17 Oct 2020

የአስተዳደር ህግ በኮመን ሎው እና ሲቪል ሎው አገራት፡ ንጽጽራዊ እይታ።


የአስተዳደር ህግ በኮመን ሎው እና ሲቪል ሎው አገራት፡ ንጽጽራዊ እይታ።
የኮንቲኔንታል እና የኮመን ሎው የአስተዳደር ህግ ስርዓት በሁለት ነጥቦች መሰረታዊ ልዩነት ይታይበታል፡፡ የመጀመሪያውን ልዩነት ለመረዳት የፈረንሳይ የአስተዳደር ህግ ስርዓት መገለጫ ከሆኑት ከሚከተሉት ሁለት ገፅታዎች እንነሳለን፡፡
በግለሰብና በአስተዳደር አካላት መካከል እንዲሁም የአስተዳደር አካላት በመካከላቸው ያለው ግንኙነት የሚገዛውና የሚመራው ከፍትሐብሔር ህግ (Civil Law) ሙሉ በሙሉ በተለየና በተነጠለ የአስተዳደር ህግ አማካኝነት ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ከፍትሐብሔር ህግ ጋር ሳይቀየጥ ራሱን ችሎ የቆመ የህግ ነው፡፡
በግለሰብና በአስተዳደር አካላት እንዲሁም በአስተዳደር አካላት በመካከላቸው የሚፈጠሩ የአስተዳደር ክርክሮች የሚዳኙት ራሳቸውን ችለው በተቋቋሙ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች አማካይነት ነው፡፡ መደበኛ ቤቶች የአስተዳደር ክርክሮችን የመዳኘት ስልጣን የላቸውም፡፡
የአስተዳደር ህግ በእንግሊዝ፤ በአሜሪካና በሌሎች የኮመን ሎው የአስተዳደር ህግ ስርዓትን በሚከተሉ አገራት ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን ችሎ የቆመ የህግ ክፍል ተደርጐ እየተቆጠረ ቢሆንም የአስተዳደር ክርክሮች ከመደበኛ ፍ/ቤቶች የስልጣን ክልል ውጭ አይደሉም፡፡ በእርግጥ በብዙ የኮመን ሎው አገራት የአስተዳደር ክርክሮችን ከመደበኛ ፍ/ቤቶች መዋቅር ውጪ በተቋቋሙ የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative Tribunals) አማካይነት መዳኘት እየተለመደና እያደገ መምጣቱ አይካድም፡፡ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ ካናዳ ወዘተ ከመደበኛ ፍ/ቤት ጋር ተቀራራቢ የዳኝነት ስልጣን ያላቸው የአስተዳደር ጉባዔዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሆኖም እነዚህ አስተዳደራዊ የዳኝነት አካላት ከመደበኛው የፍ/ቤት ስርዓት በተጓዳኝ የተቋቋሙ እንጂ ራሱን ችሎ የቆመ መዋቅር የላቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በፈረንሳይ የአስተዳደር ህግ የአስተዳደር ክርክሮች ከመነሻው እስከ መጨረሻው ታይተው የሚቋጩት ለዚህ ሲባል በሶስት እርከን በተቋቋሙት የአስተዳደር ፍ/ቤቶች አማካይነት ነው፡፡
በዚሁ መሰረት የአስተዳደር ክርክርን የሚመለከት ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ፍ/ቤት (tribunaux administratif) ታይቶ ይግባኙ በይግባኝ ሰሚ የአስተዳደር ፍ/ቤት (Cours administratives d'appel) ይሰማል፡፡ የፍ/ቤቶቹ ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለበት በአስተዳደር ጉዳዮች የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠውና Conseil d'Etat (የመንግስት ምክር ቤት) ተብሎ የሚጠራው ተቋም ይግባኝ የማይባልበት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፡፡a መደበኛ ፍ/ቤቶች በግለሰቦች መካከል ከሚነሱ ክርክሮች ባለፈ በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት የዳኝነት ስልጣን የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ በፈረንሳይ እና በአብዛኞቹ የሲቪል ሎው አገራት ይህ የሁለትዮሽ የፍ/ቤት ስርዓት የአስተዳደር ህግ ስርዓታቸው ዋነኛ መግለጫ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የፍ/ቤት ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ህገ መንግስታዊ ስርዓታቸው በህግ የበላይነት፤ በስልጣን ክፍፍልና በፍ/ቤቶች ነፃነት መርሆዎች ላይ ለተተከለው ለእንግሊዞች ሆነ ሌሎች የኮመን ሎው አገራት እንደ ባዕድ ተደርጐ በመወሰዱ በዚህ ረገድ ያለው ልዩነት አሁንም ድረስ ከፊል መቀራረብ እንኳን አይታይበትም፡፡ ስለሆነም የግለሰቦችን መብትና ነፃነት በገለልተኛ ፍ/ቤቶች አማካይነት ማስከበርና ማረጋገጥ የአስተዳደር ህጋቸው መገለጫነቱ በገሀድ ይንፀባረቃል፡፡ በእነዚህ አገራት በስልጣን፣ በስነ-ስርዓት፤ በአደረጃጀተ ወዘተ…ተቀራራቢነት ያላቸው የአስተዳደር ጉባዔዎች ቢኖሩም የሚሰጡት ውሳኔ በይግባኝ ወይም በአጣሪ ዳኝነት (judicial review) መልክ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ይታረማል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የህጉን ምንጮች በተመለከተም በሁለቱ ጎራዎች መካከል ልዩነት ይታይል፡፡ በተለምዶ እንደሚታወቀው የሲቪል ሎው መሰረቱ የተጠቃለሉ የህግ መዛግብት (codified laws) ቢሆንም የአስተዳደር ህግ በአብዛኛው በዳኞች የተፃፈ ህግ (Judge-made law) ነው፡፡ በኮመን ሎው አገራት ደግሞ የአስተዳደር ህግ የኮመን ሎው መሰረቱን ሙሉ በሙሉ ባይለቅም በአብዛኛው ምንጭና መሰረቱን በተጻፉ ህጐች (statutes) ላይ አድርጓል፡፡ የፈረንሳይ የአስተዳደር ህግ በአስተዳደር ጉዳዮች የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው የመንግስት ምክር ቤት (Conseil d'Etat) እንዲሁም በመደበኛ እና በአስተዳደር ፍ/ቤቶች መካከል የሚነሱ የዳኝነት ስልጣን ግጭቶችን የማየት የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው tribunal des conflictes ተብሎ የሚጠራው ፍ/ቤት ድምር የስራ ውጤት ነው፡፡b እነዚህ ፍ/ቤቶች የፈረንሳይ የአስተዳደር ህግ አሁን ለያዘው መልክና ቅርጽ ፈር ቀያሾች ናቸው፡፡


No comments:

Post a Comment

Popular posts

Recent Posts

LikeBtn

Type

አስተማሪ የሆኑት የችሎት ድራማ ቪዲዮዎች

DOCUMENT & FILES

Criminal Procedure Code 6/2013 PDF by ሕግ እና ፍትህ on Scribd