28 Feb 2021

አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን ባህርያትና የስልጣን ምንጭ

አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን


ባህርያትና የስልጣን ምንጭ

አስተዳደራዊ ድንጋጌ ከህግ አውጭው በተሰጠ የውክልና ስልጣን ገደብ ውስጥ በስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካል የሚወጣ የበታች ህግ (subordinate legislation) ማለት ነው። በውክልና ህግ ማውጣት የአስተዳደር ህግ አይነተኛ መገለጫ ነው። የስራ አስፈፃሚው አካል ህግ የማውጣት ስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት የነፃ ገበያ ክስተትን ተከትሎ የመጣው ዘመናው የማህበራዊ ደህንነት መንግስት (welfare state) ካስመዘገባቸው እድገቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

በውክልና ህግ ለማውጣት የዋናው የህግ አውጭነት የስልጣን ባለቤት የሆነው የተወካዮች ም/ቤት በማያወላውልና ግልጽ በሆነ አነጋገር ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ወይም ለአስተዳደር መ/ቤቶች ካልሰጠ እነዚህ አካላት ከህገ መንግስት የመነጨ የህግ አውጭነት ስልጣን የላቸውም። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የሚኒስትሮች ም/ቤት ሆነ የአስተዳደር መ/ቤቶች ደንብና መመሪያ እንዲያወጡ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ስልጣን አይሰጣቸውም። በፌደራል ደረጃ ህግ የማውጣት ስልጣን የተወካዮች ም/ቤት ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ነው። ከዚህ ውጭ ህግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል በህገ-መንግስቱ ላይ የለም።

የውክልና ስልጣን በሌለበት ሁኔታ የሚወጣ ማንኛውም ደንብ ሆነ መመሪያ ከስልጣን በላይ እንደመሆኑ የህጋዊነት መስፈርትን አያሟላም። በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማው ፀድቆ ከታወጀ የሚኒስትሮች ም/ቤት ውስን ለሆነ ጊዜ ሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶችን ደንብ በማውጣት ሊገድብ ይችላል። ከዚህ ውጭ የሚኒስትሮች ም/ቤት በቀጥታ ደንብ ለማውጣት የሚችልበት ህገ መንግስታዊ ስልጣን የለውም።

የስልጣኑ ምንጩ የተወካዮች ም/ቤት ብቻ ነው ከተባለ ይህ አካል ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ማስተላለፍ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ ይህን የሚፈቅድለት ግልጽ ድንጋጌ የለም። ብዙዎች የመስኩ ምሁራን እንደሚስማሙበት ግን ህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል በውክልና ለማስተላለፍ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ስልጣን (inherent power) አለው። እንዲያም ሆኖ ያለገደብ ከህዝብ የተሰጠውን ስልጣን በውክልና ስም ሊያስተላልፍ አይችልም።

በመሰረቱ በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ ከመንግስት አስተዳደር እየተለጠጠ መምጣት ጋር ተያያዥ የሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡት ክስተት ነው። ስለሆነም እንደ ልዩ ሁኔታ እንጂ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት የለውም። ህግ አውጭው ምንም እንኳን በከፊል ስልጣኑን ማስተላለፍ ቢኖርበትም የፖሊሲ ጥያቄዎችን የሚነኩ መሰረታዊ ጉዳዮች በደንብ ወይም በመመሪያ እንዲወሰኑ ውክልና መስጠት የለበትም። የተፈጻሚነቱ ወሰኑ በህግ አውጪው በሚወጣው ህግ ላይ የሚታዩ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ብሎም የፖሊሲ ጥያቄዎችን በማይነኩ ዝርዝርና ጥቃቅን ቴክኒካል ጉዳዮች መገደብ አለበት። ከዚህ አንጻር አፈጻጸሙ በጠባቡ ሊሆን ይገባል።

አስፈላጊነት

ብቁና ውጤታማ አስተዳደር እንዲሰፍን የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን፣ ተግባርና ግዴታ በተጨባጭ ማሳካት ይጠበቅባቸዋል። ስኬት እንዲኖር ደግሞ የማስፈፀም ስልጣን ብቻውን በቂ አይሆንም። ጠቅለል ያለ ይዘት ያላቸው በፓርላማ የሚወጡ ህጐች የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ከመጠቆም ባለፈ ቴክኒካልና ዝርዝር ጉዳዮችን ስለማይዳስሱ በየጊዜው ለሚነሱ ችግሮች ወቅታዊና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ይሳናቸዋል። ስለሆነም አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን አስፈላጊነት ከሁለት አቅጣጫዎች ማለትም ከአስተዳደር ስራ ውጤታማነት እና ከህግ አውጭው ውስንነት አንፃር ሊቃኝ ይችላል።

አስፈላጊነቱ ጎልቶ ቢታይም በመስኩ ሊቃውንት ጠንካራ ተቃውሞ ሳይገጥመው አልቀረም። እንደ ብዙዎች እምነት የአስተዳደር መ/ቤቶች ህግ የማውጣት ስልጣን በዜጐች መብት ላይ በሩን ዘግቶ ወደ አምባገነናዊነት የሚያመራ አደገኛ አካሄድ ነው። ተቃውሞው መሰረቱ ንድፈ ሀሳባዊ ሲሆን የስልጣን ኢ-ተወካይነት ንድፈ ሀሳብ (theory of non delegability of power) አንዱ ነው። በላቲን potestas delegari non potest delegare ተብሎ ሲጠራ በእንግሲዝኛው power once delegated should not be re-delegated የሚል ይዘት አለው። ይህም ወደ አማርኛ ሲመለስ ‘በውክልና የተሰጠ ስልጣን እንደገና በውክልና ሊተላለፍ አይችልም’ እንደ ማለት ነው። በአጭር አገላለፅ ህግ አውጭው ህግ የማውጣት ስልጣኑን የሚያገኘው ከመራጩ ህዝብ እንደመሆኑ ይህን በአደራ የተቀበለውን ስልጣን እንደገና (በድጋሚ) በውክልና ማስተላለፍ የለበትም ማለት ነው።a

የህግ አውጭነት የስልጣን ምንጩ ህዝብ ነው። የአንድ አገር ህዝብ ተወካዮቹን ሲመርጥ ችሎታና ብቃታቸውን መሰረት አድርጐ ‘ያስተዳድሩኛል፤ ለእኔ ይሰሩልኛል፣ ትክክለኛውን ህግ ያወጡልኛል’ በሚል እምነት ጥሎባቸው ነው። ህግ አውጭው በውክልና በአደራ ከህዝቡ የተቀበለውን ስልጣን በአግባቡ በመገልገል ልማት፤ እድገት፤ ፍትህ፣ መልካም ስርዓትና ሰላም የሚያሰፍኑ ህጐችን ማውጣት አለበት። ህዝቡ ድምፁን ሰጥቶ ተወካዮቹን ሲመርጥና ስልጣን ሲሰጥ ይህን የህግ አውጭነት ስልጣን ላልተመረጡ ግን ለተሾሙ ስራ አስፈፃሚዎች በውክልና እንዲያስተላልፉት አይደለም። ከዚህ ሀሳብ በተቃራኒ ስልጣን በውክልና ከተላለፈ ህዝቡ ድምፅ ሰጥቶ ባልመረጣቸው ስራ አስፈፃሚዎች እየተገዛ ነው።

ሁለተኛው የውክልና ህግ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ክፍፍል መርህ (separation of powers) የሚነሳ ሲሆን ዞሮ ዞሮ መሰረቱ የአስተዳደር በደል እንዲንሰራፋ ያደርጋል የሚል ነው። በስልጣን ክፍፍል መርህ መሰረት ህግ ማውጣት ለህግ አውጭው፤ ህግ መተርጐም ለፍርድ ሰጭው፤ ህግ ማስፈፀም ለአስፈፃሚ ተብሎ የእያንዳንዱ የመንግስት አካል ስልጣኑ ተመድቦና ተለይቶ ተሰጥቷል። አንድ የመንግስት አካል በተደራራቢነት ከአንድ በላይ ስልጣን የያዘ እንደሆነ ከራሱ በላይ ተቆጣጣሪ የሌለው ስልጣኑን እንዳሻው የሚጠቀም አምባገነን ይሆናል። ስለሆነም ስራ አስፈፃሚው ከተመደበለት ህግ የማስፈፀም ተግባር በተጨማሪ በደንብና መመሪያ ስም ህግ የሚያወጣ ከሆነ ሁለት የመንግስት ስልጣናትን ደርቦ ስለመያዙ ያም የስልጣን ክፍፍል መርህን መጣሱ ግልጽነቱ ጐልቶ የሚታይ ሀቅ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ንድፈ ሀሳብ ተቃውሞዎች መሰረት በውክልና የሚወጣ ህግ አስተዳደራዊ አምባገነናዊነት፤ የአስተዳደር ብልሹነት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል እንዲሰራፋ ያደርጋል በሚል ከመስኩ ባለሙያዎች የሰላ ሂስና ትችት ሲገጥመው ቆይቷል። ለምሳሌ እንግሊዝ አገር ውስጥ ሎርድ ሄዋርት የተባሉ የተከበሩ ዳኛና ምሁር በአገራቸው በየጊዜው በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ‘The New Despotism’ በሚለው መጽሐፋቸው እ.ኤ.አ. በ1931 ዓ.ም. ያቀረቡት ጠንካራ ተቃውሞ የእንግሊዝ ፓርላማ ስለጉዳዩ የሚያጠና አጣሪ እንዲሾምና ምርመራ እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል።b ይሁን እንጂ ከምርመራው በኋላ የቀረበው የምርመራ ሪፖርት (Committee on Ministers’ Powers Report) የደረሰበት ድምዳሜ የውክልና ህግ እንግሊዝ ውስጥ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ይህም በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለው ካተተ በኋላ በተግባር ግን የግድ አስፈላጊና መቅረት የሌለበት አሰራር መሆኑን በአጽንኦት ገልጿል።c

ከላይ የቀረቡት ንድፍ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞዎች አሳማኝ የመሆናቸውን ያህል እየተወሳሰበ ከመጣው የመንግስት አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግባራዊ ምክንያቶች አስፈላጊነቱን አይቀሬና የበለጠ አሳማኝ አድርገውታል። የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ አውጭው በሚወጡት አዋጆች ላይ ብቻ ተንተርሰው ውጤታማ አስተዳደር ማስፈን አይቻላቸውም። በተለያዩ አገራት እንደታየው ህግ አውጭው ከሚያወጣቸው ህጐች በበለጠ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚያወጧቸው መመሪያዎች በፍጥነት እየበዙ መጥተዋል።d በየጊዜው እያደገና እየተወሳሰበ የመጣው የመንግስት አስተዳደር ስራና የህግ አውጭው ለዚህ ስራ ውጤታማነት የሚያግዙ ህጐችን በአይነትና በጥራት ለማቅረብ አለመቻል በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ አማራጭ ሳይሆን የግድ መሆኑን ያሳየናል።

ለዚህም ይመስላል ታዋቂው የአስተዳደር ህግ ምሁር ደብሊው ኤች. አር. ዌድ በውክልና የሚወጣ ህግን “መጥፎ ግን አስፈላጊ” (necessary evil) ሲል የሚገልፀው።e ከህግ አውጭው በሚሰጥ ውክልና ህግ የማውጣት ስልጣንን በተግባር አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

የጊዜ እጥረት

ህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ለማስተላፍ ከሚገደድባቸው ምክንያቶች አንዱ ከራሱ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ችግር ነው። አንድን አዋጅ ለመደንገግ ከሚወስደው ረጅም ጊዜና ተፈጻሚ ከሚሆነው የጠበቀ የስነ-ስርዓት አካሄድ አንጻር ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ህጐችን በብዛትና በጥራት ለማውጣት አስቸጋሪ ነው።f የተወካዮች ም/ቤትን ያየን እንደሆነ ከሁለት ወራት የክረምት የእረፍት ጊዜ በኋላ በመካከል ለአንድ ወር ለእረፍት ሲበተን ጠቅላላ የስራ ጊዜው ከዘጠኝ ወራት አይበልጥም።g ከዘጠኙ ወራት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ተቀንሰው በሚቀሩት የስራ ቀናት ባሉት አጭር የስራ ሰዓታት ለአገሪቱ አስፈላጊ አዋጆችን ማውጣት አዳጋች ነው። የመስኩ ምሁራን እንደሚስማሙበት የአንድ አገር ፓርላማ ለተከታታይ 365 ቀናት ድፍን 24 ሰዓታት በስራ ላይ ቢቆይ እንኳን በብዛትና በጥራት ለአገሪቱ አስፈላጊ የሆኑ ህጐችን ማቅረብ ይሳነዋል።h

በተወሰኑ ዘርፎች የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው አዋጆች እና በውክልና የወጡ መመሪያዎች ቁጥር ብናነጻጽር ከጊዜ እጥረት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በተግባራዊ ምልከታ ለመመዘን ያስችለናል። ምክር ቤቱ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ቀረጥና ታክስ በሚመለከት (ማሻሻያዎችን ጨምሮ) ያወጣቸው አዋጆች በቁጥር ከ25 አይበልጡም። በዚህ ጊዜ ውስጥ እነዚህን ህጎች ለማስፈጸም በተለያየ ቅርጽና ስያሜ ተዋቅረው በነበሩትና በኋላም ከሐምሌ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ስልጣናቸውን አዋህዶ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በመባል ይታወቅ የነበረው (አሁን ላይ መ/ቤቱ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በሚል ለሁለት ተሰንጥቋል።) መ/ቤት በውክልና ስልጣኑ 129i መመሪያዎች ወጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁ የባንክ፣ የመድን፣ የአነስተኛ ፋይናንስ እና የካፒታል ዕቃ ኪራይ ስራዎችን ለመቆጣጠር ከወጡ ወደ ሰባት የሚጠጉ አዋጆችና በሌሎች ልዩ ህጎች በተሰጠው ስልጣን ከ110 በላይ መመሪያዎችን አውጥቷል።j ሌሎች የአስተዳደር መ/ቤቶች እያንዳንዳቸው በቁጥር ወደ 100 የሚጠጉ መመሪያዎች ባይኖራቸውም ከብዛታቸው አንጻር ጠቅላላ ድምሩ ከ1000 ያልፋል። በዚህ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እስከ ጥር 2011 ዓ.ም. ድረስ ያወጣቸውን 447 ደንቦች ስንጨምርበት በውክልና ስልጣን የሚወጡ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ቁጥር ወደ ላይ በጣም ያሻቅባል።

የተወካዮች ምክር ቤት እስከ ነሀሴ 2008 ዓ.ም. ድረስ ካወጣቸው አዋጆች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአጭር ጊዜ የሚወጡ ዓለም ዓቀፍና የሁለትዮሽ ስምምነቶችና የብድር ማፅደቂያ አዋጆች ናቸው። ስለሆነም ም/ቤቱ ሁሉንም ደንቦችና መመሪያዎች ራሱ ለመደንገግ ቢወስን በተግባር ሊወጣው አይችልም።

የእውቀት እጥረት

የህዝብ ተመራጮች ለመመረጣቸው ምክንያት እውቀት ወይም ብቃት አንዱ መለኪያ ቢሆንም ዋናው መስፈርት ግን በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታና ተቀባይነት ነው። በጠቅላላ ጉዳዮች ጠቅላላ እውቀት ይኖራቸዋል ብለን ብንገምት እንኳን ከመንግስት አስተዳደር ውስብስብነት አንፃር ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ የበለጠ እውቀትና ችሎታ ያለው በአስተዳደር መ/ቤቶች ዘንድ ነው።k ስለሆነም ፓርላማው ትኩረቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ዝርዝር የአፈፃፀም ስልት የሚጠይቁ ቴክኒካል ጉዳዮች በደንብና በመመሪያ እንዲወሰኑ ስልጣኑን በውክልና ማስተላለፍ የግድ ይለዋል።l የእውቀት እጥረት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር መ/ቤቶች በተቋቋሙለት ዓላማ ስር ልዩና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራታቸው ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ተመራጭም ያደርገዋል።

ምሳሌ ብንጠቅስ የያኔው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ልውጥ ህያዋንን /modified organisms/ አስመልክቶ ካወጣቸው ስድስት መመሪያዎች መካከል ‘የልውጥ ህያዋን ያልተጤነ ልቀት መቋቋምን ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁ. 06/2001’ አንደኛው ነው። መመሪያ የወጣበት ጉዳይ የጠለቀ ሳይንሳዊ ዕውቀት ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት ደግሞ በተወካዮች ምክር ቤት ዘንድ አይገኝም።

ተለዋዋጭ ሁኔታ

አንድ ህግ ፀድቆ ከወጣ በኃላ ወደፊት ለሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ በቂ ምላሽ አይሰጥም። መሰረታዊው ችግር እልባት ቢያገኝ እንኳን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጠሩ የአፈጻጸም ችግሮች ይኖራሉ። የህግ አውጭው የህግ አወጣጥ ስነ-ስርዓት የጠበቀና ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ አንጻር በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከተለዋዋጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች አንጻር በተከታታይ አዋጅ በማውጣት ምላሽ መስጠት አይታሰብም። በተቃራኒው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስነ-ስርዓት እጅጉን የቀለለ እንደመሆኑ ችግሮችን እየተከታተሉ አግባብነት ያለው መፍትሔ ለመቀየስ ያስችላል።m በሌላ አነጋገር ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መፍትሔ ለመስጠት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል።

ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ፣ ነዋሪ ያልሆኑና ለጉብኝት የመጡ ሰዎች ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ የሚይዝበትንና ወይም በውጭ ምንዛሪ ክፍያ የሚፈጽምበትን ወይም የክፍያ ማዘዣዎችን የሚይዝበትንና የሚጠቀምበትን ሁኔታዎችና ገደቦች በመመሪያ እንዲወስን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስልጣን ተሰጥቶታል።n እነዚህ ሁኔታዎችና ገደቦች በጊዜ ሂደት የሚለዋወጡ እንደመሆናቸው የተወካዮች ምክር ቤት በቅርበት እየተከታተለ በየጊዜው አዋጅ በማውጣት ቁጥጥር ለማድረግ የህግ አወጣጥ ስርዓቱ አይፈቅድለትም።

አስቸኳይ ሁኔታ

አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ሲያጋጥም አዋጅ ለማውጣት ከሚያስፈልገው ረጅም ጊዜ አንጻር ፈጣን ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ነው። በተቃራኒው ደንብና መመሪያ በአንድ ሳምንት ምናልባትም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ሊወጣ ይችላል። ስለሆነም ልዩና አስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ከፓርላማው ይልቅ ስራ አስፈፃሚው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ሊኖረው ይገባል።

ከአስቸኳይነት ጋር ተያያዞ ምስጢራዊነት ሌላው ውክልናን አስፈላጊ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንደኛው ነው። የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝነቱ ባያጠያይቅም ከፊል በሆኑ ሁኔታዎች በአስቸኳይ ሊወሰዱ የታሰቡ እርምጃዎች ደንብና መመሪያው ከመፅናቱ በፊት ቀድመው ከታወቁ ሊሳካ የታሰበው ግብ ይሰናከላል። የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ የተፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራት ስርዓት ለማስያዝ በሚል በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የወጣው መመሪያo ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። መመሪያው በሽንሸና ቤቱን ከተከራየው ግለሰብ የተከራዩ ሰዎች በራሳቸው ስም ከኤጀንሲው ጋር ውል እንዲገቡ ይፈቅዳል። ኤጀንሲው ሊወስደው ያሰበው እርምጃ ቀድሞ ቢታወቅ መመሪያው ሊያሳካ ያሰበው ግብ ይከሽፋል።

ህገ መንግስታዊ ገደብ

በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን የአስፈላጊነቱ አጥጋቢ ምክንያት ተግባራዊ ችግሮች ቢሆኑም የመንግስት አስተዳደርን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ራሱን የቻለ የጐላ ጥቅም አለው። በእርግጥ የስልጣን አምባገነንነትን ሊያስከትል ከመቻሉ የተነሳ የራሱ አደጋዎችም አሉት። አደጋውና አላስፈላጊ ጐኑ ሊወገድ የሚችለው ልኩ ተለይቶ በታወቀ ገደብ ውሰጥ ተግባር ላይ የዋለ እንደሆነ ነው። ውክልናው ግልጽ፣ የማያሻማ፣ ጠባብና ገደብ የተሰመረለት ሊሆን ይገባዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ህግ የማውጣት ስልጣን ለተወካዮች ም/ቤት እንደተሰጠ በግልፅ ይደነግጋል።p ይህ ስልጣን በውክልና እንዲተላለፍ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ ግን አልሰፈረም። ስልጣኑን በውክልና እንዲያስተላልፍ የሚፈቅድለት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ባይኖርም የተለያዩ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ውክልና ቢያንስ በተዘዋዋሪ የተከለከለ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል። በተለይ አግባብነት ያለው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል። ከዚህ አንጻር የተጠቀሰው ድንጋጌ ህግ የማውጣት ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ ኢ- ህገ መንግስታዊ ስላለመሆኑ በቂ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

ለአስተዳደር ህግ አስጨናቂው ጥያቄ ህገ መንግስቱ የተወካዮች ም/ቤት በውክልና ስልጣኑን እንዲያስተላልፍ የመፍቀዱ ነገር ሳይሆን በውክልና ሊተላለፍ የሚችለው ስልጣን ወሰንና ገደቡ የትላይ ነው? የሚለው ነው። ህግ አውጭው በህዝብ የተመረጠው ህግ ለማውጣት ነው። ስለሆነም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ያለገደብ ወይም ሙሉ በሙሉ ለአስፈፃሚው አካል ማስተላለፍ የለበትም።

በውክልና የማይተላለፉ ጉዳዮች

በውክልና የማይተላለፉ ጉዳዮችን በተመለከተ ህገ መንግስቱ የመለሰው ጥያቄ አይደለም። በመርህ ደረጃ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን በውክልና ስም ሊተላለፍ አይችልም። ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብትን በቀጥታ የሚነኩ ጉዳዮች፣ የፖሊሲ ጥያቄዎች እና ግብር መጣልን የመሳሰሉ ተግባራት በመመሪያ ሆነ በደንብ ሊወሰኑ አይገባም። የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ በመመሪያ እንዲያወጣ፣ እንዲያሻሽል ወይም እንዲሽር ስልጣን የሚሰጥ ህግ ኢ-ህጉ መንግስታዊነቱ ፈጦ ይታያል። ምክንያቱም ጉዳዩ ለፖርላማ ቀርቦ በህዝብ በተመረጠ አካል ውሳኔ ሊያገኝበት ይገባልና። ከመላምታዊ ምሳሌው ባሻገር ይህን መሰል ጥያቄዎች በተግባር ሲመጡ የውክልናውን የስልጣን ገደብን ማስቀመጡ በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይ ይህን አስመልክቶ የተቀመጠ ህገ- መንግስታዊ ድንጋጌ አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል።

የውክልና ወሰንና ገደቡ የት ላይ ነው? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አንገብጋቢ ነው። ምክንያቱም ጥያቄው የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ ነውና። በአጠቃላይ አነጋገር በመሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣንና በዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮች መካከል ያለው መለያ መስመር የውክልናውን ገደብ ይወስናል።q በእንግሊዝ ፓርላማው ሉዓላዊ እንደመሆኑ በህገ መንግስታዊ ገደብ አይታሰርም። ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት በዳበሩ ልምዶች በውክልና ሊተላለፉ የማይችሉ ጉዳዮች እየተለዩ መጥተዋል። በህንድም እንደዚሁ ህገ መንግስቱ በግልፅ ውክልናን ባይፈቅድም ኢ-ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ በህንድ ፍ/ቤቶች አቋም ተይዞበታል። ሆኖም የገደቡ ልክ ወጥ መስፈርት አልተገኘለትም።

ህገ መንግስታዊ ወሰንን አስመልክቶ በሌሎች አገራት ፍ/ቤቶች በተለይም በህንድ ፍ/ቤቶች ከተሰጡ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው መሰረታዊ ህግ የማውጣት ተግባር በውክልና ሊተላለፍ አይችልም።r መሰረታዊ የህግ ማውጣት ተግባር ማለት የአዋጁን ዓላማ ወይም ፖሊሲ ለይቶ ማስቀመጥና አስገዳጅነት ባለው ህግ መደንገግ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ህግ አውጭው ደንብና መመሪያውን ለሚያወጣው አካል በቂ ማብራሪያ ሊሆን የሚችል የህግ ማውጣት ፖሊሲ ወይም የአዋጁን ዓላማ ማስቀመጥ ይኖርበታል። የህጉ ፖሊሲ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከአዋጁ መግቢያ (preamble)፣ ርዕስ፣ ግብ ወይም ምክንያት ሊገኝ ይችላል። በተጨማሪም በውክልና የተሰጠው ስልጣን በአግባቡ ለተፈለገበት ዓላማ ስለመዋሉና አውጭው አካል ከስልጣኑ አልፎ ስላለመሄዱ የሚረጋገጠበት በቂ የመቆጣጠሪያ ስርዓት በቅድሚያ መዘርጋት ይኖርበታል።

በውክልና ሊተላለፉ አይገባም ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን ነው።s በአገራችን ይህ ስልጣን በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል የተከፋፈለ ሲሆን በፌደራል ደረጃ ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን የተሰጠው ለተወካዮች ም/ቤት ነው።t ከዚህ ውጭ በሚኒስትሮች ም/ቤት ሆነ በየትኛውም የአስተዳደር መ/ቤት የሚጣል ቀረጥና ግብር ህገ መንግስታዊ የንብረት መብትን ይጥሳል። በእንግሊዝu እና በህንድv ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን መሰረታዊ ከሚባሉት የህግ ማውጣት ተግባራት መካከል የሚፈረጅ ሲሆን ጥብቅ ከለላም ይደረግለታል። በተመሳሳይ መልኩ ሰብዓዊ መብቶችን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካ ጉዳይም እንዲሁ በደንብ ወይም በመመሪያ ሊወሰን አይችልም።

በህግ አውጪው የወጣን ህግ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ፣ ማሻሻል፣ የተፈፃሚነቱን ሽፋን ማጥበብ ወይም ማስፋት ሌላው የልቅ ውክልና ምሳሌ ተደርጐ ይወሰዳል። በእንግሊዝ ስራ አስፈፃሚው ነባር ህግ እንዲያሻሽል ወይም ተፈጻሚነቱን እንዲያስቀር ስልጣን የሚሰጥ የህግ አንቀጽ ‘የሄነር ስምንተኛ አንቀጽ’ (Henry viii clause)w (ወደ አማርኛ አጠጋግተን ስንመልሰው ደግሞ ‘የእንዳሻው አንቀፅ’) ይባላል። የዚህ ምክንያቱ ንጉሱ በፓርላማ የወጡ ህጐችን የመሻር ስልጣን ስለነበረው ነው።

በተግባር እንደሚታየው ግን በህግ አውጭው የወጣን ህግ በከፊል የተፈፃሚነቱን ወሰን የማጥበብና የማስፋት ስልጣን አልፎ አልፎ በውክልና ይተላለፋል። እስከ አሁን ድረስ የተወካዮች ም/ቤት ራሱ ያወጣውን አዋጅ በደንብ ወይም በመመሪያ በከፊል ወይም በሙሉ እንዲሻሻል ሆነ እንዲሰረዝ ስልጣን የሰጠበት አጋጣሚ ባይኖርም የተፈጻሚነት ወሰኑን ማጥበብና ማስፋት በተመለከተ ግን አልፎ አልፎ በደንብ እንዲወሰን ውክልና ይሰጣል።x

የአስተዳደር መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣን

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህግ አውጭነት ስልጣን በህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት ገደቦች አልተገታም። የተወካዮች ምክር ቤትም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ለማስጠበቅ አቅም ያጣ ይመስላል። በውክልና ሰበብ የሚወጡትን ደንቦች ሊቆጣጠር ቀርቶ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣኑን ጭምር እያጋራ ይገኛል። በ2001 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁ. 603/2001y የተወካዮች ምክር ቤት የውክልና ዲሞክራሲን መርህ ከስሩ የሚንድ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ለሚኒስትሮች ም/ቤት አስተላልፏል። ይኸው አዋጅ በአዋጅ ቁ. 691/2001 እና በአዋጅ ቁ. 916/2008 ቀጥሎም በአዋጅ ቁ. 1097/2011 ተተክቷል። በእነዚህ ህጎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት መነሻና መድረሻ የሌለው የህግ አውጭነት ስልጣን ተጎናጽፏል። በሶስቱም ህጎች የሚገኘው ድንጋጌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት፣ ማንኛውም አስፈፃሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈፃሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም እንዲከፋፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈፃሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን እንዲኖረው በመፍቀድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያልተገደበ የስልጣን ባለቤት አድርጎታል።

እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ስልጣን በ1923 ዓ.ም. ህገ መንግስት አንቀጽ 11 እና 34 እንዲሁም በ1948 ዓ.ም. ህገ መንግስት አንቀጽ 27 ንጉሱ አላስነካም ብለው በብቸኝነት ይዘውት ነበር። በ1980 ዓ.ም. በቆመው የደርግ ህገ መንግሰት እንዲሁ መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣን በተዘዋዋሪ ከስራ አስፈፃሚው እጅ አልወጣም። በአንቀጽ 82/3/፣ 83/1/ እና 86/4/ በተሰጣቸው ስልጣን ዋናዎቹ ህግ አውጭዎች ምክር ቤቱ (Council of State) እና ፕሬዚዳንቱ ነበሩ። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ግን የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን የአስተዳደር ተቋማትን አደረጃጀት ከመወሰን እንዳያልፍ ገድቦታል። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 77/2/ እንደሰፈረው የሚኒስትሮች ም/ቤት የሚኒስቴሮችንና በቀጥታ ለራሱ ተጠሪ የሆኑ የመንግስት አካላት አደረጃጀት (በእንግሊዝኛው ቅጂ organizational structure) ይወስናል። አደረጃጀት ሲባል የአንድን ተቋም ውስጣዊ መዋቅር ይመለከታል። ማቋቋም፣ ማጠፍ፣ ማዋሃድ፣ መከፋፈል እንዲሁም ስልጣንና ተግባር መለወጥ በህዝብ ከተመረጡ ተወካዮች እጅ መውጣት የሌለበት መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ነው።

በውክልና ዲሞክራሲ መርህ መሰረት የሁሉም ስልጣን መነሻ እና ባለቤት የሆነው ህዝብ የሚያስተዳድሩትን ተወካዮች ሲመርጥ በምርጫው (ወዶና ፈቅዶ) በውክልና ስልጣኑን ያስረክባቸዋል። በህዝብ ያልተመረጡ የመንግስት ባለስልጣናት እና ሹመኞች ከእነዚህ የህዝብ ተወካዮች በከፊል ተቆርሶ ከሚሰጣቸው ስልጣን በስተቀር ከሌላ ምንጭ የሚያገኙት ስልጣን የለም። ሆኖም የተሻሩትን ጨምሮ አዋጅ ቁ. 1097/2011 ስራ አስፈጻው ራሱ ስልጣን ሰጪ ራሱ ተቀባይ እንዲሆን በማድረግ ህግ አውጭውን ከተወካዮች ም/ቤት ወደ ‘ወካዮች ም/ቤት’ አሳንሰውታል።

የአስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የመሻት ቀዳሚ ኃላፊነት የተጣለባቸው በየዘርፉ የተቋቋሙት የአስተዳደር መ/ቤቶች ናቸው። ከትምህርት አሰጣጥ ወይም ጥራት ጋር የተያያዘ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ሲከሰት የትምህርት ሚኒስቴር እንቅስቃሴ ይጀምራል። በጉምሩክ ህግ አፈጻጸም አቤቱታዎች ሲጎርፉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መፍትሔ ያፈላልጋል። በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ላይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ትኩረት ሰጥቶ ስራ ይጀምራል። ችግሮችን ለመቅረፍ መላ መዘየድ ችግር የለውም፤ እንዲያውም ይበረታታል።

ይሁን እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች ሊቀረፉ የሚገባው በህግና በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው። ከፊል ጉዳዮች የተወካዮች ም/ቤትን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ። የአስተዳደር መ/ቤቶች ችግር ፈቺነት በህግ ከተፈቀደላቸው ስልጣን በላይ ሊለጠጥ አይችልም። አዋጅ ሊመልሰው የሚገባውን መመሪያ ከቀደመው መ/ቤቶች ችግር ፈቺ መሆናቸው ቀርቶ ችግር ፈጣሪ ይሆናሉ። የአስተዳደር ድንጋጌዎች መመዘኛ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ህጋዊነት ነው። የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ተወካዮች ሊመክሩበትና ሊፈቱት የሚገባውን ችግር ተሿሚዎች በመመሪያ ለመቅረፍ መሽቀዳደም የለባቸውም። ከላይ የቀረበውን ሀሳብ በተጨባጭ የሚያሳዩ ጥቂት አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይጠቀሳሉ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓት

በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓትን በሚመለከት የትምህርት ሚኒስቴር በ2000 ዓ.ም. መመሪያ አውጥቷል።z መመሪያው ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ድረስ በሁሉም የትምህርት ተቋማት ተፈጻሚ የሚሆነውን የአምልኮ፣ የአለባበስ እና የአመጋገብ ስርዓት ይደነግጋል። በአንቀጽ 6.2 እስከ 6.6 ድረስ ከተፈቀዱና ከተከለከሉ ተግባራት መካከል እንደ ቅደም ተከተሉ የሚከተሉት ይገኙበታል።

6.2 የተማሪ ደንብ ልብስ በማያስፈልጋቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሁኔታው በወርክሾፕ፣ በላቦራቶሪ፣ ወይም በህክምና ትምህርት ተቋማት ሙያው ወይም ስልጣናው የሚፈልገው አይነትና የአንዱን ወይም የሌላውን እምነት የማይጋፋ የአለባበስ ስርዓት መከበር ይኖርበታል።

6.3 የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ከዩኒፎርም ጋር የሚመሳሰል “ሂጃብ” ማድረግ ይችላሉ፤ ከሂጃብ በቀር ሙሉ ጥቁር ልብስ ሙሉ በሙሉ ፊትንም ጨምሮ የሚሸፍን ወይም “ኒቃብ” በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም።

6.4 የክርስትና እምነት ተከታይ መነኮሳት፤ መነኮሳያይት እና ካህናት እንዲሁም የእስልምና ተከታይ ሼኮች ብቻ በትምህርት ተቋማት ቆብ ሊያደርጉ ወይም ሻሽ ሊጠመጥሙ ይችላሉ።

6.5 በተራ ቁጥር 6.2፤ 6.3፤ 6.4 የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው፤ የትምህርት ተቋማት በሚያዘጋጁት ክብረ በዓል ወይም ተመሳሳይ ጉዳዮች ምክንያት በተቋሙ አስተዳደር ሃይማኖታዊ አለባበሶች ካልተፈቀዱ በስተቀር በማንኛውም መልኩ የማንኛውንም የሃይማኖት የአለባበስ ስርዓት በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም።

6.6 በተራ ቁጥር 6.2፤ 6.3፤ 6.4 የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለየ ሁኔታ የትምህርት ተቋሙ አስተዳደር (በሀዘን፣ በህመም ወዘተ) ከሚፈቅደው በስተቀር ተማሪዎች በመማሪያ ክፍል ውስጥ ነጠላ፣ ጋቢ ወዘተ… መልበስ ሻሽ መጠምጠምና ቆብ ማድረግ የተከለከለ ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያውን ለማውጣት የስልጣኑን ምንጭ በጊዜው ፀንቶ የነበረውን የኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 471/1998 እንደሆነ ይጠቅሳል። በአዋጁ አንቀጽ 14 የትምህርት ሚኒስቴር የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት አሉት።

የትምህርት ስልጠና ስታንዳርድ ያወጣል። ሥራ ላይ መዋሉንም ያረጋግጣል።

የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፣

ሀ) አጠቃላይ የስርዓተ ትምህርት ማእቀፍ ያዘጋጃል።

ለ) ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን አነስተኛውን የትምህርት ብቃት መለኪያ ያወጣል።

ሐ) በሙያና ቴክኒክ ዘርፍ የሙያ ስልጠና ደረጃና የብቃት ማረጋገጫ ደረጃ ያወጣል።

መ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያሟሉ የሚገባቸውን አነስተኛውን ደረጃ ያወጣል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ያቋቁማል፣ ያስፋፋል፤ ዕውቅና ይሰጣል፣ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት መስጠታቸውን ይቆጣጠራል።

ትምህርትና ስልጠናን በተመለከተ አገራዊ የአህዝቦት (በእንግሊዝኛው ቅጂ ‘popularization’) ተግባሮችን ያከናውናል።

ከላይ የተዘረዘሩት ስልጣንና ተግባራት መመሪያውን ለማውጣት ስልጣን እንደሚያጎናጽፉ ድምዳሜ ከመያዙ በፊት አንድ መሰረታዊ ነጥብ መነሳት ይኖርበታል። ይኸውም፤ ማንኛውም መ/ቤት ከተቋምነቱ ወይም ከአጠቃላይ ስልጣንና ተግባራቱ የመነጨ መመሪያ የመደንገግ ስልጣን (inherent rulemaking power) የለውም። እያንዳንዱ ተቋም የስልጣኑ ምንጭ የተወካዮች ም/ቤት ውክልና እንደሆነ መቼም መዘንጋት የለበትም። የትምህርት ሚኒስቴር ሊጠቅስ የሚገባው ውክልና የሰጠውን የህግ ድንጋጌ ነው። ስለሆነም ውክልና በሌለበት በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓትን በሚመለከት መመሪያ መደንገግ ከስልጣን በላይ የሆነ ተግባር በመሆኑ መመሪያው የህጋዊነት መስፈርት አያሟላም።

በተጨማሪም የአዋጅ ቁ. 471/1998 አንቀጽ 14 ድንጋጌ ይዘት የአምልኮ ስርዓት በትምህርት ሚኒስቴር እንዲወሰን አይፈቅድም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያው በክልል መንግስታት ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ጭምር አካቷል። በመመሪያው የትርጓሜ ክፍል የትምህርት ተቋማት የተባሉት ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ያሉትን በሙሉ ያጠቃልላል። የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር፣ የትምህርት አሰጣጥ፣ የመምህራን አቀጣጠርና አስተዳደር በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር ስልጣን የትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር በወጣው (ማሻሻያ) አዋጅ ቁ. 217/1992 አንቀጽ 1 ተሽሮ ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ለአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች ተላልፏል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የአምልኮ ስርዓቱን በተመለከተ በህግ መወሰን/ያለመወሰን ስልጣኑም የእነዚህ አካላት ነው።

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች አስተዳዳር

ፍትህ የማግኘት መብትን የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀፅ 37/1/ እንደሚከተለው ይነበባል።

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 በልዩ ሁኔታ ሰራተኞችን ማሰናበትን በተመለከተ በአንቀጽ 37 እንደሚከተለው ደንግጓል።

1) በዚህ ደንብ በሌላ ሁኔታ የተደነገገው ቢኖርም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ሰራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈፃፀም ስርዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናበት ይችላል።

2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ስራ መመለስ አይችልም።

የህገ መንግስቱና የደንብ ቁ. 155/2000 ድንጋጌዎች በስም (አንቀጽ ቁጥር) ይመሳሰላሉ። በተግባር ግን ተጻራሪ ናቸው። የመጀመሪያው መብት ያናጽፋል፤ ሁለተኛው ይነፍጋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ ከተጣለባቸው አካላት መካከል አንደኛው ነው። በዚህ ግዴታው የህግ አውጭነት ስልጣኑ ምንጭ የሆነው ህግ ያሰመረለትን ወሰን ሊያከብር ይገባል። ምክር ቤቱ ደንብ ቁ. 155/2000 ለማውጣት ህግ እንደፈቀደለት የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ አዋጅ ቁ. 587/2000 አንቀጽ 19/1/ ለ ድንጋጌ ነው። ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል።

[የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን] ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይመራል።

በስልጣን ምንጭነት የተጠቀሰው ህግ ም/ቤቱ የሠራተኞች አስተዳደርን በተመለከተ ደንብ እንዲያወጣ ይፈቅድለታል። ይሁን እንጂ ሠራተኞች በጥርጣሬ እንዲሰናበቱና በየትኛውም የፍርድ አካል መብቸውን እንዳይጠይቁ የሚከለክል ኢ-ህገ መንግስታዊ ደንብ እንዲያወጣ ስልጣን አልሰጠውም።

የህብረህዋሳት ልገሳና ንቅለ ተከላ

የመድሀኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ደንብ ቁ. 299/2006 አንቀጽ 58-62 ድንጋጌዎች ስለ ደምና ደም ተዋጽኦ እና የሰውነት አካል ክፍሎችና የህብረህዋሳት ልገሳና ንቅለ ተከላ (donation of blood and blood products and donation and transplantation of organs and tissues) የሚከናወንባቸውን ሁኔታዎች ይደነግጋሉ። ደንቡ የወጣው የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 661/2002 አንቀጽ 55/1/ እና በአዋጅ ቁ. 916/2008a በተተካው አዋጅ ቁ. 691/2003b አንቀጽ 5 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሰጠ ስልጣን እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተመልክቷል። አዋጅ ቁ. 661/2002 የአካላት ልገሳና ንቀለ ተከላ የሚመለከት ድንጋጌ አልያዘም። አንቀጽ 55/1/ ም/ቤቱ የሰጠው ስልጣን አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ ደንቦች እንዲያወጣ ብቻ ነው። አዋጁ በዝምታ ያለፈውን ለዛውም ንቀለ ተከላን የሚያክል ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በማስፈጸም ሰበብ በደንብ መወሰን የፓርላማን ቦታ መቀማት እንጂ በውክልና ህግ የማውጣት ተግባር አይደለም።

እንደ ተጨማሪ የስልጣን ምንጭ የተጠቀሰው የአዋጅ ቁ. 691/2003 አንቀጽ 5 ትንሽ አግራሞት መፍጠሩ አይቀርም። ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 የተመለከተው ይሆናል።

ህገ መንግስት ጠቅሶ ህግ ማውጣት የሚችለው የተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ነው። በአንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 እንደሰፈረው የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን አለው። ስልጣን በማስተላለፍ የሚፈጠረው የወካይ-ተወካይ ግኝኑነት ሚኒስትሮችን ከአስፈፃሚነት በተጨማሪ የህግ አውጭነት ሚና ያላብሳቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ በውክልና የተላለፈ ስልጣን በሌለበት የሚወጣ ማንኛውም ደንብ የህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት ገደቦችን ይጥሳል።

ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱት አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የህጋዊነትና የህገ መንግስታዊነት ችግር ያንጸባርቃሉ። ውጤታማ የቁጥጥር ስልቶች ባልተረዘጉበት ሁኔታ በየጊዜው የሚወጡት መመሪያዎችና ደንቦች በስም ‘የበታች ህጎች’ በተግባር ግን ‘የበላይ ህጎች’ ሆነዋል።

የባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ አባልነት

በሰ/መ/ቁ. 44226c የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከፊል ድንጋጌዎች ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ስለሚቃረኑ ተፈጻሚነት እንዳይኖራቸው በተጠሪዎች ክስ ቀርቦ በፌደራል መጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሻሩ ተወስኗል። ተቃውሞ የቀረበበት መመሪያ እ.ኤ.አ. 2006 ዓ.ም. የወጣው Directive No. SBB/39/2006 Licensing and Supervision of Banking Business፡ Amendment for New Bank Licensing and Approval of Directors and CEO ሲሆን የባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ አባል በተመሳሳይ ጊዜ በሌላ የገንዘብ ተቋም የቦርድ አባል ሆኖ እንዳያገለግል፣ 75 ፐርሰንት አባላት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲኖራቸው እንዲሁም በድጋሚ መመረጥ እንዳይችሉ የተለያዩ ገደቦችን ይጥላል። ባንኩ መመሪያውን ያወጣው በጊዜው ጸንተው በነበሩት የገንዘብና ባንክ አዋጅ ቁ. 83/1986 አንቀጽ 41 እና የባንክ ስራ ፈቃድና ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 84/1986 አንቀጽ 36 እንደሆነ በመመሪያ መግቢያ ላይ ተገልጿል።

ጉዳዩ በሰበር ሲታይ ባንኩ መመሪያውን ለማውጣት ስልጣን እንዳለው በተደረሰበት ድምዳሜ መሰረት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎች ተሽረዋል። ሆኖም ለስልጣኑ ምንጭ ችሎቱ የጠቀሳቸው ድንጋጌዎች ባንኩ ራሱ በመመሪያው ላይ ካሰፈራቸው ይለያሉ። ችሎቱ ለህግ ትርጉሙ ድጋፍ ያደረገው የባንኩን የመቆጣጠር ስልጣን እና በሁለቱም አዋጆች በጥቅል የተደነገገው ባንኩ አዋጆቹን ለማስፈጸም የተሰጠው መመሪያ የማውጣት ስልጣን ነው።

የማስፈጸም ዓላማ ያለው መመሪያ በሚያስፈጽመው አዋጅ ላይ ከተደነገጉ ጉዳዮች በላይ አልፎ ሊሄድ አይችልም። የመቆጣጠር ስልጣን እንዲሁ በህጉ ከተዘረጋው የቁጥጥር ማዕቀፍ ሊያፈነግጥ አይገባም። የመቆጣጠርና የማስፈጸም ስልጣን ብቻውን መመሪያውን ህጋዊ የሚያደርገው ከሆነ በባንኩ መመሪያ የማውጣት ስልጣን ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ማስቀመጥ አይታሰብም። ይህ አካሄድ ማናቸውንም የባንኩን መመሪያዎች ህጋዊነት የማጽደቅ ያክል ነው። በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ላይ የሚደረጉ ገደቦችን በመመሪያ ለመወሰን መጀመሪያ ዋናው ህግ መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ሊደነግግ ይገባል።

የውክልና አሰጣጥ መንገዶች

የተወካዮች ም/ቤት በሁለት ዓይነት መንገዶች በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ያስተላልፋል። የመጀመሪያውና የተለመደው ‘ማስፈፀሚያ የውክልና ስልጣን’ ሲሆን በየአዋጁ የመጨረሻ ገጽ ‘የሚኒስትሮች ም/ቤት (የአስተዳደር መ/ቤት) ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንብ (መመሪያ) ሊያወጣ ይችላል።’ የሚል አገላለጽ ይዞ ይገኛል። የውክልና ስልጣን በዚህ መልኩ ከተቀመጠ ደንቡ ወይም መመሪያው አግባብነት ያለውን አዋጅ ለማስፈጸም ብቻ በመሆኑ በአዋጁ ባልተሸፈኑ ጉዳዩች ላይ ሊወጣ አይችልም። ያመረታቸውን ምርቶች በችርቻሮ መነገድ አይችልም። ሆኖም በልዩ ሁኔታ በችርቻሮ መነገድ የሚችልባቸውን ምርቶች ዓይነት በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይወሰናል።d

የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዕውቅና ስለሚታደስበት፣ ስለሚታገድበት፣ ስለሚሰረዝበት እና ስለ ቅሬታ አቀራረብ እንዲሁም እውቅና የሚሰጣቸው የማሰልጠኛ ተቋሞች ስለሚጠበቅባቸው የአገልግሎት ክፍያና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይወሰናል።e

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅታዊ የውጭ አገር የስራ ገበያ ሁኔታዎችን እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን አስመልክቶ የሥራ ሁኔታ መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።f

የውክልና ስልጣን የሚተላለፍላቸው አካላት

የህግ አውጭነት ስልጣን በውክልና የሚተላፍላቸው አካላት ህግና ፖሊሲ የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ናቸው። በመተላለፉ ሂደት በወካይና ተወካይ በሚወጡት ሀጎች መካከል የበላይና የበታች ግንኙነት ይፈጠራል። ስለሆነም የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የበላይ ህግ ሲሆን አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች (ደንብና መመሪያ) ደግሞ የበታች ህግ በመሆን አዋጁን ያስፈጽማሉ። ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የህግ አውጭነት ስልጣን የሚተላለፍላቸው አካላት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የአስተዳደር መ/ቤቶች ናቸው። በአንዳንድ አዋጆች ላይ ደግሞ ወካይ የሆነው ተወካዮች ምክር ቤት ራሱ እንዲሁም የክልል መንግስታት የውክልና ተቀባዮች ተደርገዋል።

የሚኒስትሮች ም/ቤት

በጣም ውስንና ልዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም በየትኛውም አገር ያለው የህግ አውጭነት ውክልና ግንኙነት የሚፈጠረው በፓርላማና በአስተዳደር መ/ቤቶች መካከል ነው። ከላይ በአንደኛው ጫፍ የተቀመጠው ወካይ ህግ የማውጣት ስልጣኑን ያስተላልፋል። ከስር የሚገኙት የአስተዳደር መ/ቤቶች ተለክቶ የተሰጣቸውን ስልጣን ይቀበላሉ። ሆኖም በእኛ አገር የስልጣን ፍሰቱ ይህን ቀጥተኛ መስመር ብቻ ይዞ አይጓዝም። በወካይ እና ተወካይ መካከል ሌላ የስልጣን ተጋሪ አለ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት። ይህ ተቋም በኢትዮጵያ የመንግስት ስርዓት ውስጥ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ህገ መንግስት ከቆመበት ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ እስካ አሁን ድረስ በህግ ማውጣት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነው።g

የሚኒስትሮች ም/ቤት የህግ አውጭነት ስልጣን ከፖለቲካዊ ፋይዳው በስተቀር አስፈላጊነቱን አሳማኝ የሚያደርጉ የመርህ እና የጠቀሜታ ምክንያቶች የሉም። እንዲያውም የሚፈጥረው ህገ መንግስታዊ ችግር ይብሳል። ከተዋጽኦ አንጻር ካየነው በጣት ከሚቆጠሩት ውጪ ሁሉም የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላት ተመራጮችና የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ናቸው። በተናጠል ሆነ በስብስብ ከህግ አውጭው የተሻለ ደንብ በሚያወጡበት ጉዳይ ላይ ልዩ ዕውቀት የላቸውም። እያንዳንዱ ሚኒስትር በስሩ የሚመራውን ተቋም በመከታተል በስራ ይጠመዳል። የጋራ ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች በምክር ቤት አባልነቱ ከሌሎች ሚኒስትሮችና ባለስልጣኖች ጋር ስብሰባ ይቀመጣል። ስለሆነም የአገሪቱን ፖሊሲዎች የመንደፍና ህጎች በስራ መተርጎማቸውን የማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሸከመው ም/ቤት ከህግ አውጭው በባሰ ጊዜ ያጥረዋል። ዕውቀትና ጊዜ ከሌለው ደግሞ ህግ ማስፈጸሚያ ደንቦችን ለማውጣት ትክክለኛው ተቋም አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ በህግ አመንጭነቱ የሚጫወተው ሚና በውክልና አሰጣጡ ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል። ከተግባራዊ ምክንያቶች የተነሳ ተመራጮች ሁሉንም ህጎች ማውጣት ቢሳናቸውም ይህን ስልጣናቸውን በከፊል የሚያስተላልፉት ወደውና ፈቅደው አምነውበት ነው። አገሪቱ የምትመራባቸው አዋጆች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ይመነጫሉ። አሊያም በሱ በኩል ያልፋሉ። በዛ ላይ ረቂቆች ለውይይት ሲቀርቡና ሲጸድቁ የተወሰኑ ሚኒስትሮች ፓርላማ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ እስከሆነ ድረስ በእያንዳንዱ አዋጅ ላይ ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም ደንብ ያወጣል’ የምትለው አንቀጽ ፓርላማው ወዶና ፈቅዶ የደነገጋት ናት ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል። ይህም የሚያደርሰን ድምዳሜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህግ አውጭነት ተግባር አስፈላጊነት የስልጣን መጋራት እንጂ ከውጤታማ አስተዳደር ጋር የተያያዙ አጥጋቢ ምክንያቶች አይደሉም።

ብዙ አገራት ህግ አውጭው ስልጣኑን በውክልና ማስተላለፍ የመቻሉን ነገር በሀገ-መንግስታቸው ላይ ሳያካትቱ በዝምታ አልፈውታል። ምክንያቱም ውክልና የአንዲት አገር ችግር ሆኖ ፈጦ የመጣው ከማህበራዊ መንግስት መወለድ ጋር በጣም በቅርብ ነው። እንደ ጀርመን ያሉ ህገ መንግስታቸውን በቅርብ ያጸደቁ አገራት ግን የህግ አውጭነት ስልጣን ሊተላለፍባቸው የሚችሉ ሁኔታዎችና ገደቦችን በህገ መንግስታቸው ላይ በግልጽ ደንግገዋል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት በይፋ የታወጀው ስለ ውክልና ዓለም ብዙ ካወራና ከተነጋገረ በኋላ በጣም በቅርቡ ነው። ከዚህ አንጻር የህግ አውጭነት ስልጣን የሚተላለፍበትን አኳኋን እና ገደብ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በቀላሉ የሚረሳውና በዝምታ የሚያልፈው ጉዳይ መሆን አልነበረበትም። ከአንቀጽ 77/13/ ድንጋጌ እንደምንረዳው ትልቁ ጭንቀት በስልጣን ተቀባዩ ማንነት ላይ ሆኗል። የስልጣን አሰጣጡ መንገድና ህገ መንግስታዊ ገደብ ማለትም መሰረታዊው ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ቦታ አልተሰጠውም። ይህም የሚያደርሰን ድምዳሜ ቢኖር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህግ አውጭነት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዲኖረው አስቀድሞ ታስቦበታል። ምናልባት ለዚህ ተቋም ስልጣን መተላለፉ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ እንዳያስነሳ ነው እንዳይባል ድምራቸው በመቶ ሳይሆን በሺ የሚቆጠሩትን መመሪያዎች የሚያወጡት የአስተዳደር መ/ቤቶችን የሚጠቅስ ተመሳሳይ ድንጋጌ የለም።

‘የራስ ውክልና’

የፌደራል ዋና አዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 982/2008 አንቀጽ 22 /1/ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለአዋጁ አፈጻጸም አስፈላጊ የሆነ ደንብ ሊያወጣ እንደሚችል ተመለክቷል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ለራስ የሚሰጥ ውክልና ትርጉም የለውም። ከአዋጅ ቀጥሎ ማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣት የግድ የሚል ነገር አይደለም። ስልጣን ማስተላለፍ ያስፈለገው ስራ ለማቅለል ነው። በጊዜና በዕውቀት እጥረት የተነሳ እንዲሁም አዋጅ ለማውጣት ጥብቅ ስነ ስርዓት መከተል ስለሚያስገደድ በአጠቃላይ በእነዚህ ድምር ችግሮች የተነሳ ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት እንዳይበደል ነው። ለዚህ ተግባራዊ ምክንያት ሲባል በየአስተዳደር መ/ቤቱ የሚገኙ በህዝብ ያልተመረጡ ሹመኞች ተጨማሪ የህግ አውጭነት ስልጣን ይተላለፍላቸዋል። ይህ አሰራር በመርህ ደረጃ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው። ሆኖም ለዴሞክራሲ መርህ ከማሰብ ይልቅ ለተጨባጭ የህዝብ አስተዳደር ችግር መጨነቅ ስለሚሻል የህዝብ ተመራጮች ስልጣናቸውን ቆርሰው ማስተላለፍ ተገደዋል። በዚህ መነጽር ካየነው ራስን መወከል በተግባር ሆነ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አንዳችም ነገር አይፈይድም። አዋጁን ያወጡት ተወካዮች ለራሳቸው በሰጡት ውክልና ደንብ ለማውጣት ተመሳሳይ የህግ አወጣጥ ስርዓት መከተላቸው የማይቀር ነው።

የክልል መንግስታት

የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ቁ. 922/2008 አንቀጽ 37/2/ ክልሎች በአዋጁ በወጡ ደንቦች ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ሕግ ሊያወጡ እንደሚችሉ ይደነግጋል። የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት ስርዓት አዋጅ ቁ. 457/1997 አንቀጽ 10/2/ የቆዳና ሌጦ የአገር ውስጥ ግብይት ስርዓትን በሚመለከት አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችንና መመሪያዎችን ክልሎች ሊያወጡ እንደሚችሉ ተመልክቷል። በቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁ. 602/2000 አንቀጽ 19/3/ እንዲሁ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ህጎች እንዲያወጡ ተወክለዋል።

የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ብ/ክ/መንግስት መስተዳድር ከአዋጅ ቁ. 457/1997 ያገኘውን ውክልና እንዲሁም የክልሉን ህገ መንግስት በማጣቀስ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት ደንብ ቁ. 55/1998 አውጥቷል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግን በህግ አውጭው አማካይነት ህግ ማውጣት በመምረጡ የቆዳና ሌጦ ግብይት ስርዓት ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 148/2001 በክልሉ ነጋሪት ጋዜጣ አውጇል። በዚህ አዋጅ ላይ በስልጣን ምንጭነት የተጠቀሰው የክልሉ ህገ መንግስት ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ምንጩ የፌደራሉ ህግ አውጭ ውክልና አይደለም። ስልጣን ሰጪው አዋጅ ቁ. 457/1997 አሁን በስራ ላይ የለም። በጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ ቁ. 814/2006 ተሸሯል። ይህ አዋጅ ክልሎች ያወጧቸውን ህጎች በተመለከተ መሸጋገሪያ ድንጋጌ አልያዘም። ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ ህግ ለክልሎች ህግ የማውጣት የውክልና ስልጣን አይሰጥም። ከዚህ አንጻር የሁለቱ ክልሎች ህግ በተዘዋዋሪ ተሽረዋል ማለት ነው? አዋጅ ቁ. 814/2006 ከአዋጁ ጋር የሚቃረኑ ህጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ልምዶች ተፈጻሚነት እንደሌላቸው የሚጠቁም ድንጋጌ አልያዘም። ይህ ደግሞ በሁለቱ ክልሎች የወጡትን ህጎች ውጤት ይበልጥ ያወሳስበዋል።

የውክልና ውክልና

በተለያዩ ደንቦች ላይ ለደንቡ ማስፈጸሚያ የሚረዳ መመሪያ የማውጣት ስልጣን ለበታች አካል ማስተላለፍ በተግባር ይስተዋላል። በዋናው አዋጅ በግልጽ ካልተፈቀደ በስተቀር ‘የተወካይ ወካይነት’ ህጋዊ መሰረት የለውም። ከመነሻው የሌለ ስልጣን ወደ ሌላ አካል አይተላለፍም። በተጨማሪም ደንቡ ያስፈለገው የበላይ ህግ ለማስፈጸም እስከሆነ ድረስ ‘ማስፈጸሚያው’ ሌላ ማስፈጸሚያ አያስፈልገውም። በይዘቱ ራሱን ችሎ የቆመ ወይም የተሟላ ሊሆን ይገባል።

የተወካይ ወካይነት የሚያስነሳውን የህግ ጥያቄ ለማስቀረት ህግ አውጭው በአሁኑ ጊዜ ‘ቀጥተኛ የውክልና ውክልናን’ እንደ አማራጭ እየተጠቀመ ይገኛል። በዚሁ መሰረት የሚመለከተው መ/ቤት አዋጁን ብቻ ሳይሆን በአዋጁ መሰረት የሚወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም መመሪያ የማውጣት ስልጣን ይሰጠዋል።

ቅርጽ እና አመዳደብ

በውክልናው የሚወጣው ህግ በተለያየ ቅርጽ ይገለጻል። በአገራችን ሁለት ዓይነት መሰረታዊ ቅርጾችን የሚይዝ ሲሆን ከስያሜው አንጻር ‘ደንብ’ እንዲሁም ‘መመሪያ’ እየተባለ ይጠራል።

‘ደንብ’ በተወካዮች ም/ቤት ከሚወጣው አዋጅ ዝቅ ብሎ አስገዳጅነት ያለው ህግ ሲሆን አውጭው አካል የሚኒስትሮች ም/ቤት ነው። ‘መመሪያ’ በተለያዩ የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና የሚወጣ ህግ መጠሪያ ሲሆን ከደንብ ቀጥሎ አስገዳጅነት አለው።h

ከደረጃ (hierarchy) በተጨማሪ ደንብና መመሪያን ህትመት ይለያቸዋል። ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ይታተማል። የእያንዳንዱ የአስተዳደር መ/ቤት መመሪያ ግን በኮምፕዩተር ተጽፎ በወረቀት ላይ ታትሞ (print) ይሰፍራል። በሁለቱ መካከል የተፈጠረው የህትመት ልዩነት ምንጩ ልማድ እንጂ የህግ ቅድመ ሁኔታ አይደለም። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/2/ ደንብ ‘ይታተም መመሪያ አይታተም አይልም።’ ድንጋጌው የሚያስገድደው ‘የፌደራሉ መንግስት ህጎች’ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታተሙ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ‘መመሪያ’ የሚለው መጠሪያ አስገዳጅነት ያለውን አስተዳደራዊ ድንጋጌ ለማመልከት እንጠቀምበታለን። ሆኖም መጠሪያ ብቻውን አስገዳጅነትን በእርግጠኝነት አይወስንም። መለኪያ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ይዘቱና ባህርያቱ ናቸው። ‘መመሪያ’ ስለተባለ ብቻ አስተዳደራዊ ድንጋጌ አይሆንም፤ ስላልተባለም ህጋዊ ውጤቱን አያስቀረውም። ለምሳሌ አንዳንዴ ‘የስራ መመሪያ’ የሚባለው ሰነድ የበታች አካላት ስራቸውን የሚያከናውኑበትን ቅደም ተከተልና የተወሰኑ የስራ ተግባራት የስራ ክንውን አቅጣጫ ይጠቁማል። በይዘቱ ህግ ለማስፈጸም የሚወጣ አስተዳደራዊ ድንጋጌ አይደለም። ምሳሌ ለመጥቀስ ያክል የሚከተሉት ‘መመሪያ’ዎች በአስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ስር አይወድቁም።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተግባር ልምምድ ፕሮግራም መመሪያ

በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም መመሪያ

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የቀጥታ ዘር ግብይት አተገባበር መመሪያ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ኤክስቴንሽን አተገባበር መመሪያ (የተከለሰ)

ከላይ የተዘረዘሩት ሰነዶች የመመሪያን ስያሜ ቢይዙም አንዳቸውም በውክልና በተሰጠ የህግ አውጭነት ስልጣን ተለይቶ የታወቀን ህግ የሚያስፈጽሙ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አይደሉም። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የየተቋሙን የውስጥ ጉዳይ የሚመለከቱ የቅበላና የአጠቃቀም መግለጫዎች ናቸው። የተቀሩት ደግሞ የሚከናወኑ ተግባራት፣ ፕሮግራሞች፣ የአሰራር፣ የአደረጃጃትና የአተገባበር ቅደም ተከተልና ግንኙነት ይወስናሉ።

ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ ‘መመሪያ’ የሚል ስያሜ ያልያዙ ሰነዶች አንዳንድ ጊዜ በይዘታቸው በአስተዳደራዊ ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ ይሆናሉ። በእርግጥ ከመልካቸው መዘበራረቅ የተነሳ ከሶስቱ አስተዳደራዊ ተግባራት (ህግ አውጭነት፣ ዳኝነታዊ እና አስተዳደራዊ) በአንዱ መመደብ ያስቸግራል። ምክንያቱም ተመሳሳይ ስም የያዙ ሰነዶች ህጋዊ ውጤታቸው የሚለያይበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ከመመሪያ የተለየ ስያሜ ካላቸው ውስጥ ስታንዳርድ (standard)፣ ማኑዋል (manual)፣ ጋይድላይን (guideline)፣ ሰርኩላር (circular)፣ የህዝብ ማስታወቂያ (public notice) ውስጠ-ደንብ (by-law)፣ እና ኮድ (Code) ይጠቀሳሉ። በእነዚህ ስያሜዎች ከሚታወቁት ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ።

ስታንዳርድ (standard)

Standard Conditions of Contract for Construction of Civil Work Projects

ማኑዋል (manual)

የኢንዱስትሪ ሰላም ማስጠበቂያ ዋና የስራ ሂደት የትግበራ ማኑዋል

የመንግስት ግዥ አፈጻጸም ማኑዋል

ጋይድላይን (guideline)

Guideline for Adverse Drug Reaction (ADR) Reporting

Guidelines for Procurement, Distribution and use of Antiretroviral Drugs in Ethiopia

ሰርኩላር (circular)

ከተለያዩ የፌደራል የመንግስት መ/ቤቶች ለተነሱ የህግ ጥያቄዎች የተሰጠ ማብራሪያ (ሰርኩላር)

የህዝብ ማስታወቂያ (public notice)

የጉምሩክ ወደቦች፣ ማቋረጫዎችና መተላለፊያ መንገዶች የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣኑ በሚያወጣው የህዝብ ማስታወቂያ ይወሰናሉ።i

ፈቃድ ሰጨው ባለስልጣን ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን የህዝብ ማስታወቂያ በማውጣት ማናቸውንም መሬት የታወቀ የጂኦተርማል ክልል ነው ብሎ ሊሰይም ይችላል።j

ፈቃድ ሰጭው ባለስልጣን ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን የሕዝብ ማስታወቂያ በማውጣት ማናቸውም መሬት የጂኦተርማል ስራ የማይካሄድበት ነው ብሎ መከለል ይችላል።k

መንግስት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሲባል ተገቢው የማካካሻ እርምጃ ተወስዶ የጂኦተርማል ስራ እንዳይካሄድበት በፈቃድ ሰጭው ባለስልጣን የተከለለ መሬት ወይም በህግ የተከለከለ ማንኛውም ስፍራ ለጂኦተርማል ስራ ክፍት እንዲሆን ሊፈቅድ ይችላል።l

ውስጠ-ደንብ (by-law)

Asosa University Senate Legislation

አክሱም ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ዲሲፕሊን መመሪያ

ኮድ

የኢነርጅ ባለስልጣን ከስልጣንና ተግባራቱ መካከል የኢነርጂ ኦዲት ኮድ፣ የኢነርጅ ብቃት ደረጃዎች ኮድ፣ የኢነርጅ ብቃት ማረጋገጫ ተለጣፊ ምልክት ኮድ፣ የግሪድ ኮድ፣ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ኮድ፣ የኢንስፔክሽን ኮድ፣ የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ኮድ፣ የሕንፃ ኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ ኮድ፣ የቴክኒካል ስታንዳርድ ኮድ እና ሌሎች ኮዶችን ማውጣትና አፈጻጸማቸውን መቆጣጠር አንደኛው እንደሆነ በኢነርጂ አዋጅ ቁ. 810/2006 አንቀጽ 4/4/ ተመልክቷል። በአዋጁ አንቀጽ 2/12 ኮድ ማለት በባለስልጣኑ መመሪያ የተደነገጉ የኤሌትሪክ ስራዎችን ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎችን የሚመለከቱ የስርዓቶችና አሰራሮች ስብስብ ነው።

ቅድመ ሁኔታዎችና መስፈርቶች

በቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደርር የውልና ክብር መዝገብ ማስረጃ አገልግሎትት ወሳኝ የስራ ሂደት የሚሰጣቸው አገልግልቶች እና መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

የአገር ውስጥ ስራ ተቋራጮች በኮንስትራክሽን አገልግሎት ሰጭነት ለመመዝገብ ማሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች

አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስርዓት

ስነ-ስርዓት ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ ሲሆን የበዘፈቀደ አሰራርን በማስወገድ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ዝርዝር የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በውክልና የተሰጠ ስልጣን በአግባቡ ተግባር ላይ ስለመዋሉ አንዱ መለኪያ መስፈርት ነው።

የኛን አገር ጨምሮ በአንዳንድ አገራት አስተዳደራዊ ድንጋጌ የሚወጣበት ወጥ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ደንብ (Administrative procedure code) ራሱን ችሎ በተለይ ይደነገጋል። ወጥ ስነ-ስርዓት በሌለበት ሁኔታ ግን የውክልና ስልጣኑን የሚሰጠው ህግ የአስተዳደር መ/ቤቱ መከተል ያለበትን አነስተኛ የስነ-ስርዓት አካሄድ ለይቶ ያስቀምጣል። በአገራችን የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ቁ. 1183/2012 እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በሚኒስትሮች ም/ቤት ደረጃ ሆነ በአስተዳደር መ/ቤቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አስገዳጅና ወጥ የስነ-ስርዓት ደንብ ያልነበረ ከመሆኑም በላይ የውክልናው ምንጭ የሆነው አዋጅ ዝርዝር የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎችን አያስቀምጥም። በዚህ የተነሳ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ውጤታማ አስተዳደር በማስፈን ረገድ ያላቸውን ሚና ከማሳነሱም በላይ ለህገ-ወጥ አሠራር፣ ሙስና እና አስተዳደራዊ ብልሹነት መንሰራፋት አይነተኛ ምክንያት ሆኗል።

ልዩ ሁኔታዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው በውክልና ህግ የሚያወጣ አካል የሚከተሉትን የስነ-ስርዓት ደንቦች መከተል ይጠበቅበታል። እነዚህም ስነ-ስርዓቶች ማስታወቂያና መረጃ መስጠት፣ ምክክር (የህዝብ ተሳትፎ)፣ ክለሳ እንዲሁም ህትመት በሚል በአራት ዋና ዋና ንዑስ ስርዓቶች ልንከፍላቸው እንችላለን።

እነዚህ ንዑስ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ጥሩ ሊባል የሚችል አስተዳደራዊ ደንብ ወይም መመሪያ ከማርቀቅ ሂደት እንደሚጀምር ልብ ሊባል ይገባል። ሲረቀቅ ያላማረ ሲጸድቅም አያምርም። ስለሆነም ደንቡ ወይም መመሪያው ግልጽ፣ በቀላሉ የሚገባ፣ የማያደናግር ይሆን ዘንድ በማርቀቅ ሂደቱ ላይ የህግ ባለሙያ ተሳትፎ ተመራጭነት አለው።m

አዲስ በወጣው የስነ-ስርዓት አዋጅ በመመሪያ አወጣጥ ሂደት ተፈጻሚ የሚሆኑ የስነ-ስር ዓት ደንቦችን በተመለከተ በዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ክፍል ላይ ቀርቧል።

ማስታወቂያ እና መረጃ መስጠት

የህዝብ ተሳትፎ ለአስተዳደራዊ ድንጋጌው ተዓማኒነትና ተቀባይነት ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህ መሰረት ሀሳብ በተግባር የሚተረጎመው ግልፅ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ ማስፈፀሚያ ስርዓት ሲኖር ነው። በዚህ ረገድ አስተዳደራዊ ደንቡ ወይም መመሪያው ከመታተሙ በፊት የሚመለከተው የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ፣ ጥቆማ፣ አስተያየት፣ ትችትና ሂስ ለመስጠት እንዲያስችለው ረቂቁን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።

ለምሳሌ በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት በውክልና ህግ የማውጣት ስነ-ስርዓት ብንወስድ የሚመከለተው የአስተዳደር መ/ቤት መመሪያ ለማውጣት ሲያቅድ አስቀድሞ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ጋዜጣ (state register) ማስታወቂያ ያወጣል። ረቂቁ መመሪያ በሙሉ ወይም በከፊል ከማስታወቂያው ጋር የሚወጣ ሲሆን በከፊል ከታተመ የረቂቁ ሙሉ ቅጂ ስለሚገኝበት አድራሻና ሁኔታ በጋዜጣው ላይ መግለጫ ይሰጣል። ስለሆነም አስተያየት ማቅረብ የሚፈልግ ወገን መመሪያ በሚያወጣው የአስተዳደር መ/ቤት በቀጥታ በአድራሻው በመሄድ የረቂቁን ቅጂ በነጻ ወይም በአነስተኛ ክፍያ ማግኘት ይችላል። በተጨማሪም ከኢንተርኔት ድረ-ገጽ ላይ በቀላሉ ይገኛል።n

ማስታወቂያው በጋዜጣ ላይ ከታተመበት ዕለት ጀምሮ ለ45 ቀናት መቆየት ያለበት ሲሆን ዓላማውም በጉዳዩ ጥቅም ያላቸው ወገኖች አስተያየት፣ ጥቆማና ሂስ ለማቅረብ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ነው። ሀሳብ መስጠት የፈለገ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት አስተያየቱን በጽሁፍ፣ በፋክስ፣ በኢ-ሜይል ወይም በሌላ በሚያመቸው መገናኛ ዘዴ መላክ ይችላል።

በካሊፎርኒያ ሆነ በሌሎች ግዛቶች ያለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት ከሞላ ጎደል እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. በፌደራል መንግስት ደረጃ ከወጣው የአስዳደር ስነ ስርዓት ደንብ (Administrative Procedure Act, 1946) ከሚደነግጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ተቀራራቢ ነው። በዚህ ህግ መሰረት የአስተዳራዊ ድንጋጌ (በህጉ አነጋገር ‘Rule’) አወጣጥ ስርዓቱ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሚል ለሁለት (እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም. የህግ ዕውቅና ያገኘውን Negotiated Rulemaking ሳይጨምር) ተከፍሏል።o

መደበኛው ስርዓት እንደ ፍርድ ቤት ክርክር ዓይነት የጉዳዩ መሰማት የሚካሄድበት ሲሆን የሚመለከታቸው ወገኖች አስተያየት ከመስጠት ባለፈ የኤጀንሲውን አቋም ለማስተባበል ተቃራኒ ክርክር እና ማስረጃ ማቅረብ ይፈቀድላቸዋል።p በአሜሪካ የፌደራል መ/ቤቶች በስፋት የሚከተሉትና እንዲከተሉትም የሚገደዱት ኢ-መደበኛውን ስርዓት ሲሆን መሟላት ያላባቸው አነስተኛ ቅድመ ሁኔታዎች ማስታወቂያ፣ አስተያትና ህትመት ናቸው። የአስተዳደራዊ ድንጋጌ (Rule) አወጣጥ ስርዓቱ ፌደራል ሬጅስተር በሚባለው ዕለታዊ የመንግስት ጋዜጣ ይፋ ማስታወቂያ በማውጣት ይጀመራል።q ማስታወቂያው የሚከተሉትን መግለጫዎች መያዝ ይኖርበታል።

ሊወጣ የታቀደው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የሚገኝበትን ቦታ፣ ጊዜ እና አጠቀላይ ባህርያቱን

ስልጣን የሰጠው አዋጅና ለድንጋጌው መውጣት መነሻ የሆነውን የህግ ምክንያት

ሊወጣ ስለታሰበው ድንጋጌ ይዘት እና በውስጡ የተካተቱ ጭብጦች አስመልክቶ አጠቃላይ መግለጫ

በአገራችን 1993 ዓ.ም. በተዘጋጀው ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግr መሰረት ደንብ ማውጣት የሚፈልግ የአስተዳደር መ/ቤት ከ30 ቀናት በፊት የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች የያዘ ማስታወቂያ በጋዜጣs ማውጣት አለበት።

ስለ ረቂቅ ደንቡ ዓላማ አጭር ማብራሪያ

የደንቡ ረቂቅ የተፈቀደበት ሕጋዊ ስልጣን

የደንቡ ረቂቅ ሰነድ

የደንቡ ረቂቅ ላይ ሰዎች የት፣ መቼና እንዴት አስተያየታቸውን እንደሚያቀርቡና

የደንቡ ረቂቅ ላይ ስለሚሰጥ የቃል አስተያየት የማቅረብ ስርዓት በሚመለከት የት፣ መቼና እንዴት እንደሚካሄድ መጠየቅ እንደሚችሉ የሚገልጽ መረጃ

በ2001 ዓ.ም. ድጋሚ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይም እነዚህን አምስት መግለጫዎች የያዘ ማስታወቂያ በጋዜጣ ወይም በሌላ መገናኛ ብዙኃን ሊነገር እንደሚገባው ተመልክቷል። የቃል አስተያየት (hearing) በአሜሪካ የመደበኛው ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ተፈጻሚነቱ ተቋሙ ይህን ስርዓት እንዲከተል ህግ አውጭው በልዩ ህግ በግልጽ ባመለከታቸው ውስን ሁኔታዎች የተገደበ ነው። የአገራችን አርቃቂዎች ባይገለጥላቸውም አሜሪካኖች ይህን አካሄድ የመረጡበት ምክንያት ግልፅ ነው። የየትኛውም አገር አስተዳደር ውጤታማነት እና ቅልጥፍና ተቀዳሚ እሴቶቹ ናቸው። አንድ መመሪያ ለማውጣት እንደ ፍርድ ቤት ዓይነት ሙግት እየተደረገ፣ ደጋፊና የሚያስተባብል ማስረጃ እየቀረበ፣ የቃል ክርክር እየተሰማ በአጠቃላይ ከፍተኛ ወጪና ጊዜ በሚጠይቅ ሂደት ማለፍ አስገዳጅ ከሆነ አስተዳደር ይንዛዛል እንጂ አይቀላጠፍም።

ከላይ ከተዘረዘሩት የማስታወቂያ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በመጨረሻ ላይ የሚገኘው የቃል አስተያይት አቀራረብ ስርዓት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንደምታቸው ግዙፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መወሰን ይኖርበታል። እነዚህን ጉዳዮች ለመለየት ቋሚ መለኪያ ማበጀት ብዙም አይጠቅምም። ምክንያቱም በጊዜና በሁኔታ ይለዋወጣሉ። ዛሬ ላይ ሲመዘን ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ በጊዜ ሂደት ፋይዳው ሊያንስ ይችላል። ስለሆነም አሜሪካኖቹ እንደተከተሉት አማራጭ ህግ አውጭው በየጊዜው በሚያወጣቸው አዋጆች ቢወሰኑ ይሻላል። በሌላ አነጋገር የቃል አስተያየት የማቅረብ ስርዓት አስገዳጅነት የተወካዮች ም/ቤት በየጊዜው በሚያወጣቸው አዋጆች በግልፅ ሲደነገግ ብቻ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል።

ማማከር እና ማሳተፍ

‘ምክክር’ የሚለው ቃል ከህዝብ አስተያየት መሰብሰብንና በአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ሂደት እንደ ግብዓት መጠቀምን ያመለክታል። ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ሀሳብ ከመቀበል በተጨማሪ ምክክር አልፎ አልፎ በተወሰኑ ሁኔታዎች በቀጥታ የሚደረግ ውይይት ወይም ስብስባ ሊያካትት ይችላል። በጉዳዩ ጥቅም ያላቸው ወገኖች ተሳትፎ ሕዝባዊ ተቀባይነትና አመኔታን ያረጋግጣል። ተግባራዊ አፈጻጸሙንም ምቹ ያደርገዋል። በተጨማሪም ዜጐች በቅድሚያ አውቀውት እንቅስቃሴያቸውን በደንቡና መመሪያው መሰረት እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል።

ምክክር ትርጉም የሚኖረው እውነተኛና በተግባር ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ብቻ ነው። በካሊፎርኒያ ግዛት መመሪያውን የሚያወጣው የአስተዳደር መ/ቤት በህዝብ ከቀረቡ አስተያየቶችና ጥቆማዎች መካከል ያመነባቸውና የተቀበላቸው ካሉ በረቂቁ ላይ ማካተትና የማይቀበል ከሆነም ያልተቀበለበትን ምክንያት በመግለጽ ለሁለቱም መግለጫ (statement of reasons) ማቅረብ አለበት።

ተጠያቂነት እና የክለሳ ስርዓት

በውክልና የሚወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በህግ አውጭው ከተሰመረለት ስልጣን በላይ አለማለፉን ማረጋገጥ ዋነኛው የአስተዳደር ህግ ዓላማ ነው። ዓላማውን ለመተግበር የስልጣን ወሰን ወይም ገደብ የሚቆጣጠር አካል ሊኖር ያስፈልጋል። በእንግሊዝ ይህ የማጣራት ወይም የክለሳ ሂደት የሚከናወነው በዋነኛነት በራሱ በፓርላማ ሲሆን በአሜሪካ በተለይ በካሊፎርኒያ ግዛት በህግ የተቋቋመና ራሱን የቻለ የአስተዳደር ህግ ጽህፈት ቤት (Administraive Law office) ተብሎ በሚጠራ ተቋም አማካይነት ቁጥጥር ይደረጋል። በእንግሊዝ የመመሪያውን ህጋዊነት የማጣራት ሂደትና ስነ-ስርዓት ብዙውን ጊዜ ውክልና በሰጠው አዋጅ ላይ ይደነገጋል። ይህ ስነ-ስርዓት የማንጠፍ ስነ-ስርዓት (Laying procedure) ተብሎ ሲጠራ ውክልና ተቀባዩ አካል አስተዳደራዊ ድንጋጌውን ለፓርላማው የማቅረብ (በፓርላማ ፊት የማንጠፍ ወይም የመዘርጋት (laying before parlament) ወይም (laying before the table) ቅድመ ሁኔታን ያሰቀምጣል፡

በዚህ ስነ-ስርዓት ፓርላማው በሚያደረገው ፍተሻና ምርመራ መሰረት ድንጋጌው ከስልጣን በላይ አለመሆኑና በአግባቡ ስለመውጣቱ ይጣራል። የማንጠፍ ስነ-ስርዓቱ የተለያዩ ቅርጽና መልክ ይኖረዋል። ነፃ የማንጠፍ ስነ-ስርዓት (Bare laying procedure) ድንጋጌው ተፈፃሚነት ከማግኘቱ በፊት ትክክለኛ ቅጂው ለፓርላማው እንዲቀርብ ያስገድዳል።t ዋና ዓላማው ፓርላማው የድንጋጌውን ይዘት እንዲያየው ከማድረግ አይዘልም። ስለሆነም ለፓርላማ ከቀረበበት ቀን አንስቶ ወዲያውኑ ውጤት ይኖረዋል።

አሉታዊ የማንጠፍ ስርዓት (Negative resolution procedure) ከሆነ ደግሞ ድንጋጌው ለፓርላማ ከቀረበ ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ጥያቄ ከቀረበበትና ግድፈት ከተገኘበት ይሰረዛል ። ሆኖም ከመሰረዙ በፊት በድንጋጌው መሰረት የተወሰዱ እርምጃዎች እንደጸኑ ይቆያሉ። ካልተሰረዘ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ይሁንታ አግኝቷል ማለት ነው።u ከዚህ በተቃራኒ ስርዓቱ አዎንታዊ የማንጠፍ ስርዓት (positive resolution procedure) በሚሆንበት ጊዜ ለፓርላማ ቀርቦ መፅደቅ ይኖርበታል።v የማንጠፍ ስርዓት መከተል ያለበት አስተዳደራዊ ድንጋጌ ስርዓቱን ባልተከተለ መንገድ የወጣ እንደሆነ ዋጋ አልባ (void) እንደሆነ ይቆጠራል።

በካሊፎርኒያ በውክልና የሚወጣ ህግ ውጤት ኖሮት ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት የተወሰኑ መመዘኛዎች ማሟላት አለበት። መመዘኛዎቹ መሟላታቸውን የአስተዳደር ህግ ጽህፈት ቤት (Administraive Law Office) የተባለ በህግ የተቋቋመ አካል ያረጋግጣል። እያንዳንዱ መ/ቤት የሚያወጣውን አስተዳደራዊ ድንጋጌ ረቂቅ ለክለሳ ለዚህ ጽህፈት ቤት በቅድሚያ መላክ ይኖርበታል። ከዚህ አንጻር ከእንግሊዝ የማንጠፍ ስነ-ስርዓት ጋር በከፊል ይመሳሰላል። ጽህፈት ቤቱ ድንጋጌውን ሲከልስ የሚከተሉትን መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ ነው።

ስልጣን (Authority)፤ የአስተዳደር መ/ቤቱ ድንጋጌውን እንዲያወጣ ከህግ አውጭው በእርግጥ ውክልና የተሰጠው መሆኑ

ማጣቀስ (Reference)፤ የአስተዳደር መ/ቤቱ በሚያወጣው ድንጋጌ ላይ የሚያስፈጽመው ህግ እና ስልጣን የሰጠውን ህግ አንቀጽ መጥቀሱ (ማመልከቱ)

ወጥነት (Consistencey)፤ ድንጋጌው ስልጣን ከሰጠው ወይም ከሌላ ህግ ጋር የተስማማ ወይም የማይቃረንና የማይጋጭ መሆኑ

ግልፅነት (Clarity)፤ የድንጋጌው ትርጉም ግልጽና በቀላሉ ለመረዳት የሚቻል መሆኑ

አለመደጋገም (Non- duplication)፤ ድንጋጌው ስልጣን የሰጠውን ህግ ድንጋጌዎች መድገም የለበትም። የህጉ ይዘት በከፊል ወይም በሙሉ በድጋሚ በድንጋጌው ላይ ከሰፈረ መመዘኛው አልተሟላም።

ህትመት

‘ህትመት’ የሚለው ቃል በአፍ የሚደነገግ መመሪያ እንደሌለ ያመለክታል። ‘የህግ መታተም’ ሲባል አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ለህዝብ በቀላሉ ሊደርስ በሚችል ወጥ የህትመት ውጤት ላይ ታትሞ ለህዝብ ማሰራጨት ማለት ነው። ህግ በጽሑፍ ላይ ሰፍሮ መውጣቱ ብቻ ብቻ በቂ አይደለም። ቁም ነገሩ ታትሞ መውጣቱ ሳይሆን ህትመቱ ይፋ መደረጉና በቀላሉ ለህዝቡ የሚደርስ መሆኑ ነው። ዜጎች ላልታተመና ይፋ ላልሆነ ብሎም በቀላሉ ለማይገኝ ህግ ሊገዙ አይችሉም። ድብቅ ህግ ህጉን ካወጣው አካል በስተቀር አውቆት የሚያከብረው አይኖርም።

በእንግሊዝ ውስጥ በብላክፑል ኮርፖሬሽን እና ሎከር (Blackpool Corporation Vs. Locker) መካከል በነበረው ክርክር ላይ በተሰጠ ውሳኔ የህትመት አስፈላጊነት እንዲህ ተገልጾ ነበር።w

ህግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም የሚለው መርህ በእንግሊዝ ዲሞክራሲ የህግ የበላይነት የቆመበትን መሪ ሀሳብ ይወክላል። ነገር ግን የዚህ መርህ የትክክለኛነቱ መሰረት ሁሉም ህጐች በቀላሉ ለህዝቡ እንደሚደርሱ ግምት በመውሰድ ነው።

በአሜሪካ በእያንዳንዱ የፌደራል መንግስት የአስተዳደር መ/ቤት የሚወጣ አስተዳደራዊ ድንጋጌ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ፌደራል ሬጅስተር (Federal Regiser) ተብሎ በሚጠራ ወጥና መደበኛ ጋዜጣ ላይ መታተም አለበት። እያንዳንዱ መመሪያ በጋዜጣው ላይ ሲታተም የራሱ መለያ ቁጥር ስለሚሰጠው ፈልጐ ለማግኘት በጣም ቀላል ያደርገዋል። መመሪያውን ማግኘት የሚፈልግ ሰው ከመ/ቤቱ ወይም ከጋዜጣው ድረ-ገጽ ላይ በቀላሉ በነጻ ማንበብና መቅዳት ይችላል። በተጨማሪ በአካል ሄዶ ጋዜጣውን በአነስተኛ ክፍያ መግዛት ሌላው አማራጭ ነው። እ.ኤ.አ በ1946 ዓ.ም. በወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ (Administrative Procedure Act) መሰረት ማንኛውም መመሪያ ተፈፃሚነት የሚኖረው በፌደራል ሬጅስተር ከታተመ ከ30 ቀናት በኃላ ነው። በእነዚህ 30 ቀናት ውስጥ ማንኛውም ሰው መመሪያውን ለማግኘትና ይዘቱን ለመረዳት በቂ ጊዜ ያገኛል።x

በተመሳሳይ ወቅት (እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም.) በእንግሊዝ የወጣው ህግ (statutory instrumnets act) ከተወሰኑ አስተዳራዊ ድንጋጌዎች በስተቀር ከሞላ ጎደል ሁሉም ተፈጻሚ ከመሆናቸው በፊት በይፋ እንዲታተሙና ለህዝብ እንዲሰራጩ ያስገድዳል።y ህጉ በማያካትታቸው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ ዓይነቶች ህትመት ቅድመ ሁኔታ ባይሆንም አብዛኛዎቹ የአስተዳደር መ/ቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲታተሙ ያደርጋሉ። ሆኖም በልዩ ህግ ላይ ህትመት እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጠ አስገዳጅ ነው። ድንጋጌው በይፋ ካልታተመ ውጤት ወይም ዋጋ አይኖረውም።

በህንድ ኦፊሴሊያዊ በሆነ ጋዜጣ እንዲታተሙና ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ የሚያስገድድ አንድ ወጥ ህግ የለም። ሆኖም ስልጣን በሚሰጠው ህግ ላይ የህትመት ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ እንደሆነ በአስተዳደር መ/ቤቱ ላይ አስገዳኝነት አለው።z

በኢትዮጵያ ውስጥ ከአዋጅና ደንብ በስተቀር በአስተዳደር መ/ቤቶች በየጊዜው የሚወጡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መመሪያዎች በነጋሪት ጋዜጣ አይታተሙም። ስልጣን የሚሰጠው አዋጅም ህትመትን እንደቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም።a

የመቆጣጠሪያ ስልቶች

በውክልና ስልጣን የሚወጣ አስተዳደራዊ ድንጋጌ ከንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞው ይልቅ ተግባራዊ አስፈላጊነቱ ጐልቶ ተቀባይነት ቢያገኝም ስልጣን በአንድ የመንግስት አካል እጅ እንዲከማች በማድረግ ለዜጐች መብትና ነፃነት አደጋ በመጋረጥ የከፋ ጐን እንዳለውም አይካድም። ገደብ ካልተበጀበትና ቁጥጥር ካልተደረገበት በሙስና ወደ ተዘፈቀ አሰራር፤ ከስልጣን በላይ ወደሆነ ህገ-ወጥ ድርጊት እና ወደ ሌሎች ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ ውድቀቶች ያመራል።

ጥቅሙ ከጉዳቱ ሊታረቅ የሚችለው በአግባቡና ልኩ በታወቀ ገደብ ውስጥ ስራ ላይ የዋለ እንደሆነ ነው። ልቅ ስልጣን ከመስጠት ባላነሰ ልቅነትን አለመቆጣጠር የከፋ አደጋ ያስከትላል። አግባብነት ያለው፣ ፍትሐዊ፣ ህጋዊ፣ ህገ- መንግስታዊ መመዘኛዎችን ያሟላ አስተዳደራዊ ድንጋጌ እንዲኖር ተገቢው ስርዓት ተዘርግቶ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። ቁጥጥሩ በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ይተገበራል። እነዚህም በህግ አውጭው የሚደረግ ቁጥጥር፣ በፍ/ቤት የሚደረግ ቁጥጥር እና ስነ-ስርዓታዊ ቁጥጥር በሚል ይመደባሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ አልፎ አልፎ በተቋማት (ለምሳሌ በእንባ ጠባቂ ተቋም እና በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን) ቁጥጥር ይከናወናል።

በህግ አውጭው የሚደረግ ቁጥጥር

የተወካዮች ም/ቤት ለስራ አስፈፃሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ስልጣን ላይ በአንድ ሶስተኛ አነስተኛ የም/ቤቱ አባላት ጠያቂነት በመወያየት አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ መውሰድ ይችላል።b በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን አንዴ ከተሰጠ በኋላ ከጥቅሙ ጉዳቱ ካመዘነ ወይም በስልጣን አለአግባብ መገልገልን የሚያስከትል ከሆነ የተወካዮች ም/ቤት ለመቀነስ፣ ለማሻሻል ወይም መልሶ ለመውሰድ የሚከለክለው የለም። ይህ በተግባር የሚረጋገጠው ግን በቂ ክትትል በማድረግ በጐና አሉታዊ ጐኖችን መገምገም ሲቻል ነው።

ውክልናው ከተላለፈ በኃላ መከታተልና መቆጣጠሩ አዳጋች እንደመሆኑ አስቀድሞ ልኩን መወሰን ተመራጭ ነው። ስልጣን የሚሰጠው አዋጅ ከመፅደቁ በፊት የተወካዮች ም/ቤት የአንድ ሶስተኛ አነስተኛ ድምፅ ሳያስፈልገው በውክልናው ወሰንና ህገ መንግስታዊነት ላይ ትችተና አስተያየት በመስጠትና ከጅምሩ እርምጃ ለመውሰድ ሰፊ እድል አለው። ስልጣን በውክልና ከመተላለፉ በፊት አስፈላጊነቱ፣ በመሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ውስጥ የማይወድቅ መሆኑ እንዲሁም ተግባር ላይ ቢውል ሊያስከትል የሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በም/ቤቱ አባላት መካከል ሰፊና ጥልቅ ውይይት ሊደረግበት ይገባል።

ህግ አውጭው በሌሎች የተለያዩ መንገዶችም ውጤታማ ቁጥጥር ማድረግ ይችላል። በእንግሊዝ የማንጠፍ ስነ-ስርዓት (laying procedure) አንደኛው የመቆጣጠሪያ ዘዴ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት አንጻር የአስተዳደራዊ ድንጋጌዎችን የስልጣን ወሰን በየጊዜው እየመረመረ ለፓርላማው ሪፖርት የሚያቀርብ ቋሚ የፓርላማ ኮሚቴ በማቋቋም ውጤታማ ቁጥጥር ለማድረግ ተችሏል። እ.ኤ.አ. በ1944 ዓ.ም የተቋቋመው የአስተዳደር ድንጋጌዎች መርማሪ ኮሚቴ (Statutory Instruments Scrutiny Committee) ምስክሮችን እስከ መጥራትና ተገቢ ሰነዶች እንዲቀርቡለት እስከ ማዘዝ የሚደርስ ሰፊ ስልጣን ነበረው። ዋና ተግባሩም ደንብና መመሪያ በህግ አውጭው በተሰጠ ስልጣን መሰረት ስለመውጣቱ፣ ምክንያታዊ ስለመሆኑ፣ ወደኋላ ተፈጻሚ አለመሆኑ ወዘተ… በአጠቃላይ ህጋዊና ህገ መንግስታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ሲሆን በዚህም ስኬታማ ስራዎችን ሰርቷል።c

ስነ-ስርዓታዊ ቁጥጥር

ማንኛውም ስልጣን ተግባር ላይ በሚውልበት ወቅት ስልጣኑ የተሰጠው አካል ሊከተል የሚገባው የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታ የበዘፈቀደ አሰራርን ያስወግዳል፤ ከዚህም ባሻገር አስተዳደራዊ ፍትሕን በማስፈን ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው። በአገራችን አዲስ በወጣው የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ቁ. 1183/2011 የምክክርና የህትመት ስነ-ስርዓቶች አስገዳጅነት ያላቸው ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ የወጣ ደንብና መመሪያ የተፈጻሚነት ውጤት የሌለው ዋጋ አልባ እንደሆነ ይቆጠራል።

በፍርድ ቤት የሚደረግ ቁጥጥር

በብዙ አገራት በውክልና የሚወጣ ህግ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ቁጥጥር ይደረግበታል። ‘ማንኛውም አስተዳደራዊ ድርጊት ወይም ውሳኔ ከስልጣን በላይ (ultra vires) መሆን የለበትም’ የሚለው መርህ በስራ አስፈፃሚው በሚወጡት ደንቦችና መመሪያዎች ላይም ተፈጻሚነት አለው። ፍ/ቤቶች ህጋዊነትን በማረጋገጥ ከህግ ውጭ ሆኖ የተገኘውን ውድቅ የማድረግ ወይም የመሰረዝ ስልጣን ከሌላቸው ለዜጐች መብትና ነፃነት ምንም አይነት ዋስትና አይኖርም።

አስተዳደራዊ ድንጋጌ በሁለት ዋና ምክንያቶች ማለትም ከህገ መንግስታዊነትና ከህጋዊነት አንጻር በፍ/ቤት ይታረማል። የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ ከራሱ ከደንብና መመሪያው ወይም ስልጣኑን ከሰጠው ማቋቋሚያ አዋጅ (enabling act) ይመነጫል። ህገ መንግስት የአንድ አገር የበላይ ህግ እንደመሆኑ በህግ አውጭው የሚወጣውን ህግ ጨምሮ ማንኛውም ደንብና መመሪያ ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር ከተቃረነ አስገዳጅ ውጤት አያገኝም። አንዳንዴ ስልጣኑን የሰጠው አዋጅ ራሱ ኢ-ህገ መንግስታዊ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ህግ አውጭው ስልጣኑን ቆርሶ በውክልናው ሲያስተላለፍ የውክልናው መጠን ቴክኒካል ከሆኑ የአፈፃፀም ጉዳዮች መዝለል የለበትም። ከዚህ በተቃራኒ መሰረታዊ የህግ ማውጣት ስልጣን በውክልና ከተላለፈ ውክልናው በራሱ ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው።

የተወካዮች ም/ቤት የህግ አውጭነት ስልጣን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55 ላይ ተዘርዝሯል። እነዚህ በከፊል ሆነ በሙሉ በደንብና መመሪያ እንዲወሰኑ ውክልና ሊሰጥ አይችልም። ከተሰጠም ውክልናው ኢ-ህገ መንግስታዊ ይሆናል።

ሁለተኛው በውክልና የሚወጣ ህግ በፍርድ የሚታይበትና የሚታረምበት ምክንያት ህጋዊነቱ ሲሆን ይህም ሙሉ በሙሉ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ስልጣን ስር ይወድቃል። ህጋዊነት ሲባል ከስልጣን በላይ የሆነ ድርጊት ወይም የስልጣን አለአግባብ መገልገልን ያመለከታል። ደንብ ወይም መመሪያ ስልጣን ከሰጠው አዋጅ ጋር ሲነጻጸር ከስልጣን በላይ ከሆነ ውጤትነት የሌለው ዋጋ አልባ ህግ ነው። የአስተዳደር መ/ቤቶች ህግ ሳይፈቅድላቸው የዜጐችን መብት በአስተዳደር ውሳኔ መጣስ እንደማይችሉት ሁሉ ከስልጣን በላይ የሆነ መመሪያ ድርጊታቸውን የህጋዊነት ሽፋን ሊያሰጠው አይችልም።

በሌሎች አገራት ለምሳሌ በእንግሊዝ፣ በህንድ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ የውክልና ስልጣን በህግ የተወሰነውን ገደብ ባያልፍም አግባብነት በሌለው መንገድ ግልጋሎት ላይ ከዋለ ዋጋ አይኖረውም። ለአብነት ያህል አስተዳደር መ/ቤቱ መመሪያውን ያወጣው ለበጐ ዓላማ ሳይሆን ሆነ ብሎ በክፋት አንድን ወገን ለመጉዳት በማሰብ ከሆነ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታዎች ልዩነት ወይም አድልኦ የሚያደርግ ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ከዚህ ባሻገር የመመሪያው ይዘት ፈጽሞ የማይገባና ግልጽነት የጐደለው ከመሆኑ የተነሳ እርግጠኛ የሆነ ትርጓሜ ሊሰጠው የማይቻል ከሆነ ጥያቄ ሲቀርብበት ይሰረዛል።

በእኛ አገር በተመሳሳይ ሁኔታዎች ፍ/ቤት ጣልቃ የሚገባበት ህጋዊ መሰረት አይኖርም ማለት ይቻላል። በግልጽ ህግ ካልተፈቀደ በቀር ድረስ የስልጣን ገደቡን ያላለፈ ደንብ ወይም መመሪያ የቱንም ያህል ኢ-ምክንያታዊ ወይም ኢ-ፍትሃዊ ቢሆን በመደበኛ ፍ/ቤት ሊታረም ሆነ ሊሰረዝ አይችልም። የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ በአስተዳደር ተቋማት ሊሻር የሚችልባቸውን ሶስት ምክንያቶች ይዘረዝራል። በዚህ መሰረት የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንድን መመሪያ መሻር የሚችለው የአዋጁን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል ከወጣ፤ ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ ከሆነ ወይም በእርከን ከመመሪያ በላይ ከሆኑ ሌሎች ህጎች ጋር የሚቃረን ሲሆን ነው።d

በአገራችን ስላለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ አጠቃላይ ዳሰሳ

በህግ አውጭው የወጣ አንድ አዋጅ ስጋና ደም ለብሶ በተጨባጭ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ብዙውን ጊዜ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች ያስፈልጉታል። በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተወካዮች ም/ቤት ከሚወጣው አዋጅ ይልቅ በየጊዜው ስለሚደነገጉት መመሪያዎች የተለየ ቅርበትና እውቀት አለው። በእያንዳንዱ አስተዳደር መ/ቤት ውስጥ የመንግስት ስራ የሚሰራው ‘በህጉ መሰረት’ ሳይሆን ‘በመመሪያው መሰረት’ ስለመሆኑ እውነትነት ያለው ሀቅ ነው።

ስልጣን በሰጠው አዋጅ መሰረት እስከወጣ ድረስ በመመሪያ መስራቱ ባልከፋ ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ‘መመሪያ’ ሲባል ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት፣ ለህገ ወጥነትና ለኢ-ፍትሐዊነት የሚሰጥ የሽፋን ልብስ ነው። ዋና ችግሩ ከውክልና ሰጪው ከተወካዮች ም/ቤት ይጀምራል። በተለያዩ አዋጆች ላይ ለሚኒስትሮች ም/ቤትና ለአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና የሚተላለፈው ስልጣን እንደሰማይ የሰፋ ቢሆንም ጥያቄው የህግ የበላይነትና የህገ-መንግስታዊነት ሆኖ ተመክሮበት አያውቅም። ከዚህ ባሻገር አነስተኛ ስነ-ስርዓት ያልነበረ መሆኑ መመሪያዎች ‘የስርቻው ስር ህጎች’ ሆነው እንዲቀሩ አድርጐት ቆይቷል።

መመሪያ የሌለው መመሪያ

አስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት (Rule–Making Procedure) ግልፅነትና የህዝብ ተሳትፎን በማሳካት ረገድ ካለው ወሳኝ ሚና በተጨማሪ በዘፈቀደ በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች አማካይነት የዜጐች መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ከለላና ውጤታማ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው። በአገራችን እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ለየትኛውም አይነት አስገዳጅ ስነ-ስርዓት አይገዙም ነበር። እስከ አሁን ድረስ ህግ አውጭው አንድ ደንብ በሚኒስትሮች ም/ቤት የሚወጣበትን ስነ-ስርዓት በአዋጅ ደንግጐ አላስቀመጠም።

ከመሰረታዊ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ ቀላል በሆነ መንገድ ታትሞ መሰራጨት ያለበት መሆኑ ነው። በተግባር ያለው እውነታ እንደሚያሳየን መመሪያዎች በአስተዳደር መ/ቤቱ ውስጥ ተደብቀው የሚቀሩ የጓዳ ህጐች ናቸው። አብዛኛዎቹ መመሪያዎች በ3ኛ ወገን ላይ አስገዳጅነት ቢኖራቸውም ሊታወቁና ሊከበሩ የሚችሉበት አንዳችም አማራጭ መንገድ የለም። ግለሰቦች እና ድርጅቶች በመመሪያው መሰረት እርምጃና ቅጣት ሲወሰድባቸው መመሪያዎቹ ባልታወቁበትና ባልታተሙበት ሁኔታ ነው። ይህም የግልፅነትን መርህ የሚጥስ፣ ለሙስናና ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል በአጠቃላይ ለአስተዳደራዊ ብልሹነት የሚያጋልጥ አደገኛ ሁኔታ ነው። ማንም ዜጋ ላልታተመ፣ ለማያውቀው እና ሊያውቀው ለማይችል ህግ የመገዛት ግዴታ የለበትም።

የመመሪያዎች አለመታተም ተፈጻሚነት (ውጤት) የሚያገኙበትን ጊዜ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለመሆኑ አንድ መመሪያ ውጤት የሚኖረው ከመቼ ጀምሮ ነው? በተለምዶ በመ/ቤቱ ኃላፊ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ውጤት ያገኛል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ያልተፈረመ መመሪያ በተግባር ተፈጻሚ የሚደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል። በአንዳንድ መመሪያዎች ላይ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን በግልጽ ቢመለከትም የመ/ቤቱ ኃላፊ ፊርማ የለውም።

በስነ-ስርዓት አለመኖር ምክንያት በየአስተዳደር መ/ቤቱ የሚወጡት መመሪያዎች ቅርጽና ይዘት ወጥነት አጥቷል። መመሪያ ለአውጭውም አካል ሳይቀር አስገዳጅ ህግ እንደመሆኑ አነስተኛ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል። ለምሳሌ የመመሪያው መለያ ቁጥር፣ የተሻረ መመሪያ ካለ ቁጥሩና የወጣበት ጊዜ አንዲሁም ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ቁጥርና አንቀጽ መጥቀስ ይገባል። እንዲሁም መመሪያው በምእራፍ፣ በክፍልና በአንቀጽ (ቁጥር) ተከፋፍሎ አስገዳጅነት ያለው ድንጋጌ ሊያስቀምጥ ይገባል። ይዘቱ ጥናት፣ ጥቆማ ወይም ምክር ወዘተ… መምሰል የለበትም።

ህትመትና የሰበር ችሎት አቋም

መመሪያዎች በይፋ አለመታተማቸው በፍትሐብሔር እና በወንጀል ክርክሮች የሚረጋገጡበትን መንገድ ያወሳስበዋል። አውጭው አካል በተከራካሪነት ሲሰለፍ መመሪያ ጠቅሶ የሚያቀርበው ክርክር መመሪያውን እንደ አንድ የማስረጃ ዓይነት ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ መደገፍ ይኖርበታል። ምክንያቱም ከእርሱ በስተቀር ፍርድ ቤቱ ሆነ ባለጋራው ተከራካሪ ስለመኖሩ ሊያውቁ አይችሉም። ስራ ላይ መዋሉ ሊታወቅና ሊረጋገጥ የሚችለው የተባለውን መመሪያ እንዳወጣ የሚከራከረው የመንግስት ተቋም እንደ ሰነድ ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር ማያያዝ ሲችል ነው።

አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠረው መመሪያውን ያወጣው አካል ተሳታፊ በማይሆንባቸው ክርክሮች ይዘቱ በአንደኛው ወገን መከራከሪያ ሆኖ ሲቀርብ ነው። ለምሳሌ ይህ ተከራካሪ ትክክለኛውን የመመሪያ ቁጥር መለየት ሳይችል ሲቀርና መኖሩ በተቃራኒ ወገን ሲካድ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው አቅጣጫ ምንድነው? በመመሪያው መኖር ተጠቃሚነቱን ገልጾ የሚከራከረው ወገን የማስረዳት ግዴታውን ስላልተወጣ ክርክሩን ውድቅ ማድረግ አንደኛው አማራጭ ነው። ሆኖም ይህ አካሄድ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል። መሰረታዊ የማስረጃ ህግ ደንቦችንም አያሟላም። አንድ ተከራካሪ አስገዳጅነት ያለውን የህግ ድንጋጌ ጠቅሶ ከመከራከር ባለፈ ‘ህግ እንደማስረጃ’ እንዲያቀርብ አይገደድም።

‘መመሪያ ህግ ነው’ እስከተባለ ድረስ ካለበት ቦታ ማስቀረብ ዞሮ ዞሮ ፍርድ ቤቱ ጫንቃ ላይ ያርፋል። ሆኖም ያልታተመ መመሪያ ፍርድ ቤቶች ግንዛቤ እንዲወስዱበት አይገደዱም። ከዚህ በተቃራኒ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 40804e በሰጠው የህግ ትርጉም፤

…በመንግስት የሚወጡ ሕጏች እና መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ወዘተ በግልጽ የሚታወቁ እንደመሆናቸው ፍ/ቤቶች (ዳኞች) ግንዛቤ የሚወሰዱባቸው ናቸው።

ችሎቱ ያንጸባረቀው አቋም ዳኞች ያልተጻፈ እንዲያነቡ የማስገደድ ያክል ነው። እንደ ችሎቱ ከሆነ መመሪያ-ጠቀስ ክርክር በተከራካሪ ወገኖች ባይቀርብም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዳ መመሪያ ካለ ፍርድ ቤቱ መኖሩን ማወቅ አለበት (በይግባኝ ደረጃ ደግሞ ማወቅ ነበረበት) ማለት ነው።

የነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ዳኞች ያልታተሙ መመሪያዎችን ግንዛቤ እንዲወስዱባቸው አያስገድድም። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/3/ ህግ ተርጓሚውን ጨምሮ ማናቸውም የፌደራልና የክልል የመንግስት አካላት እንዲሁም ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ማንኛውም ድርጅት በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣን ህግ የመቀበል ግዴታ (shall take judicial notice of Laws published in the Federal Negarit Gazeta) አለበት። ስለሆነም ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 40804 ያንጸባረቀው አቋም ከነጋሪት ጋዜጣ ህጉ ጋር አይስማማም።

ችሎቱ በከፊል የተለሳለሰ አቋም የያዘው በሰ/መ/ቁ. 83060f ሲሆን በመዝገቡ በሰፈረው የህግ ትርጉም መሰረት ክርክር የቀረበበት መመሪያ ይዘት ለውሳኔ አሰጣጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፍርድ ቤት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 145(1) እና 345(1)(ለ) ማስቀረብ ይገባዋል። ይህም ማለት አንደኛው ተከራካሪ መመሪያ ጠቅሶ ካልተከራከረ ወይም የመዝገቡ አካል እንዲሆን ካላሳሰበ በስተቀር የማስቀረብ ግዴታ አይኖርም። ፍርድ ቤትም በዚህ መልኩ ያልተነሳን ወይም በክርክሩ ያልተጠቀሰን መመሪያ በውሳኔው ከግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ብቻ ውሳኔው በህግ ስህተት በይግባኝ ወይም በሰበር ሊሻር አይገባውም።

አዲስ የወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ ከህትመት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩትን ችግሮች ይቀርፋቸዋል ተብሎ ይታመናል። በአዋጁ አንቀጽ 17 መሰረት ማንኛውም መመሪያ ህጋዊ ውጤት የሚኖረው የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲመዘግበው ሲሆን የመዘገበውን መመሪያ በድህረ ገጹ ላይ መጫን ይኖርበታል። በተጨማሪም ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ያወጣውን መመሪ አሳትሞ ለሚመለከታቸው መንግስታዊና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማሠራጨት ግዴታ ያለበት ሲሆን ተደራሽ እንዲሆን በተቋሙ ድህረ ገጽ ላይ መጫን አለበት። ማንኛውም የመመሪያውን ቅጂ ማግኘት የሚፈልግ ሰው መመሪያውን ባለበት ሁኔታ የመመልከት ወይም ወጪውን ሸፍኖ ከአስተዳደር ተቋሙ የማግኘት መብት አለው።

የነጋሪት ጋዜጣ የህትመት ቅድመ ሁኔታ

ለመመሪያዎች አለመታተም ዋናው ምክንያት ልማድ እንጂ ህግ አይደለም። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ማናቸውም የፌደራል መንግስት ህግ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣ ያስገድዳል።g አዋጁ መታተም ያለባቸውን የፌደራል መንግስት ህጎች በትርጓሜ አሊያም በዝርዝር አልለየም። ‘መመሪያ’ ከአዋጅና ደንብ ቀጥሎ አስገዳጅ ውጤት ያለው አንደኛው የፌደራል መንግስት ህግ እንደሆነ ክርክር አያስነሳም። ስለሆነም መመሪያዎች አለመታተማቸው የቆየ ልማድ እንጂ ህጉ በልዩ ሁኔታ ከህትመት ነጻ ስላደረጋቸው አይደለም።

የቋንቋ ጉዳይ

የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው። ባለስልጣኑ እንግሊዝኛውን ሲያስቀር ቋንቋውን አንብበው የማይረዱ በርካታ የውጭ አገር ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ዘንግቶታል ለማለት ይከብዳል፤ ችላ ብሎታል እንጂ። የዚህ የቆየ ልማድ ተገላቢጦሹን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እናገኛለን። ባንኩ በመመሪያ አወጣጥ ሂደት አማርኛ አይጠቀመም፤ እንግሊዝኛ ብቻ እንጂ። ይህ የልማድ አሰራር በግልና በመንግስት ባንኮች የህግ አተገባበር መሰረታዊ ችግር ላይፈጥር ይችላል። ሆኖም በህግ ተርጓሚው ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። እንግሊዝኛ የማወቅ ያለማወቅ አይደለም ቁምነገሩ።

በእንግሊዝኛ ተረቆ የተዘጋጀ ህግ በአማርኛ ወይም በሌላ የክልል ቋንቋ ሲተገበር ውስብስብ ችግር ያስከትላል።h በአንደኛው የሚገኝ ቃል በሌላኛው አይኖርም። አንደኛው በአግባቡ የገለጸውን ሀሳብ አንዳንዴ ሌላኛው ያዛባዋል። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተም ያለበት በአማርኛና በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ሲሆን በመካከላቸው የሚፈጠረውን የይዘት ልዩነት ለማስታረቅ አማርኛውን ብቻ ገዢ አድርጎ መጠቀም ውጤታማ አማራጭ ባይሆንም የአማርኛው የበላይነት ህጋዊ ዕውቅና አግኝቷል።i

ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በነጋሪት ጋዜጣ መታተም ያለባቸው ሁሉም የፌደራል መንግስት ህጎች ናቸው። ሆኖም በተግባር ሲታይ መመሪያዎች ለብቻቸው አፈንግጠው አይታተሙም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚዘጋጁበት መንገድ በውክልና ስልጣን የሰጣቸው ህግ የያዘውን መልክና ቅርጽ ሊያንጸባርቁ ይገባል። የህግ አውጭነት ስልጣናቸው ምንጭ የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የሚጻፈው በአማርኛና በእንግሊዝኛ እስከሆነ ድረስ መመሪያዎችም ይህንኑ ተከትለው በሁለቱም ቋንቋዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻር በአንደኛው ቋንቋ ብቻ የተዘጋጀ መመሪያ አስገዳጅ ውጤት ሊኖረው አይገባም።

የአስተዳደር መ/ቤቶች እየተከተሉት ያለው ዝብርቅርቅ የቋንቋ አጠቃቀም ከሚያስነሳው የህግ ጥያቄ በተጨማሪ ወደ አገራችን የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችና ባለሀብቶች የአገሪቱን ህግ አክብረው ለመንቀሳቀስና ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዝ ይልቅ ተጨማሪ ጫና ይፈጥርባቸዋል። ሆኖም የቋንቋ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ብዙም አሳሳቢ ሆኖ አለመገኘቱ ሲታይ የተለመደው አሰራር ከህግ አውጭው አዋጅ በስተቀር የዳኝነት አካሉ ፍርድ መቼም የሚያስተካክለው አይመስልም።

በሰ/መ/ቁ. 43781j ብሔራዊ ባንክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ያዘጋጀው መመሪያ በአማርኛ ተተርጉሞ ባለመገኘቱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውጤት ቢነፈገውም የሰበር ችሎት፤

በመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የሚወጡት የበታች ሕጎች… በተወሰነ ቋንቋዎች እንዲጻፉ የሚያስገድድ ሕግ የለንም።

በሚል ምክንያት የመመሪያውን አስገዳጅነት ተቀብሎታል። ችሎቱ ‘ህግ የለም’ ይበል እንጂ ህጉ አለ። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 መመሪያዎች እንዲታተሙ ከዚያም አልፎ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ ያስገድዳል። የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/2/ በግልጽ እንደሚደነግገው ማናቸውም የፌደራል መንግስት ህግ የሚወጣው በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ይሆናል። ስለሆነም የህትመት ቅድመ ሁኔታ ተፈጻሚነት በፌደራል መንግስቱ ህጎች ላይ እንጂ በተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ላይ ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ላይ ብቻ አይደለም። ችሎቱ ‘መመሪያ በፌደራል መንግስት ህጎች ውስጥ አይጠቃለልም’ የሚል አቋም ከያዘ በመዝገቡ ላይ ‘መመሪያ ተላልፏል’ በሚል የወንጀል ክስ ቀርቦበት በይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ነጻ የተደረገውን ተጠሪ በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሊለው ባልተገባ ነበር። ምክንያቱም የተላለፈው ‘ህግ’ የለም።

የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ በአንቀጽ 15 ላይ በአስተዳደር ተቋም የሚወጣ ማንኛዉም መመሪያ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዘጋጀት እንዳለበት በግልጽ በመደንገግ ለረጅም ጊዜ ስር የሰደደውን ችግር መቋጫ አበጅቶለታል።

በአንዳንድ ህጎች የሚገኙ ቅድመ ሁኔታዎች

ምንም እንኳን እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በአገራችን የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥን የሚገዛ ወጥ ህግ ያልነበረ መሆኑ እውነት ቢሆንም በተወሰኑ አዋጆች ላይ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች አስገዳጅ ሆነው ተደንግገዋል። በተጨማሪም በራስ ተነሳሽነት የዳበሩ መልካም አሰራሮችም ብቅ ብቅ እያሉ ነው።k በህግ ከተደነገጉ አስገዳጅ ስርዓቶች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን መመሪያ ከማውጣቱ በፊት ባለፈቃዶችን፣ ከፍተኛ የኤሌትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን፣ የኢነርጂ ብቃትን የሚተገብሩ ተቋማትን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሊወክሉ ይችላሉ ብሎ የሚገምታቸውን ሰዎች ማማከር አለበት::l በተጨማሪም ባለስልጣኑ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች የማሳተም ኃላፊነት ያለበት ሲሆን የህትመቱ ሁኔታ የሚወሰነው ግን በራሱ በባለስልጣኑ ነው።m

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የመመሪያ አወጣጥ ስርዓት የአሳታፊነትና የህትመት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል። በዚሁ መሰረት ባለስልጣኑ ማንኛውንም መመሪያ ከማውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ የሲቪል የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪን፣ የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን እንዲሁም የሚመለከታቸው ሌሎች አካላትን ይወክላሉ ብሎ ያመነባቸውን ሰዎች ማማከር ያለበት ሲሆን በዚህ መልኩ የሚወጣው መመሪያ ባለስልጣኑ በሚወስነው ሁኔታ መታተም ይገባዋል።n ከላይ በተመለከቱት ሁለት አዋጆች በምክክር ሂደት የሚሳተፉ ሰዎች ማንነትና የህትመት ቅድመ ሁኔታ የአስተዳደር መ/ቤቱ ባመቸው መንገድ የሚወሰን ጉዳይ ነው።

በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006 ዝርዝር የምክክርና ህትመት ቅድመ ሁኔታዎች ተለይተው ተደንግገዋል። በአዋጁ በአንቀጽ 13/1/ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ እና የኦዲት ደረጃዎችን ከመቀበሉ (adopting)፣ ከማስማማቱ (adopting) ወይም ከማሻሻሉ በፊት ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን የማማከር ግዴታ ተጥሎበታል። ሆኖም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ተቋማትንና ሰዎችን ቦርዱ የሚያማክረው አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ብቻ ነው።o

ምንም እንኳን አስገዳጅ የምክክር ስርዓት በቁልፍ ባለድርሻ አካላት ላይ የተገደበ ቢሆንም አስተያየቶች የሚስተናገዱበት ሂደት ሲታይ ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ በተግባር ያረጋግጣል። በአዋጁ አንቀጽ 14/1/ እንደተመለከተው የህዝቡን አስተያየት መቀበል እንዲቻል በቦርዱ ድረ-ገፅ እና ሀገር ዓቀፍ ስርጭት ባላቸው ከሁለት ባላነሱ ዕለታዊ ጋዜጣዎች ቢያንስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ማስታወቂያ በማውጣት እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህዝቡ በደረጃዎቹ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ መጋበዝ አለበት። አስተያየት መስጠት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ቦርዱ ማስታወቂያ ካወጣበት የመጨረሻ ቀን አንስቶ በስድሳ ቀናት ውስጥ ለቦርዱ በጽሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል። ህዝባዊ አስተያየት ለመሰብሰብ በድረ-ገፅ እና በጋዜጣ ማስታወቂያ የሚወጣበት ስርዓት በተመሳሳይ መንገድ የፀደቁ ደረጃዎችን ለማሳወቅም ተፈጻሚ ይደረጋል።p

ዝርዝር የመመሪያ አወጣጥ ድንጋጌዎችን ባይዝም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ በብቃት መስፈርቶች አዘገጃጀት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በዘርፉ የተሰማሩ የነጋዴዎች አደረጃጀቶችን እንዲያሳትፉ ግዴታ ይጥላል።q

በአንዳንድ ህጎች ላይ ደግሞ መመሪያው በበላይ አካል እንዲፀድቅ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል። አጽዳቂው አካል አንዳንዴ በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን በተወሰኑ አዋጆች ደግሞ በድፍን አነጋገር መመሪያው ‘በመንግስት’ እንደሚጸድቅ ተመልክቷል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲr ዳይሬክተር የኤጀንሲውን ሰራተኞች ‘በመንግስት በሚጸድቅ መመሪያ’ የመቅጠርና የማስተዳደር ስልጣን ተሰጥቶታል። በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የሚዘጋጅ መመሪያ ረቂቁ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር መቅረብ ያለበት ሲሆን የሚወጡት መመሪያዎች የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት የማድረግ ግዴታ አለበት።s በበላይ አካል መጽደቅና የማሳወቅ ግዴታ በባለስልጣኑ አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን ላይ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። የማሳወቅ ግዴታው ባለስልጣኑ መመሪያውን እንዲያሳትም አያስገድድም። ያም ሆኖ ግን ቢያንስ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

ተሰበጣጥረው ከሚገኙት ጥቂት ድንጋጌዎች በተሻለ መንገድ ደንብና መመሪያ አወጣጥ ስርዓትና መሰረታዊ መርሆዎችን በተመለከተ በተብራራ መልኩ ተደንግጎ የሚገኘው በተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 60 ላይ ነው። የድንጋጌው ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

60.ደንብና መመሪያ ስለማውጣት

1. ምክር ቤቱ በሚያወጣው ህግ ማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ በውክልና እንዲወጣ ስልጣን ሊሰጥ ይችላል።

2. ደንብና መመሪያ እንዲወጣ በህግ ምክር ቤቱ የውክልና ስልጣን በግልፅ ካልሰ በስተቀር ማንኛውም አካል ደንብ ወይም መመሪያ ማውጣት አይችልም

3. ምክር ቤቱ በሚያወጣው ህግ በውክልና ደንብና መመሪያ እንዲወጣ ስልጣን ሲሰጥ ደንቡን እና መመሪያውን የሚያወጡ አካላትን በግልፅ ማመልክት አለበት።

4. ማንኛውም የሚወጣ ደንብ የአዋጁን ወሰን የጠበቀና የተጣጣመ መሆን ይኖርበታል።

5. ማንኛውም የሚወጣ መመሪያ የአዋጁን እና የደንቡን ወሰን በጠበቀና የተጣጣመ መሆን ይኖርበታል።

6. ምክርቤቱ በሚያወጣው ህግ ላይ ደንብና መመሪያ እንዲወጣ ሲወሰን የተጠቀሰው ደንብና መመሪያ ህጉ በስራ ላይ በዋለ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ መውጣት አለበት።

7. ማንኛውም መመሪያ ለማንኛውም ሰው ተደራሽ መሆን ይኖርበታል፣ ተደራሽነቱንም የሚመለከተው ተቋም የበላይ ኃላፊ የማረጋገጥ ግዴታ ይኖርበታል።

8. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (7) የተደነገገውን የመመሪያዎች ተደራሽነት ኃላፊነት ያልተወጣ ተቋም የበላይ ኃላፊ ተጠያቂነት ይኖርበታል።

መመሪያ አወጣጥ በአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ

የመመሪያ ትርጓሜ እና እንደምታው

በአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 2/2/ መመሪያ እንደሚከተለው ተተርጉሟል።

ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ ሲሆን በስራ ላይ ያለ መመሪያን የሚያሻሻል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድንም ይጨምራል።

ለመመሪያ የሚሰጥ ትርጓሜ መመሪያ የሆነውን ካልሆነው መለየት የሚያስችል ግልጽ መለኪያዎች ሊያቅፍ ይገባል። በአስተዳደር ህግ ውስጥ በመመሪያ እና የአስተዳደር ውሳኔ መካከል ያለው ልዩነት አሁንም ድረስ ፍንትው ብሎ አልጠራም። በርካታ የመስኩ ምሁራን የልዩነቱን ወሰን መለያ ክር አበጅተው ለማስመር ብዙ ለፍተዋል። በፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ላይም መመሪያን ከውሳኔ ለመለየት የሚያስችሉ መመዘኛዎች ለማስቀመጥ ተሞክሯዋል። የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ያላቸው አገራት እንዲሁ በህጋቸው መለያ መንገዶችን ደንግገዋል። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ግን አጠራጣሪ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አልቻሉም። አከራካሪ ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አዳጋች ቢሆንም በአንድ አገር የመመሪያ አወጣጥ ስርዓትን የሚደነግግ ህግ መመሪያን ሲተረጉም ይብዛም ይነስም የትርጓሜው ይዘት መመሪያ የሆነውን ካልሆነው መለየት የሚያስችል መለኪያ ማካተት ይጠበቅበታል።

የህግ አውጭው ትርጓሜ የሚተረጎመውን ነገር መሰረታዊ ባህርይ ከመግለጽ ባሻገር ተፈጻሚ ለሚሆነው ህግ ዓላማ ይዘቱን በማስፋት ወይም በማጥበብ ሊመጥነው ይችላል። ለምሳሌ በርካታ ሰዎች የሚሰሩት ስራ ‘ሰራተኛ’ የሚያሰኛቸው ቢሆንም በአሰሪው መሪነት የሚለው አገላለጽ ትርጓሜውን በማጥበብ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የሚካተቱን ሰራተኞች ውስን አድርጎታል።

ከላይ ከተቀመጠው ጥቅል ሀሳብ መነሻነት በአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጁ የመመሪያ ትርጓሜ ውስጥ የታቀፉ ሶስት አላባውያንን እንደሚከተለው በዝርዝር እናያለን።

ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ስልጣን

በአዋጁ ላይ “ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት” የሚለው አነጋገር መመሪያ ብቻ የሚጋራው መሰረታዊ የባህርይ መግለጫ አልያዘም። የአስተዳደር ተቋማት የህግ አውጭነትና ዳኝነታዊ ስልጣናቸው ምንጭ ህግ አውጭው እንደመሆኑ ሁለቱንም ተግባራት የሚያከናውኑት በውክልና ስልጣናቸው ነው። በተጨማሪም የውክልና ስልጣንን የትርጓሜ አካል ማድረጉ ስልጣን ሳይኖር የሚወጣውን መመሪያ ከትርጓሜው ውጭ የማድረግ ያልተፈለግ ውጤት ያስከትላል።በአዋጁ አንቀጽ 50/1/ ለ እና 56/2/ መሰረት ከውክልና የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ መመሪያ የክለሳ አቤቱታ ሲቀርብበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚሻር ተመልክቷል። ፍርድ ቤቱ የመሻር ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ግን አቤቱታ የቀረበበት “የህግ ሰነድ” በእርግጥ መመሪያ ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ጭብጥ ምላሽ መስጠት አለበት። የአንቀጽ 2/2/ ትርጓሜ ፍርድ ቤቱ ይህን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው መመዘኛ አልያዘም።

በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል

ከውክልና ስልጣን በተጨማሪ በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት ማስከተሉ የመመሪያ ትርጓሜ አካል ሆኗል። አነጋገሩ በይዘቱ ሰፊ ስለመሆኑ ማስተዋል አይከብድም። በአንድ በኩል ከ ‘መብት’ በተጨማሪ ‘ጥቅም’ የትርጓሜው አካል መሆኑ በሌላ በኩል ‘በህጋዊ ውጤት’ ሳይገደብ ማናቸውንም ዓይነት ‘ውጤት’ ካስከተለ በመመሪያ ውስጥ ሊፈረጅ እንደሚችል ሲታይ “የህግ ሰነድ” እስከሆነ ድረስ መመሪያ የማይባል ሊኖር ስለመቻሉ ማሰብ ይከብዳል።

‘በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል’ የሚለው አነጋገር በአንድ በኩል የመመሪያን አስገዳጅ ወይም አሳሪ /binding effect/ ባህርይ ለማመልከት የታሰበ ይመስላል። አገላለጹ ግን ይህንን በማያሻማ መንገድ አያመለክትም። ‘ውጤት’ የሚለውን ቃል ከአቅሙ በላይ ለጥጠን ለመረዳት ብናስብ እንኳን ለአስገዳጅ ወይም አሳሪ ውጤት ምትክ አይሆንም። በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረበው አጭር ማብራሪያt ‘በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል’ የሚለው አገላለጽ እንደምታው ሲያስረዳ በአንድ በኩል በዜጎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች ውጤት የሌላቸው የአስተዳደር ተቋማትን ማለትም የአስተዳደር ተቋሙ ውስጣዊ አሰራር ብቻ የሚደነግጉ “መመሪያዎች” ከዚህ አዋጅ የሥልጣን ወሰን ውጪ መሆናቸውን ካመለከተ በኋላ ሁለተኛውን እንደምታውን ደግሞ በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል፤

ማንኛውም በአስተዳደር ተቋማት የሚወጣ፤ በዜጎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች ውጤት ያለው ሰነድ መመሪያ ተብሎ እንደሚጠራ እና መውጣት የሚገባውም በአዋጁ የተደነገጉ ሥነ ሥርዓቶችን በመከተል ብቻ መሆኑን…ይህም አሁን ባለው የአስተዳደር ተቋማት ወጥነት የሌለው ተለምዶአዊ አሰራር እንደ ማኑዋል፣ ጋይድላይኖች፤ ሰርኩላር እና የመሳሰሉት ሰነዶች በሰዎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች ውጤት እስካላቸው ድረስ መመሪያ ተብለው እንዲወሰዱ እና የመመሪያ አወጣጥ ሥነሥርዓትን ተከትለው እስካልወጡ ድረስ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ይህም ያለው ተለምዶአዊ አሠራር የህግነት ውጤት በሌላቸው መሰል ሰነዶች መብት እና ግዴታዎች የሚጣለበትን ያልተገባ አሰራር ያስቀራል ተብሎ ታምኖበታል።

በማብራሪያው ላይ ‘የአስተዳደር ተቋሙ ውስጣዊ አሰራር ብቻ የሚደነግጉ’ መመሪያዎች በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ውጤት እንደማያስከትሉ የቀረበው አገላለጽ ሁል ጊዜ እውነት አይሆንም። ይህን የሚወስነው ይዘታቸው ነው። በተመሳሳይ መልኩ ማኑዋል፣ ጋይድላይኖች፤ ሰርኩላር እና የመሳሰሉት ሰነዶች በሰዎች መብት እና ጥቅም ላይ ውጤት ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል። ስለሆነም በማብራሪያው ላይ “ውጤት እስካላቸው ድረስ” የሚለው አገላለጽ ለሁሉም “የህግ ሰነዶች” የሚያገለግል እንጂ የአስተዳደር ተቋሙ ውስጣዊ አሰራር የሚደነግጉትን ከትርጓሜው አያገልም።

ከማብራሪያው እንደምንረዳው አዋጁ መመሪያን የሰዎችን ጥቅም የሚነኩና የማይነኩ በሚል ለሁለት መክፈል የፈለገበት ምክንያት የመመሪያ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ተፈጻሚ የሚሆንባቸውንና የማይሆንባቸውን ለመለየት ነው። ይህ ደግሞ ሁለት ጎልተው የሚታዩ ችግሮች አሉት። እነዚህም፤

‘በሰዎች መብትና ጥቅም ውጤት የሚያስከትል’ የሚለው አገላለጽ መነሻውና መድረሻው የማይታወቅ ሰፊ አገላለጽ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ መብትና ጥቅምን ከውጤት ጋር በማስተሳሰር ውጤት የሚያስከትለውን ከማያስከትለው ለመለየት የሚያስችል ፍርድ ቤቶችና የአስተዳደር ተቋማትን የሚያግባባ ግልጽ መመዘኛ ለማስቀመጥ በጣም ያዳግታል። በዚህ የተነሳ የአስተዳደር ተቋማት በቅንነት እንኳን ቢሆን በመብትና ጥቅም ውጤት አያስከትልም ብለው በማመን አስገዳጅ የመመሪያ አወጣጥ ስነ ስርዓት ባለመከተል የሚያወጡት መመሪያ በፍርድ ቤቶች እይታ ደግሞ ‘ውጤት የሚያስከትል’ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል። እንዲህ ዓይነት አለመናበብ መመሪያው እንዲሻር ምክንያት ይሆናል። በዚህ መልኩ መመሪያዎች በስነ ስርዓት ጥሰት ምክንያት በተደጋጋሚ ሲሻሩ ቀጥተኛ የጎንዮሽ ውጤት ከሆነው የሀብት ብክነት በተጨማሪ በአጠቃላይ ውጤታማ አስተዳደር ላይ የሚያስከለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መገመት አይከብድም።

የህግ ሰነድ

‘የህግ ሰነድ’ የመመሪያ ትርጓሜ ማሳረጊያ ሆኖ ተቀምጧል። መመሪያ ‘የህግ ሰነድ’ ነው ሲባል ግን ምን ለማመልከት ነው? ቃሉን ማንኛውም ሰው በሚረዳው መንገድ ከወሰድነው ‘የህግ ሰነድ’ በቀጥታ መብትና ግዴታ እንዲሁም ጥቅም የሚወስነውን ብቻ ሳይሆን የማይወስነ

2 comments:

Popular posts

Recent Posts

LikeBtn

Type

አስተማሪ የሆኑት የችሎት ድራማ ቪዲዮዎች

DOCUMENT & FILES

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd