገድበውም። በሰ/መ/ቁ. 78945f ተጠሪ በዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት የተወሰደበትን የዲሲፕሊን እርምጃ ቅድሚያ ለቦርድ ሳያቀርብ ለመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቅ እንደማይችል የህግ ትርጉም ተሰጥቷል። የትርጉሙ እንደምታ በቦርዱ የታየ የተቋሙ ውሳኔ በአስተዳደር ፍርድ ቤቱ መስተናገድ እንደሚችል ነው።
አንዳንድ ጊዜ የመጨረሻ በሚል በተለያዩ ህጎች ላይ የሚጨመረው ማሰሪያ ቃል በይዘቱ በህግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መብት አለመጠየቅ የሚያስከትለውን ውጤት ከመንገር የዘለለ ትርጉም የለውም። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የክፍያ መፈጸሚያ የግብይት ፈጻሚ ዕውቅናን በመሰረዝ ወይም በማገድ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የሚቀርበው ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ነው። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ይግባኝ ካልቀረበ ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል።g እዚህ ላይ የመጨረሻ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በጊዜ ገደቡ አቤቱታ ካልቀረበ መብቱ ቀሪ እንደሚሆን ነው።
የጊዜ ገደብ
በአስተዳደራዊ እርምጃ ‘መብቴ ተጥሶብኛል’ የሚል ወገን በፍ/ቤት አቤቱታ የሚያቀርብበትን ጊዜ መገደብ ሙግትና ክርክር በውጤታማ አስተዳደር ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነሰ ሌላኛው አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል። አስተዳደራዊ እርምጃ ከተወሰደ ከረጅም ጊዜ በኋላ ዘግይተው ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች የተጓተተ አስተዳደር እንዲኖር ምክንያት ናቸው። በተለይ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ እንደገና ‘ሀ’ ብሎ መጀመር ከፍተኛ ብክነት በሚያስከትልባቸው ሁኔታዎች ፍትህ የማግኘት መብትን በጊዜ ገደብ መዝጋት አማራጭ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው።
ለምሳሌ መንገድ ለመስራት በአስተዳደሩ በተደረሰበት ውሳኔ መሰረት ቤቶች ከፈረሱና ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የቤቶቹን መፍረስ ህጋዊነት መሞገት ከፈሰሰው ገንዘብና ንብረት አንፃር አያስኬድም። ቤቶቹን የማፍረስ ድርጊት ከስልጣን በላይ ነው ከተባለ በህግ ፊት ውጤት ስሌለው የተጀመረው ግንባታ መቆም ብቻ ሳይሆን መፍረስ ይኖርበታል። ስለሆነም ምንም እንኳ ከስልጣን በላይ የተፈጸመ ድርጊት ቢኖርም በድርጊቱ ህጋዊነት ላይ ሚዛናዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ አቤቱታ ካልቀረበ ዘግይቶ የቀረበው አቤቱታ ከመነሻው ውድቅ መደረጉ አግባብነት አለው።
በእንግሊዝ አቤቱታ የማቅረቢያ ጊዜው በአማካይ ስድስት ሳምንት ሲሆን ፍ/ቤቶች ውስን በሆኑ ሁኔታዎች ካልሆነ በቀር ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን አያስተናግዱም።
በአገራችን የይግባኝ መብት በልዩ ህግ ሲፈቀድ አቤቱታ የማቅረቢያ ጊዜው በአማካይ 30 ቀናት ነው። ለምሳሌ የብሔራዊ ባንክ የባንክ ስራ ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔ፣h መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ የእንባ ጠበቂ ተቋም በሚሰጠው ውሳኔ ላይ፣i በጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥና በጠበቃ ላይ በሚወሰድ የዲሲፕሊን እርምጃj እንዲሁም ከቡና ጥራት ጋር በተያያዘ ቡና ሲያዝ ወይም መጋዘን እንዲታሸግ በሚሰጥ ትዕዛዝ ላይk ይግባኙ በ30 ቀናት ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል።
ጊዜ በማይሰጡ ለምሳሌ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው በ5l 15 እና 20m ቀናት ተገድቧል። በአንዳንድ ህጎች ላይ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ህጉ የተመለከተው የ60n ቀናት ጊዜ በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ለሚቀርብ ይግባኝም ተፈጻሚ ተደርጓል።
በአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ አንቀጽ 50 ላይ አቤቱታ ማቅረቢያ ሶስት የጊዜ ገደቦች ተለይተዋል። የአስተዳደር ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ ባለጉዳዩ ውሳኔውን እንዲያውቀው ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ30 ቀናት ጊዜ መቅርብ ያለበት ሲሆን የአስተዳደር መመሪያ ስነ-ስርዓቱን ተከትሎ አልወጣም በሚል የሚቀርብ አቤቱታ መመሪያው ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ90 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ መመሪያው ከስልጣን በላይ ነው አሊያም ከበላይ ህግ ማለትም ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት፤ ከአዋጅ ወይም ደንብ ጋር ይቃረናል በሚል የሚቀርብ አቤቱታ በማናቸውም ጊዜ ሊስተናገድ ይችላል።
የ30 እና 60 ቀናት የጊዜ ገደብ ማለፍ ውጤት አቤቱታ የማቅረብ መብትን ያሳጣል። ህጉ የወሰነው የጊዜ ገደብ በዝቷል/አንሷል ለማለት አቤቱታዎች በፍርድ ቤት መቅረብ ከጀመሩ በኋላ ግለሰቦች መብታቸውን በመገልገል እንዲሁም አስተዳደሩ ተግባራቱን በማከናወን ሂደት ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ በተጨባጭ ጥናት መገምገም ያስፈልጋል። እስከዚያው ግን በዚህ ነጥብ ላይ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ ይመረጣል። ያም ሆኖ ጊዜው ያለፈበት አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ሊፈቀድ የሚችልበት ሁኔታ በአዋጁ በዝምታ መታለፉ የአዋጁ ትልቅ ድክመት መሆኑ በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። በ 30 ወይም በ 60 ቀናት ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ የማይቻልባቸው በርካታ አጥጋቢ ምክንያቶች ይኖራሉ። እነዛን ፍርድ ቤት እየመዘነ ጊዜው ያለፈበትን አቤቱታ የሚያስተናገድበት ስርዓት ሊኖር ይገባል።
አዋጁ ጊዜው ያለፈበት አቤቱታ የሚስተናገድበት ስርዓት ያልዘረጋ በመሆኑ አማራጭ መፍትሔ የሚሆነው ጊዜው ካለፈ በኋላ የይግባኝ ማመልከቻ እንዲቀርብ ፈቃድ ስለመጠየቅ የሚመለከቱት የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 324 እና 325 ድንጋጌዎችን ተፈጻሚ ማድረግ ይሆናል። በአዋጁ ባልተመለከቱ የክለሳ ሥነ-ሥርዓት ጉዳዮች ላይ አግባብነት ያላቸዉ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ስለሚሆኑo መፍትሔው ያስኬዳል።
ያልበሰለ ጉዳይ
ተጨባጭ እርምጃ ወይም ውሳኔ ከመወሰዱ በፊት ከአሁን አሁን መብትና ጥቅሜን የሚጎዳ ተግባር ሊፈጸምብኝ ይችላል በማለት ብቻ የሚቀርብ አቤቱታ በተቀላጠፈ አስተዳደር ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ጫና አንፃር በመደበኛ ፍ/ቤት ተቀባይነት አይኖረውም። ስለሆነም ፍርድ ቤቶች ገና ባልበሰለና ባልተቋጨ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም።
ለምሳሌ ቅጣት ወይም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድ ለበላይ ኃላፊ የሚቀርብ የውሳኔ ሃሳብ ወይም የምርመራ ሪፖርት ምንም እንኳን ይዘቱ የተፋለሰና የተዛባ ቢሆንም የበላይ ኃላፊው ውሳኔ እስኪሚያሳልፍ ድረስ አቤቱታ ሊቀርብ አይችልም። የውሳኔ ሃሳቡ ወይም የምርመራ ሪፖርቱ የቀረበለት የበላይ ኃላፊ ሙሉ በሙሉ ሊያጸድቀው ወይም በከፊልም ሆነ በሙሉ ውድቅ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም ፍርድ ቤቶች መብትና ጥቅምን የሚነካ ተጨባጭ ውሳኔ፣ ድርጊት ወይም እርምጃ መኖሩን ሳያረጋግጡ በአስተዳደሩ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይኖርባቸውም።
አስተዳደራዊ መፍትሔ ማሟጠጥ
‘መብቱን ለማስከበር በፍ/ቤት አቤቱታታ የሚያቀርብ ወገን በህግ የተቀመጡትን አማራጭ አስተዳደራዊ መፍትሔዎች አሟጦ ካልጨረሰ በቀር ጉዳዩ ሊታይለት አይገባም’ የሚለው ቅድመ ሁኔታ በአስተዳደራዊ ጉዳይ ፍርድ ቤት የመጨረሻው አማራጭ እንደሆነ ይጠቁመናል። በኮመን ሎው አገራት ቅድመ ሁኔታው በህግ አውጪው የተቀመጠ ገደብ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች በራሳቸው የተፈጠረና የዳበረ ጽንሰ-ሃሳብ ነው። በእንግሊዝ ሆነ በአሜሪካ አማራጭ የመፍትሄ መንገዶችን ወደ ጎን በመተው የሚቀርብ አቤቱታ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት አይኖረውም። ሎርድ ሰካርማን (Lord Scarman) የተባሉ የእንግሊዝ ዳኛ እንደተናገሩት፤
አማራጭ መፍትሄ ካለ በአጣሪ ዳኝነት መፍትሄ የለም። አጣሪ ዳኝነት ቅጥያ (ተቀጽላ) ሙግት እንጂ ይግባኝ አይደለም። ህግ አውጭው የይግባኝ ማቅረቢያ ሰርዓት በህግ በዘረጋበት ሁኔታ መደበኛ ፍርድ ቤቶች አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ይህን ቅጥያ አጣሪ ዳኝነት ሂደት ተፈፃሚ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።p
በአገራችን አስተዳደራዊ መፍትሔ ማሟጠጥ በመደበኛ የፍትሐብሔር ክሶች ሆነ በልዩ ህግ በሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎች በግልጽ የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ አይደለም። የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ በአንቀጽ 50 ላይ ‘አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን አሟጦ መጨረስ’ የክለሳ አቤቱታ ለማቅረብ ቅድመ-ሁኔታ አድርጎታል። በዚሁ መሰረት በሕግ በሌላ ሁኔታ ካልተደነገገ በቀር ማንኛውም ለፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታ የሚያቀርብ ባለጉዳይ አቤቱታውን ከማቅረቡ በፊት በአስተዳደር ተቋሙ ውስጥ ያሉትን አስተዳደራዊ መፍትሄዎች አሟጦ መጨረስ አለበት፡፡ “በአስተዳደር ተቋሙ ውስጥ ያሉ መፍትሔዎች” የሚለው አገላለጽ በጣም ሰፊ ከመሆኑ ከአቤቱታ አቅራቢው የሚጠበቀውን ግዴታ የማይጨበጥ አድርጎታል። ‘በተቋሙ ውስጥ በተዘረጋው የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን አሟጦ ከመጨረሱ በፊት” ቢባል ልኩ የታወቀ ግዴታ ይሆን ነበር።
ህጉ ከመውጣቱ በፊት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ‘አሟጦ የመጨረስ ግዴታ’ በአስተዳደራዊ ክርክሮች አንዱ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ተቀብሎታል። በዚህ ነጥብ ላይ በሰ/መ/ቁ. 78945q በሰጠው የህግ ትርጉም ወደ ፍርድ ቤት ወይም አስተዳደር ጉባዔ የሚቀርብ አቤቱታ አስተዳደራዊ የመፍትሔ መንገዶችን ከማጠናቀቁ በፊት ሊስተናገድ አይችልም። የጉዳዩ መነሻ ከመምህራን የዲሲፕሊን እርምጃ ጋር የተያያዘ ሲሆን ችሎቱ በአከራካሪው ነጥብ ላይ በሰጠው አስተያየት የመንግስት ዩኒቨርስቲ መምህራን በሚወሰድባቸው የዲሲፕሊን እርምጃ ለዩኒቨርስቲው ቦርድ ቅሬታ የሚያቀርቡበት መንገድ በዩኒቨርስቲው ውስጠ ደንብ ከተደነገገ ቅሬታው ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት በአስተዳደር ጉባዔ በይግባኝ አይታይም።
በህግ የተቀመጠ አማራጭ የአቤቱታ ማቅረቢያ መንገድ ቢኖርም ውስን በሆኑ ሁኔታዎች መፍትሄ የማሟጠጥ ቅድመ ሁኔታ ወደጎን ይደረጋል። ቅድመ ሁኔታው ሲቀመጥ መነሻው አቤቱታ አቅራቢው በእርግጥ ተጨባጭ መፍትሄ ማግኘት የሚያስችለው መንገድና ስርዓት እንዳለውና በተግባርም በመብቱ ለመገልገል በቂ እድል እንደተሰጠው ግምት በመውሰድ ነው።
ስለሆነም በህግ የተመቀጠውን መፍትሄ በተግባር መጠየቅና ማግኘት የማይቻል ከሆነ በደል የደረሰበት ወገን ፍትህ የማግኘት መብቱ በፍ/ቤት ሊረጋገጥለት ይገባል። በእንግሊዝ በቀረበ አንድ ጉዳይr ህገ-ወጥ ስደተኞች ተብለው የታሰሩ አቤቱታ አቅራቢዎች በህግ የተቀመጠላቸውን የአቤቱታና የመፍትሄ መንገድ ወደ ጎን በመተው በፍ/ቤት አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታ ለማቅረብ ተፈቅዶላቸዋል። በወቅቱ (እ.ኤ.አ 1974 ዓ.ም.) በነበረበው የእንግሊዝ ህግ ከእንግሊዝ እንዲባረር የተወሰነበት ስደተኛ እርምጃውን በመቃወም ይግባኝ አቅርቦ መፍትሄ ማግኘት ይችላል። ሆኖም አገር ለቆ እንዲወጣ የተወሰደበትን እርምጃ ተቀብሎ መጀመሪያ ከእንግሊዝ ካልወጣ በስተቀር አቤቱታ የማቅረብ መብት የለውም። ከላይ በተጠቀሰው መዝገብ ጉዳዩን ያስተናገደው ፍርድ ቤት በህግ የተቀመጠው የአቤቱታ ስርዓት በተግባር ሲታይ መፍትሄውን ለማግኘት አዳጋች መሆኑን በመጠቆም የቀረበውን አካል ነፃ የማውጣት አቤቱታ ተቀብሎታል።
በአማራጭ የመፍትሄ መንገዱ አተገባበር ላይ ከሚነሳው ጥያቄ በተጨማሪ መፍትሄ ለመስጠት በህግ ለተቋቋመ የአስተዳደር አካል የቀረበ አቤቱታ እልባት ሳያገኝ አለአግባብ ከዘገየ የአቤቱታውን ውጤት መጠበቅ ሳያስፈልግ በቀጥታ በፍርድ ቤት የሚቀርብ አቤቱታ ተቀባይነት ያገኛል። ስለሆነም ለይግባኝ ሰሚ የአስተዳደር አካል የቀረበ ቅሬታ ወይም አቤቱታ አለበቂ ምክንያት ውሳኔ ሳያገኝ ከዘገየ ፍርድ ቤቶች መፍትሄ የማሟጠጥ ቅድመ ሁኔታን በማስቀረት የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል።
መዘግየት በአቤቱታ አቅራቢው ላይ የሚፈጥረውን ችግር ለመቅረፍ አሟጦ የመጨረሰን ቅደመ ሁኔታ የሚያስቀር ልዩ ሁኔታ ደንግጓል። በአንቀጽ 50/1/ እንደሚነበበው የአስተዳደር ተቋሙ አስተዳደራዊ መፍትሄ የመስጠቱን ሂደት ከሚገባው ጊዜ በላይ ያራዘመ እንደሆነ አስተዳደራዊ መፍትሄ አሟጦ መጨረስ ግዴታ አይሆንም። ከመራዘም ውጭ ያሉ ግዴታውን የማይቻል የሚያደርጉ ምክንያቶች አልተጠቀሱም።
በአገራችን በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ አስተዳደራዊ ቅሬታ ምላሽ የሚያገኝበት የጊዜ ገደብ ተለይቶ ይወሰናል። ቅሬታውን የሚያስተናግደው አካል ምላሽ ሳይሰጥ የጊዜ ገደቡ ካለፈ አስተዳደራዊ መፍትሔ የማሟጠጥ ቅድመ ሁኔታ ይቀራል። ስለሆነም ቅሬታ አቅራቢው መብቱን በመደበኛ ፍርድ ቤት ለመጠየቅ መብት ያገኛል። የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅንናs እና አዋጁን ተከትለው የሚወጡ ደንብና መመሪያዎችን በመተላለፍ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደበት ሰው አግባብ ላለው ባለስልጣን ኃላፊ በአስር ቀናት ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ ያለበት ሲሆን ኃላፊው አቤቱታውን ሰምቶ በአምስት ቀናት ውሳኔውን ለአመልካቹ በጽሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል።t የበላይ ኃላፊው ውሳኔውን በጊዜ ገደቡ ውስጥ ካላሳወቀው ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቤቱታውን የማቅረብ መብት አለው።u
በተመሳሳይ መልኩ በእንስሳት መድሀኒት ንግድ ላይ የተሰማራ ግለሰብ ወይም ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ወይም የሙያ ፈቃድ ከታገደበት ወይም ከተሰረዘበት ለቅሬታ ሰሚ አካል አቤቱታውን የማቅረብ መብት ያለው ሲሆን ቅሬታ ሰሚው በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ ሳይሰጥ ከቀረ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰድ ይችላል።v
በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች
በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ በፍርድ ቤቶችና በህግ ምሁራን ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ ይዘት አያንጸባርቅም። በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12w በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው።
ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው። ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን ነው። በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም።
ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል። ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15x በተሰጠ የህግ ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል።
በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል። ለምሳሌ በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ይዋልላል።
ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው።
ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን አይመለከትም።

No comments:
Post a Comment