ሕግ ባለበት ግዴታ ፈጻሚ እንዴት ይጥፋ?
ሕግ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጸሙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ፍትኃዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚተዳደርበት ማኅበራዊ መርህ ነው፡፡ ሕግ ባይኖር ሊከሰት የሚችለውን የጥቅም ግጭት፣ አለመግባባት፣ ሁከት ወዘተ. ሕግ የተለያዩ መርሆችን በመደንገግ፣ መብትና ግዴታን በመሥራት ሚዛናዊ የሆነ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖር ይረዳል፡፡ ያም ሆኖ የሕግ መኖር በራሱ ሕግ እንዳይጣስ አይረዳውም፡፡ ሕግም ኖሮ በየዕለቱ የሚጣሱ የሕግ መርሆች፣ የማይከበሩ ግዴታዎችና የሚጣሱ መብቶችን እናስተውላለን፡፡ ሆኖም ሕግ ለዘመናት ቀርፀው ኅብረተሰባቸውን በሚያስተዳድሩና የሕግ የበላይነት በተወሰነ ደረጃ በሚከበርባቸው አገሮች ሕግ በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣል፡፡ የሕግ አንዱ ጥቅም ኅብረተሰቡን ወደ መልካም ሥነ ምግባር መምራት፣ ዘመናዊ ማድረግና የሌላውን ግለሰብ መብት እንዲያከብሩ መርዳት በመሆኑ ግለሰቡ በዕለት ተዕለት ኑሮው ሕግን የማክበር፣ የሌላውን ሰው መብት የመጠበቅ፣ ግዴታውን አውቆ የመተግበር ዝንባሌን ያዳብራል፡፡ ቢያንስ በአደባባይ በድፍረት የሌላውን ሰው መብት መጣስ፣ ግዴታን አለማክበር እንደ ጀብድ የሚያኩራራ አይሆንም፡፡ ይህ ሕግን የማክበር ባህል እንዲፈጠር የመንግሥት ድርሻ ሰፊ ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡም መብቱን በመጠየቅና ግዴታውን በማክበር ባህሉ እንዲፈጠር የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በአገራችን ሕግን፣ የሕግን አፈጻጸምና ሕግ የኅብረተሰቡን ጠባይ በመግራት ያለውን አስተዋጽኦ መገምገም ከላይ የተመለከትናቸውን የሕግና የኅብረተሰብ ግንኙነት ለማስተዋል ይቸገር ይሆናል፡፡ አገራችን ለዘመናት የተለያዩ ሕግጋት ያሏት ቢሆንም፣ የኅብረተሰቡ ለሕግ የበላይነት የመገዛት ጠባይ ላይ ያለው ተፅዕኖ የዘመናቱ ያህል የቆየ/የሰረፀ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በአደባባይ የሰዎችን ግላዊ መብት መግሰስ፣ መሳደብ፣ መተንኮስ፣ መዛት ወዘተ. ሕጋዊ ተግባራት የመሰሉ ያህል በየዐውዱ ሲፈጸሙ እንሰማቸዋለን/እናያቸዋለን፡፡ ድርጊቶቹን ወንጀል የሚያደርጉና የሚቀጡ፣ በፍትሐ ብሔርም የጉዳት ካሳ እንዲጠየቅባቸው የሚያስችሉ የሕግ ድንጋጌዎች ተቀርፀዋል፡፡ ነገር ግን ባለመብቱም አይጠይቅም፣ ግዴታ ያለበትም ወገን ሳይጨነቅ በአደባባይ የሌላውን መብት ይጥሳል፡፡ ሕጉ አለ፤ እንዳይፈጸም ግን መብት ጠያቂና ግዴታ ፈጻሚ ጠፍቷል፡፡ ጉዳዮቹ ትናንሽ ቢመስሉንም ተደጋግመው በተፈጸሙ ቁጥር የሕግ አልባነት (Lawlessness) ማስከተላቸው እንደማይቀር ልብ ይሏል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን በዚህ አንድ ወይም ሁለት ሳምንት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መቀነስን መነሻ በማድረግ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የተደረገውን የታሪፍ ማስተካከያ ተከትሎ የሚስተዋለው ነገር ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ከአምስት ዓመት በፊት በነበረበት ሁኔታ (ከ50 ዶላር በታች) መቀነሱን መነሻ በማድረግ የቅናሹን መጠን ያህል መሆኑን ለመናገር ባያስደፍርም፣ የተወሰነ የሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ለውጥ ተደርጓል፡፡ በአጭር ርቀት ወደ 15 ሳንቲም፣ በመካከለኛ ርቀት ወደ 30 ሳንቲም፣ ራቅ ባሉት ደግሞ እስከ 40 ሳንቲም ድረስ ቅናሽ ተደርጎባቸው ማስተካከያው ተግባራዊ ከሆነ ሁለት ሳምንት አለፈው፡፡ የዋጋ ክለሳውን ያደረገው የትራንስፖርት ባለሥልጣን በአዋጅ ይህንን የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት አካል ሲሆን፣ ያወጣውም መመርያ ሕግ መሆኑ አያከራክርም፡፡ የዚህን ሕግ አተገባበር ከተመለከትን ግን የወጣው ሕግ ነው ወይስ የመንገደኛ ሰው ትዕዛዝ የሚለውን ለመለየት ያስቸግረናል፡፡ እስካሁን ድረስ ባለታክሲውም በድሮው ታሪፍ ብቻ ያስተናግዳል፣ ሕዝቡም የተጠየቀውን ይከፍላል፡፡ ሕዝቡ የታሪፉን መለወጥ ቢያውቅም ባያውቅም፣ በድሮው መመርያ መሠረት ታሪፉን እየከፈለ ይጓዛል፡፡ መብቱን በአደባባይ የሚጠይቅ በብዛት አይስተዋልም፣ ከጠየቀም እንደ ወንጀለኛ ይሸማቀቃል፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት አስተዳደር ሌሎችም ሕግጋት በአደባባይ ሲጣሱ እናስተውላለን፡፡ ለመጫን ከተፈቀደለት ሰው ቁጥር በላይ ማሳፈር፣ የትራፊክ መብራት አለማክበር፣ ባልተፈቀደለት መንገድና የአነዳድ አካሄድ ማሽከርከር ወዘተ. በየዕለቱ የሚጣሱ የሕግ መርሆች መገለጫ ናቸው፡፡ ወቅታዊ ስለሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍን አነሳን እንጂ እንዲህ ዓይነት ባህል በሌሎችም ጉዳዮችም ይስተዋላል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት ሁኔታ የነዳጅ ማደያዎች በተለወጠው የነዳጅ ታሪፍ ደንበኛን ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆን፣ የሸቀጦች የዋጋ ዝርዝር በመሸጫ ቦታ በግልጽ አለማስቀመጥ፣ በዓላትን መነሻ በማድረግ ገበያ ያልፈቀደውን ዋጋ መጨመር ፣ለሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ አለመቁረጥ ወዘተ. በየዕለቱ ሕግ ያልወጣላቸው ያህል የሚጣሱ መሆናቸውን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እያስተዋልን ነው፡፡ ሕግ አክባሪ ዜጋ መፍጠር ለምን ዳገት ሆነ? ትናንሽ የሚባሉቱ ግን አብዛኛውን ኅብረተሰብ የሚመለከቱት ሕግጋትን አለማክበር ውጤቱ ምን ይሆናል? ለሕግ ተገዥ ዜጎችን ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ምን ሊያደርጉ ይገባል? የሚሉትን ጭብጦች መነሻ አድርገን በዚህ ጽሑፍ የተወሰነ ነገር ለማለት እንሞክር፡፡ ሕግ ለኅብረተሰቡ ያለው ተግባር በሕግ ሙያ የታወቁ የተለያዩ የሥነ ሕግ አስተምህሮዎች አሉ፡፡ የሕግ ትርጉም፣ ዓላማ፣ ከኅብረተሰብና ከሞራል ጋር ያለው ግንኙነት ወዘተ. አከራካሪና እንደ የሕግ አስተሳሰቡ (ሥነ ሕግ) የሚለያይ ነው፡፡ ሁሉንም የአስተሳሰብ ልዩነቶች ለመዳሰስ በዚህ ጽሑፍ ባይቻልም፣ ሁሉንም የሚያስማሙ የተወሰኑን ሕግ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ተግባር ለመመልከት መሞከር ግን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ኅብረተሰቡን ከመጥፎ ነገር (Evil) መከላከል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ያለምንም ምክንያት ሌላውን ሰው የሚጎዱበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዲህ ሲሆን፣ ዜጎች በሌሎች መጥፎ ተግባር እንዳይጎዱ ሕግ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ በተለይ የወንጀል ሕግ በሰዎች ሕይወት፣ ንብረት፣ ክብርና ነፃነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በዓይነት በመዘርዘር አጥፊዎቹ እንዲቀጡ ያደርጋሉ፡፡ ሁለተኛው ኅብረተሰቡ ያለው መልካም እሴት እንዲጠናከር ወይም እንዲስፋፋ መርዳት ነው፡፡ ሕግ ስለአጥፊዎች በመጨነቅ እነሱን ብቻ ያማከለ ድንጋጌዎችን አይቀርፅም፡፡ በመልካም አኗኗር ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍልም መርሆችን ይደነግጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ፍላጎት ለማሳካት በሚጣጣርበት ወቅት የሌላውን ሰው ጥቅም እንዳይጎዳ፣ የፍላጎት መብዛትና የሀብት ማነስ በሚፈጥረው ክፍተት ግለሰቦች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ሕግ ሚዛናዊና ፍትኃዊ የሆኑ መርሆችን በመደንገግ መብትና ግዴታ ይሠራል፡፡ በሦስተኛነት የሕግ ተግባር መርሆች ተጥሰው ልዩነት፣ አለመግባባት ወይም ግጭት በተከሰተ ጊዜ ሕግ የመገላገል ወይም መፍትሔ የመስጠት ወይም የመዳኘት ድርሻውን ይወጣል፡፡ በመጨረሻም ሕግ መልካም የሚሠሩ ዜጎችን የማበረታታት ድርሻ አለው፡፡ መልካም የሚሠሩ ዜጎች የሚበረታቱ ከሆነ ኅብረተሰቡ መልካም ሥራ በመሥራት በሰላም ለመኖር የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠርለታል፡፡ ሕግ እነዚህን ተግባራቱን የሚወጣው በተለያዩ መንገዶች ነው፡፡ መጥፎ ሥራ የሠሩትን ይቀጣል፡፡ ሰው የገደለ፣ ንብረት የሰረቀ በእስራትና በገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣው ዓይነት፡፡ የተወሰኑት ሕግጋት መብት የተጣሰባቸውን ግለሰቦች ደግሞ በተጎዱት መጠን እንደካሳ ድንጋጌዎችን ቀርፆላቸዋል፡፡ የተሰረቀ ንብረቱ ይመለስለታል፣ ውል የፈረሰበት የደረሰበት ጉዳት በካሳ መልክ እንዲከፈለው ይፈቅድለታል፡፡ አንዳንድ መልካም ግለሰቦችን ደግሞ ስለመልካምነታቸው ያበረታታቸዋል፡፡ የጠፋ ዕቃ ያገኘ ባለቤቱን ለማግኘት አስተዳደራዊ ሥራዎችን አከናውኖ ሲያበቃ ባለቤቱን ካላገኘ ሰውየው የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ ለኅብረተሰቡ እጅግ ጠቃሚ በሆኑ (ለምሳሌ ትምህርት ወዘተ.) ሥራዎች ላይ የተሰማራ ሰው የግብር ነፃ ልዩ ጥቅም ያገኛል፡፡ ሕጉ የተለያዩ ተግባራትን ለመፈጸም ድንጋጌዎችን ቢቀርፅም፣ በተግባር ግን ሕግን የማያከብሩት ሳይታረሙ፣ ሕግን አክባሪዎቹም ሲጎዱ እናስተውላለን፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ባደረግነው ጉዳይ የሕዝብ ትራንስፖርት የታሪፍ ለውጡ በአግባቡ ስላልተፈጸመ ሕግ አክባሪው ተሳፋሪ ሲጎዳ፣ ሕጉን ያላከበረው አገልግሎት ሰጪው ደግሞ ሲጠቀም እያስተዋልን ነው፡፡ ሕግ ያለማክበር ምንጮችን ፍለጋ ሕግን ያለማክበር በምን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል፣ ምንጮቹ ምን እንደሆኑ ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለት ተዕለት የሕይወት ተሞክሮ ከምናስተውለው የተወሰኑ ምንጮችን መጠቆም እንችላለን፡፡ ከተነሳንበት የሕዝብ ትራንስፖርት ዋጋ ለውጥና የአገልግሎቱ ሰጪዎች ግብረ መልስ ተሞክሮን ለአብነት በመጥቀስ ለማብራራት እንሞክር፡፡ የመጀመሪያው ሕግን ያለማክበር ምንጭ ሕግ ካለማወቅ የሚከሰት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕጉ መውጣቱን፣ ይዘቱን፣ የሚፈቅደውንና የሚከለክለውን ያላወቀ ባለመብት መብቱን መጠየቅ ይቸግረዋል፤ ግዴታ ፈጻሚውም ግዴታውን ለመወጣት አይችልም፡፡ ከትራንስፖርት ታሪፍ ጋር በተያያዘ በታክሲ ውስጥ ከሚሰሙ ንትርኮች ለመገንዘብ እንደሚቻለው አብዛኛው ሰው የታሪፉን ቅናሽ ያደረገው መመርያ ስለመኖሩ፣ ማስተካከያው ምን ያህል እንደሆነ ለማስረዳት ይቸግረዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ ማስተካከያ ታሪፉን በጋዜጣ አትሞ ማውጣት በቴሌቪዥንም መንገር የተለመደ ቢሆንም፣ በዚህ ሰሞን ግን ማስተካከያው የተደረገበት አግባብ በይፋ ባለመታወቁ ባለመብቱም ግዴታ ፈጻሚውም ስለ መመርያው በቂ ዕውቀት ስለሌለው የሕጉ መጣስ ቀጥሏል፡፡ በአገራችን ሕግን አለማወቅ ይቅርታ እንደማያሰጥ ቢታወቅም፣ ሕዝቡ ሕጉን እንዲያውቅ የሚደረግበት አግባብ እጅጉን አነስተኛ ነው፡፡ እንኳን በነጋሪት ጋዜጣ ለማይታተሙት መመርያዎችና የሕዝብ ማስታወቂያዎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው የሚወጡት ሕግጋት (አዋጆችና ደንቦችን) እንኳን ኅብረተሰባችን የሚያውቅበት ሁኔታ አነስተኛ ነው፡፡ ሕጉን የሚያውቀው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ አቤቱታውን ለየትኛው የመንግሥት ተቋም በምን ሁኔታ እንደሚያቀርብ ላያውቅ ይችላል፡፡ ሁለተኛው የሕግ መጣስ ምክንያት ኅብረተሰቡ ሕጉን ቢያውቀውም የሕጉ ይዘት ከጊዜ ብዛት፣ በመንግሥት አደረጃጀት ተገቢ መዋቅር ስላልተዘጋጀለት ወይም ከኅብረተሰቡ ወግና ባህል ያፈነገጠ በመሆኑ ምክንያት ሕጉ የማይከበርበት ሁኔታ ነው፡፡ በአገራችን ለዚህ ዓይነት የሕግ አለመከበር ምክንያት የሆኑ ድንጋጌዎችን በብዛት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የስም ሕጋችን ከምዕራባውያን የተቀዳ ባህላችንን የማይመስል በመሆኑ ከመውጣቱ ጀምሮ ባለመከበር የታወቀ ነው፡፡ ሕጉ የቤተሰብ ስም እንዲኖረን ያስገድዳል፤ እኛ ግን ለዘመናት ያለቤተሰብ ስም በመኖር ላይ ነን፡፡ ልደት፣ ጋብቻና ሞት እንዲመዘገቡ የፍትሐ ብሔር ሕጉና የወንጀል ሕጉ በግዴታ ይደነግጋሉ፡፡ ነገር ግን ለዘመናት መዝጋቢ አካል (Notary) ባለመኖሩ ዕድሜያችን በግምት፣ ጋብቻችን በምስክር ሞታችን በስማ በለው ሲረጋገጥ ይኖራል፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አዋጅ ችግሩን ይቀርፈዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሌላም ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የቤተሰብ ሕጉ በጋብቻ ላይ ጋብቻን ይከለክላል፤ ከተጣሰም ጋብቻው እንዲፈርስ ደንግጓል፡፡ ሆኖም ይህ ሕግ ከአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች እምነትና ባህል ጋር ስለማይጣጣም ከሚከበርበት ይልቅ የሚጣስበት ሁኔታ ይሰፋል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍን የሚገዛ መመርያ ግን በምንም መስፈርት ከባህልም ሆነ ከእምነት ስለማይቃረን፣ ከጊዜ አንፃርም ወቅታዊና አንገብጋቢ በመሆኑ ይህ ምክንያት ላለመከበሩ ቅቡል ምክንያት አይሆንም፡፡ ሦስተኛው ሕግ ያለመከበር ምንጭ የመብት ጠያቂው ተሳትፎ ማነስ ነው፡፡ በአገራችን አብዛኛው ሰው መብቱ እየተጣሰ ዝም ማለት፣ መብቱንም ሲጠይቅ ግለሰቡ እንደ ነገር ተንኳሽ፣ ጨቅጫቃ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜም መብቱን በመጠየቁ የሚያገኘው ጥቅም ከሚያጣው ጉዳት ጋር ሲታሰብ አነስተኛ በመሆኑ መብቱን የማይጠይቅበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ በአገራችን አብዛኛው ሰው መብቱ ሲጣስ የማይጠይቅበት ሁኔታ ከባህል ጋር የተያያዘ ወይም ከዕውቀት ማነስ ወይም ድፍረት ማጣት ወይም ሌላ ምክንያት መሆኑ ሊጠናና በመንግሥት ወይም መብት ላይ በሚሠሩ ድርጅቶች ግንዛቤ ሊፈጠርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ማስተካከያ ጋር በሚታዩ የሕግ አለማክበር ግዴታዎች ግን አብዛኛው ሕዝብ መብቱ ላይ መተኛቱን በየሰዓቱ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀም የሚያስተውለው ነው፡፡ እንኳን መብት ጠይቆ ያለአግባብ የከፈለው ታሪፍ እንዲመለስለት መጠየቅ፤ ሌላው ሲጠይቅ እንኳን አለመተባበር ከዚያም አልፎ እንደ ‹‹ሕግ የጣሰ›› ሰው መታየት ተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የመብቱን መጣስ፣ ግዴታውን ያላከበረውን አገልግሎት ሰጪ ድፍረት ያሰፋዋል፡፡ አሁን አገራችን በገጠማት የሕዝብ ብዛትና የትራንስፖርት አቅርቦት ማነስ እንኳን ትንሽ ሳንቲም፣ አገልግሎቱ ተገኝቶ በብዙ እጥፍም ቢከፍሉ የሚመኙ አይጠፉም፡፡ ይህ አካሄድ ግን የሕግ የበላይነትን የማጥፋት ባህል ጅማሮ መሆኑ አይቀርም፡፡ በመጨረሻ ለሕግ መጣሱ ምክንያት የሚሆነው የአስፈጻሚው አካል ጥንካሬ ማጣት ነው፡፡ እንኳን በሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ቁጥጥር በሌሎች የትራፊክ ሕግጋት አከባበር የሕዝብ ትራንስፖርትን የሚቆጣጠሩ አካላት ችግሮች ከሠሩት ሥራ ገዝፈዋል፡፡ ሾፌሮችና ረዳቶች መብት ለመጠየቅ የተነሳ አካል ሲገጥማቸው፣ የትም ሄደህ መክሰስ ትችላለህ ሲሉ በድፍረት መናገራቸው የተቆጣጣሪውን አካል ጥንካሬ ማነስ ማሳያ ነው፡፡ ተቆጣጣሪው ጠንካራ/አስተማሪ ቁጥጥር አለማድረጉ፣ በወጥነት ሕግን እንዲከበር አለመሥራቱ፣ የተቀጣ ካለ እንኳን በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ለሕዝብ ይፋ አለማድረጋቸው ቁጥጥሩ ጠንክሮ የሕግ የበላይነት እንዲከበር አላስቻለም፡፡ ከሌሎች አገሮች የትራፊክ ሕግ መጣስ አንዳንዶች አልፎ አልፎ ሲፈጽሙት የሚስተዋሉት እንጂ ሁሉም በየዕለቱ ሲያፈርሰው የሚስተዋል አይደለም፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት የብዙኃኑን ጥቅም የሚነካ የመብት ጥሰት የሚከናወንበት እንደመሆኑ ጠንካራ ቅጣት፣ ክትትልና ቁጥጥር ኅብረተሰቡን የሚያስተምር፣ የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍንና ለሕግ ተገዥ የሆነ ባህልን የመፍጠሪያ ዐቢይ አጋጣሚ ነው፡፡ ሕግ ያለማክበሩ ፍጻሜ ሕግ ትንሽ ይሁን ትልቅ ሕግ ነው፡፡ የተሠራው የሰዎችን ጠባይ ለመግራት፣ የኅብረተሰቡን ሰላምና ሥርዓት ለመጠበቅ፣ ዘመናዊነትን/ሕግን ማክበርን ባህል ለማድረግ እንዲሁም እንዲፈጸም ነው፡፡ የትራንስፖርት ሕግም በየዕለቱ ሲጣስ ብንመለከትም እንዲፈጸም የወጣ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከዚህ አንፃር ትንሽ የምትባል የሕግ መጣስ አትኖርም፡፡ እንዲያውም በትንሿ የሕግ ጥሰት ያልተማረ ትልቅ የተባለውንም ለመጣስ ድፍረት ያገኛል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄው 15 ሳንቲም፣ 30 ሳንቲም የታክሲ ታሪፍን ለመግዛት የወጣችውን መመርያ ሊሆን ይገባል፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን እንደተናገረው ጥቃቅን ቀበሮዎች ካልተጠመዱ ሰፊውን የወይን እርሻ ያበላሹታል፡፡ በሕግ ደረቅ ቃል ደግሞ ሥርዓት አልበኝነት (Lawlessness) ይፈጠራል፡፡ እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሕጉ ካስቀመጠው መንገድ ውጪ ይጠቀማል፡፡ ሀብት ያለው በሀብቱ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ጥበብ ያለው በጥበቡ ያጋጠመውን ችግር ይወጣል እንጂ ሕግን ተከትሎና አቤቱታ አቅርቦ መፍትሔ ለማግኘት ትዕግስተኛ የሚሆን አይገኝም፡፡ ለዚህ የሕዝብ ትራንስፖርት በተለይ የታክሲ አገልግሎት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በታሪፉ የሚያስተናግደውን፣ መልስ የማይሰጠውን፣ ትርፍ እንዲጫንበት የሚያስገድደውን ረዳት ጉልበተኛው ተሳፋሪ በኃይለ ቃልና በጉልበት ይቀበለዋል፡፡ ጉልበት፣ አፍ እና ጥበብ የሌለው ደግሞ የተጠየቀውን ይከፍላል፣ የተሰጠውን ይቀበላል፣ ውረድ የተባለበት እንጂ ያልፈቀደው ቦታ ይወርዳል፡፡ ችግሩን በስፋት ተመልክተን ሕግ የማክበር ባህል እንዲፈጠር ካልሠራን ሥርዓተ አልበኝነት ይርፈድ እንጂ አይቀርም፡፡ ሕግ የማክበር ባህል እንዴት ይፈጠር? ለሕግ አለመከበር ምንጭ ያደረግናቸው ባለድርሻ አካላት ሕግ የማክበር ባህል በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲፈጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕግጋት ይዘታቸው የኅብረተሰቡን ባህልና ወግ እንዲጠብቁ በማድረግ ከሕዝብ ጋር ተመካክሮ ሕግጋቱን መቅረፅ፣ ሕግ የሚያስፈጽመውን አካል ጠንካራ አድርጎ ማደራጀት፣ ለሕግ ማስፈጸም የሚበቃውን የሰው ኃይል፣ የገንዘብ ድጋፍና ሥልጠና መስጠት፣ በተግባርም ሕግ የሚያስፈጽመው አካል የወጡትን ሕጎች ኅብረተሰቡን በማስተማር፣ ከሕግ የወጡትን በማረምና በመቅጣት መስመር መያዛቸውን እያረጋገጠ ስለመሆኑ መከታተልና መቆጣጠር ተገቢ ነው፡፡ ባለመብቱም መብቱን አውቆ መተግበር ካልቻለ የመብት ባለቤትነቱ ለይስሙላ ነው፡፡ የመብት ጥቅሙ የሚታወቀው በወረቀት ሕግ ተጽፎ ሳይሆን እንዳይጣስ ወይም ከተጣሰ በኋላ ሕግ አፍራሹን ተጠያቂ በማድረግ ነው፡፡ በቅርቡ በሪፖርተር ‘ይድረስ ለሪፖርተር’ ዓምድ ላይ ኢዮቤድ ጥበቡ የተባሉ ሰው ‹‹ሁሉም ሸማች ይወቀው›› በሚል የነገሩን እውነታ መብት መጠየቅን ያበረታታል፡፡ ግለሰቡ ለላውንደሪ የሰጡት ምንጣፍ የንጽህና አገልግሎቱን በሚሰጠው አካል በመቀደዱ/በመበላሸቱ ሸማቾች ጥበቃና ባለሥልጣን ክስ አቅርበው ምንጣፉን የሚተካ ካሳ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡ የዚህ ግለሰብ ጉዳይ መብትን ለሚጠይቅ ሰው ሞራላዊ ጥንካሬ ይሰጣል፡፡ ግዴታ ፈጻሚዎችም የግለሰቦችን መብት ማክበር የህሊና ሰላም እንደሚሰጥና ዘመናዊነት መሆኑን በመገንዘብ ግዴታ ቢያከብሩ ለሕግ የበላይነት ሰፊ ቦታ የሚሰጥ ባህል ይዳብራል፡፡ መብትና ግዴታ ተነፃፃሪና ለሁሉም ሰው የማይቀሩ ናቸው፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ፣ ቀበሌ ለሚሠራው ባለጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ታክሲ ላይ ያከበረው ግለሰብ ነገ ቢሮው ሲመጣ የሚያከብረው ግዴታውን ስለፈጸመ ብቻ ነው፡፡ ግዴታ በተደጋጋሚ አለመፈጸም የሚያሰጠው መልካም ያልሆነ ስም ሰብዕናን ይጎዳል፡፡ ግዴታ መፈጸም መንግሥት ለሕዝብ ትራንስፖርት ያስቀመጠውን ታሪፍ ማስከፈል የሕግ የበላይነትን ማክበርና ዘመናዊነትም ነው፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው lawandjustice140@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

❤❤
ReplyDelete