የመሰማት መብት በዝምታ የታለፈባቸው ድንጋጌዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ ፈቃድ የተሰጠው ኩባንያ አሰራሩ ለአደጋ ያልተጋለጠ፣ አስተማማኝና ጤናማ መሆኑን ለማረጋገጥ የኩባንያውን ዳይሬክተር፣ ዳይሬክተሮች ወይም ዋና ስራ አስፈፃሚ ከስራ ማገድ ወይም ማሰናበት ይችላል፡፡a ባንኩ በምን ዓይነት ሁኔታዎችና በቂ ምክንያቶች እርምጃውን እንደሚወስድ ስልጣን በሰጠው አዋጅ ቁ. 807/2005 ላይ አልተመለከተም፡፡ በተጨማሪም እርምጃው የሚወሰድባቸው የኩባንያው ኃላፊዎች የተከሰሱበትን ጉዳይ ባንኩ ፊት ቀርበው ለማስረዳትና ማስተባበያ ማስረጃ ለማቅረብ በአጠቃላይ የመሰማት መብታቸው በአዋጁ አልተጠበቀም፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በማስታወቂያ አዋጅ ቁ. 759/2004 አንቀጽ 31/3/ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር የውጭ ማስታወቂያን ሳይጨምር የአዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ የተሰራጨን ማንኛውንም ማስታወቂያ ይመረምራል፣ ያግዳል፣ የአፀፋ ማስታወቂያ እንዲወጣ ያዛል፡፡ ነገር ግን እርምጃውን ከመውሰዱ በፊት የማስታወቂያውን ባለቤት የመስማት ግዴታ አልተጣለበትም፡፡ በእርግጥ ለእርምጃው ምክንያት የሆኑት አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ህሊናዊ ፍርድ የሚጠይቁ እንደመሆኑ ማስረጃ-ነክ ክርክሮች አይኖሩም፡፡ ሆኖም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተቃራኒውን ወገን መስማት የተዛባ አመለካከትን በማጥራት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም ባለስልጣኑ የማስታወቂያ ባለቤቶችን እይታ በጥልቀት ይረዳል፡፡ ለምሳሌ በአዋጁ ክልከላ ከተደረገባቸው ህግን ወይም መልካም ስነ ምግባር እንደሚጻረሩ የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎች መካከል በአንቀጽ 7/6/ እና /8/ የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፡
የህብረተሰቡን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትና ደህንነት ለጉዳት የሚያጋልጥ ድርጊት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ማስታወቂያ
ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ የጽሑፍ መልዕክት፣ ምስል፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ ፊልም ወይም መሰል አቀራረብን የያዘ ማስታወቂያ

No comments:
Post a Comment