ፍርድ ቤት ተከሳሹ ከጠየቀው የተለየ ወይም በላይ ዳኝነት ሊሰጥ አይችልም፡፡
ውል ባለመፈጸሙ ምክንያት ተከሳሽ የወሰደውን ቅድሚያ ክፍያ እጥፍ እንዲመለስ ዳኝነት ከጠየቀ መፍትሔ ሊሰጠው የሚችለው ቀብድ ስለሚከፈልበት ሁኔታ አስመልክቶ በተቀመጡት ድንጋጌዎች እንጂ የመቀጮ ስምምነት ላይ ተፈጻሚ በሚሆኑት የህግ ድንጋጌዎች መሰረት አይደለም፡፡
ክርክር የሚመራውና ዳኝነት የሚሰጠው በህጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ነው፡፡ በህጉ ከተዘረጋው የክርክር አመራርና የዳኝነት አሰጣት ስርዓት ውጪ ክርክር የመምራትና ዳኝነት የመስጠት አካሄድ የዳኝነት ሰጪ አካሉን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ የሚታመን ነው፡፡ አንድ ፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጠው በተከራካሪ ወገን የተጠየቀ ሁኖ በሕጉና በውሉ የተፈቀደ መሆኑን በጥንቃቄ አረጋግጦ ሲሆን ተከራካሪ ወገን በሕጉ ወይም በውሉ የተፈቀደለትን መፍትሔ ለማግኘት በግልጽ ዳኝነት መጠየቅ የሚገባው መሆኑን ስለክስ አመሰራረትና የመከላከያ መልስ አቀራረብን የሚደነግጉት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 222፣ 234፣ 235፣ 236 እና 83 ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 224 እና 182 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር ተዳምረው ሲታዩ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የዳኝነት ጥያቄ አይነትና መጠኑን በክሱ ማመልከቻ በግልጽ መስፈር ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡
የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 224 ድንጋጌ ጠቅላላ ይዘቱ ሲታይም ከሳሹ በጉዳዩ ላይ የሚጠይቀው ዳኝነት ፍርድ ቤቱ የክሱን ጭብጥና የማስረጃውን አካባቢ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ትክክለኛ መስሎ የታየውን ፍርድ ሊሰጥ እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 241 ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ ተከራካሪ ወገኖች በጽሑፍ ያቀረቡትን ድንጋጌዎች አግባብ ጭብጥ ለመመስረት እንዲያግዝ ሲሆን በጽሑፍ ማመልከቻው ላይ ያልሰፈረን ዳኝነት ለመጠየቅ የሚያስችል ያለመሆኑን የድንጋጌው ይዘትና መንፈስ ያስረዳል፡፡ ተከራካሪ ወገኖች በመጀመሪያው ክርክር ላይ ካቀረቡት በቀር ሌላ ተጨማሪ ሙግት ወይም ሌላ ማስረጃ ማስቀረብና መመርመር የሚያስፈልግ ከሆነ ወይም ቀድሞ የተያዘው ጭብጥ የሚሻሻል ወይም ተጨማሪ ጭብጥ የሚያዝ መሆኑ ከታመነም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 255 እና 251 አግባብ የሚፈፀም እንጂ ያለህጋዊ ምክንያት በማናቸውም የክርክር ደረጃ የቀረበ ክርክር ሁሉ ተቀባይነት የሚያገኝበት የክርክር አመራር የለም፡፡

No comments:
Post a Comment