ሰው ከሳሽ ፍጡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለይበት ዐቢይ ነጥብ ከሳሽነቱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ (ሊሆንም ይችላል፡፡) የክሱና የከሳሹ ብዛት ብቻ ሳይሆን የክሱ ዓይነትና ይዘት ሰዎች ከሙግት ጋር ስላላቸው ጥብቅ ቁርኝት አስረጂ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በዓለማችን ላይ እጅግ በጣም በርካታ ፌዝ መሳይ ክሶች ቢኖሩም በእግዚአብሔርና በሰይጣን ላይ የቀረቡት ክሶች ግን በአውራነት ሊፈረጁ ይችላሉ፡፡ ነገሩ የፌዝ ቢመስልም ከሳሾቹ ግን የፌዝ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በእግዚአብሔር ላይ የክስ አቤቱታ አዘጋጅቶ ፋይል ያስከፈተው ግለሰብ አንቱ የተባለ የአሜሪካ ኔብራስካ ግዛት ሴናተር ነው፡፡ ግለሰቡ ኤርኒ ቻምበርስ (Ernie Chambers) ይባላል፡፡ ይህ ሰው በአሜሪካ ዳግላስ ካውንቲ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ በእግዚአብሔር ላይ ቋሚ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጠው ዳኝነት የጠየቀ ሲሆን በእግዚአብሔር ተፈጸሙ ያላቸውን በደሎችንም በክሱ ላይ ዘርዝሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እግዚአብሔር በዓለማችን ላይ ተንሰራፍቶ ያለውን የሰው ልጆች ስቃይ፤ ረሀብ፤ የተፈጥሮ አደጋ፤ ጦርነት፤ የመብት ረገጣ ወዘተ…ማስቆም አልቻለም የሚል ነው፡፡ ጉዳዩን ያዩት ዳኛ የቀረበውን ክስ በጥሞና ከመረመሩ በኋላ “እግዚአብሔርን በአድራሻው ፈልጎ መጥሪያውን ማድረስ ስለማይቻል” በሚል ምክንያት ክሱን ውድቅ አድርገውታል፡፡
በሰይጣን ላይ ክስ የቀረበው እ.ኤ.አ በ1971 ዓ.ም. ሲሆን ከሳሹም ጌራልድ ማዮ (Gerald Mayo) ይባላል፡፡ ከሳሽ በሰይጣንና ጀሌዎቹ ላይ ባቀረበው በዚሁ ክስ ሰይጣንና ጭፍራዎቹ ህገ መንግስታዊና ሰብዓው መብቶቹን በመጣስ በተደጋጋሚ አላስገባ አላስወጣ ብለው ነፃነቱንና የመኖር መብቱን እንደጣሱት በምሬት በመግለፅ ክቡር ፍርድ ቤቱ የዕግድ ትዕዛዝ ይሰጠው ዘንድ ተማፅኗል፡፡
ጉዳዩን የመረመሩት ዳኛ ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ ያደረጉት ቢሆንም በውሳኔያቸው ላይ ክሱን በቀላሉ አጣጥለው መዝገቡን ለመዝጋት አለፈለጉም፡፡ እያንዳንዱ ነጥብ እየተነሳ ከግራም ከቀኝም እየተዳሰሰ መዝገቡ በጥልቀት ተመርምሯል፡፡
በአጭሩ ለማስቀመጥ ፍርድ ቤቱ በሰይጣን ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ ሲያደርግ የሚከተሉትን ዐቢይ ምክንያቶች በማተት ነበር፡፡
የክስ ምክንያት
የከሳሽ መብት በእርግጥ ተረግጧል ቢባል እንኳን ፍርድ ቤቱ ሊያደርግ የሚችለው ማለትም ሊሰጠው የሚችለው መፍትሄ የለም፡፡ ፍርድ ቤት ሰይጣንን ምን ሊያደርገው ይችላል?
የተከሳሽ አድራሻ
ክሱ ይቅረብ ቢባል እንኳን ለሰይጣን መጥሪያ እንዴት ይደርሰዋል?
የቡድን ክስ
ሰይጣን የጀሌዎቹን ማለትም የጭፍሮቹን ጥቅም ሊያስጠብቅ እንደሚችል ሳይረጋገጥ ክሱን በዚህ መልኩ ማስኬድ አስቸጋሪ ነው፡፡ በውልና ማስረጃ የተረጋገጠ ውክልና ያለው ስለመሆኑም ማስረጃ አልቀረበም፡፡
ፍትሃዊነት
ተከሳሾች ችሎት ቢመጡ መጀመሪያ የሚያዩት ከዳኛው አናት ላይ “In God We Trust” የሚል በትልቁ የተፃፈ ፅሑፍ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተከሳሾች ፍትሃዊ ዳኝነት ያገኛሉ ተብሎ አይገመትም፡፡
“ስለሆነም የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገነዋል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ የይግባኝ መብት የተጠበቀ ነው፡፡”

No comments:
Post a Comment