ካሳ እና ንብረት ማስመለስ
የመንግስት ተቋም በግል ወይም በመንግስታዊ ተግባሩ ላደረሰው ጉዳት ካሳ ሊከፍል ይገደዳል፡፡ ተቋሙ ስልጣኑን በመጠቀም የሚፈጽማቸው ተግባራት መንግስታዊ ሲሆኑ የተቀሩት ግን ግላዊ ናቸው፡፡ ባለቤትነቱ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተመዘገበ መኪና በንብረት ወይም በአካል ላይ ጉዳት ሲያደርስ ድርጊቱ ህግ በማስከበር ሂደት የተከሰተ አይደለም፡፡ ስለሆነም ግላዊ ነው፡፡ ኃላፊነቱ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 2126/2/ ይወሰናል፡፡ ድንጋጌው መንግስት ኃላፊነት የሚሸከመው ጉዳቱ የደረሰው ሰራተኛው ወይም ሹመኛው የመንግስት ስራ ሲሰራ የደረሰ እንደሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የባለስልጣኑ አሽከርካሪ ጉዳት ያደረሰው የግብር ገማች ኮሚቴ አባላትን ለስራ ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከሆነ ባለስልጣኑ ተጎጂውን የመካስ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ የመኪና አደጋ በሌላ የመንገስት ተቀጣሪ ባልሆነ ግለሰብም ሊደርስ ይችላል፡፡ ስለሆነም ከባለስልጣኑ አንጻር ተግባሩ ግላዊ ነው፡፡
መንግስታዊ የሚባለው ተግባር ደግሞ አንድ የመንግስት ተቋም በህግ የተቋቋመለትን ዓላማ በማከናወን ሂደት ስልጣኑን በመገልገል የሚፈጽመው ድርጊት ነው፡፡ ለምሳሌ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኗል በሚል የያዘውን መኪና ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ በስህተት መሆኑን ሲረዳ መኪናውን መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ የማይለቅ ከሆነ ግን የመኪናው ባለቤት ንብረቱን የማስመለስ እና ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ የባለስልጣኑ ተግባር ህገ ወጥ መሆኑ ከተረጋገጠ ጥያቄው በፍርድ ቤት ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ህጋዊነትን በማጣራት ሂደት የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ መኪናው ለባለቤቱ እንዲመለስ እንዲሁም ለተቋረጥበት ጥቅም እንዲካስ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ባለስልጣኑ ከስልጣኑ በላይ አሳልፎ ስለመስራቱ ወይም አለአግባብ በስልጣን ስለመገልገሉ በጭብጥነት ይያዛል፡፡ ይህም ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ህግ አንደኛው የስልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ እንደሆነ ያሳየናል፡፡
በሰ/መ/ቁ. 47935a ተጠሪ ወደ አገር ውስጥ ይዘውት የገቡትን ዶላር ለጉምሩክ ካስመዘገቡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መቶ ሰማንያ ቀናት አሳልፈው ከአገር ሲወጡ አመልካች ገንዘቡን ከልክሏቸዋል፡፡ አመልካች ለክልከላው ምክንያት ያደረገው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ሲሆን በመመሪያው መመሰረት በጊዜያዊነት ለጉብኝት ወይም ለንግድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሰዎች ለጊዜው በእጃቸው የያዙትን የውጭ ምንዛሬ ለጉምሩክ አስመዝግበው ማስረጃ ከያዙ ከአንድ መቶ ሰማኒያ ሶስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ይዘውት የመጡትን የውጭ ምንዛሬ ይዘው ለመውጣት ፈቃድ አያስፈልጋቸውም፡፡ ተጠሪ ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ክስ ሲያቀርቡ የክሱ ምክንያት ከውል ውጭ ኃላፊነት ህግ ውስጥ የሚመደብ የንብረት ማስመለስ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ ፍርድ ቤቱ የአመልካችን ድርጊት ህጋዊነት መወሰን ይኖርበታል፡፡ በሌላ አነጋገር አመልካች ገንዘቡን የመውረስ ስልጣን እንዳለውና እንደሌለው በጭብጥነት ተይዞ ሊጣራ ይገባዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ተመዝግቦ የገባ የውጭ የምንዛሪ የሚወጣበትን ጊዜ ገደብ ከመደንገግ ውጭ የጊዜውን ማለፍ ህጋዊ ውጤት አይናገርም፡፡ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች የበታች ህጎች እንደመሆናቸው በግልጽ ካልተደነገገ በቀር የግለሰቦችን መብት እንደሚያሳጡ ተደርገው መተርጎም የለባቸውም፡፡ ስለሆነም የመመሪያው ዝምታ የተጠሪ መብት የማሳጣት ውጤት የለውም፡፡ በሌላ በኩል አመልካች የውጭ ምንዛሪውን እንዲወስዱ መፍቀዱ የጊዜ ገደቡን ትርጉም ያሳጣዋል፡፡
የስር ፍርድ ቤቶችና የሰበር ችሎት የተከተሉት የህግ አተረጓጎም የመመሪውን ገደብ ከአመልካችን መብት ጋር ያስታርቃል፡፡ ይኸውም አመልካች ያስመዘገቡትን የውጭ ምንዛሪ በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንዲወስዱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የውሳኔውን ይዘት በአስተዳደር ህግ መነጽር ስናየው አመልካች የውጭ ምንዛሪውን የማስቀረት ስልጣን ባይኖረውም በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንዲከፈል ማድረግ ይችላል፡፡

No comments:
Post a Comment